tgoop.com/news_et/15
Last Update:
" ለረጅም ግዜ ታግሰናል። ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ነገር በህግና ስርዓት መልክ እንዲይዝ እናደርጋለን " - የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የሰላምና የፀጥታ ቢሮ
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ፤ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
" በአሁኑ ሰዓት የክልሉ የፀጥታ ሃይል በተናበበና በተቀናጀ አኳሃን በመስራት በቅርቡ ከሌላው ጊዜ የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ እንዲኖር በመስራት ላይ እንገኛለን " ብሏል።
የህግ ልዕልና ማረጋገጥ እንዳለ ሆኖ በተለይ ከብረታ ብረት ስርቆት ጋር ተያይዞ የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ እንደ መነሻ በመውሰድ በወርቅ ፣ ማዕድንና መሬት ዘረፋና እገታ እንዲሁም በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ስርዓት የማስያዝ ስራዎችና እርምጃዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብሏል።
" የተጀመረው ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ ያስደነገጣቸው ህገ-ወጥ አካላት ጉዳዩ ፓለቲካዊ መልክ ሊያስይዙት እየሞከሩ ነው " ያለው ቢሮው " በማህበራዊ የትስስር ገፆች በሚነዛው በሬ ወለደ ውዥንብር ሳንደናገጥ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን " ሲል አሳውቋል።
" ለረጅም ግዜ ታግሰናል ፤ ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ነገር በህግና ስርዓት መልክ እንዲይዝ እናደርጋለን " ሲል አረጋግጧል።
እስካሁን በተለያዩ ህገ-ወጥ ተግባሮች ተሳተፉ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል።
እነማን እንደሆኑ በስም የተጠቀሰ ነገር የለም።
ሳምንቱን በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ከትግራይ ፓሊስ ኮሚሽን 3 ከፍተኛ አመራሮች ከሃላፊነት ተነስተው በሌሎች መተካታቸው ሲዘዋወር ነበር።
ከብረታ ብረት ስርቆትና ሌሎች ህገ-ወጥ ተግባራት ጋር በተያያዘም በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ቢነገርም መረጃውን የጊዚያዊ አስተዳደሩና የፀጥታና ሰላም ቢሮ ማረጋገጫ ሊሰጥበት አልቻለም።
BY Et News
Share with your friend now:
tgoop.com/news_et/15