Warning: Undefined array key 0 in /var/www/tgoop/function.php on line 65

Warning: Trying to access array offset on value of type null in /var/www/tgoop/function.php on line 65
- Telegram Web
Telegram Web
                          †                          

[    🕊    ገ ድ ለ   ቅ ዱ ሳ ን   🕊     ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[ ቅዱስ መቃርዮስ ካስተማረው ትምህርት ]

          [      ክፍል  ሰባ ዘጠኝ      ]

                         🕊  

[  ሁለት አኃው አብረው ለመኖር ለጠየቁት የመለሰው ! ]

🕊

❝ አንድ አረጋዊ ከአንድ እኁ ጋር ሆነው አባ መቃርዮስን እንደ ጎበኙት ተነገረ፡፡ እነርሱም ፦ “አባታችን ሆይ ፣ እንደ አንድ ሰው ሆነን አብረን መኖር እንፈልጋለን” አሉት:: እርሱም አረጋዊውን እንዲህ አለው ፦ “መጀመሪያ እንደ እረኛ ሁን፡፡ ክፉ ትል ተሸካሚ [አስተላላፊ] የሆነች ወፍ በበጎች መካከል ትሎችን ብትዘራባቸው ትሎቹን እስከሚገድላቸው ድረስ ለታመመችው በግ መድኃኒት ይሰጣታል:: አንድ በግ ተላላፊ የሆነ በሽታ የሚዘራ ከሆነ ግን በሽታውን እስከሚያስወግደው ድረስ መድኃኒት ይጠቀማል፡፡”

አረጋዊውም ፦ “የዚህን አባባል ትርጉም ንገረኝ" አለው:: አባ መቃርዮስም እንዲህ አለው ፦ “ትል የሚዘራው ወፍ እንደ ዲያብሎስ ነው ፣ በጉ ደግሞ ከአንተ ጋር እንደሚኖረው ወንድም ያለ ነው። ትሎቹ ደግሞ በነፍስ የሚኖሩና በልብ የሚራቡ የአጋንንት ፍትወታትና ክፉ ምኞቶች ናቸው። ትሎች በሰውነት ቁስል ላይ እንደሚኖሩት ማለት ነው። በሽታውን የሚያስወግደው መድኃኒት ደግሞ በመንፈስ ማደግ ፣ ትኅርምትና መድኃኒት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት
ነው።

ነፍስን የሚያነጹዋት ነገሮች እነዚህ ናቸው ፤ አጋንንት በእኛ ላይ ከሚያሰማሯቸው ክፉ ጠላቶቻችን ከሆኑት ከእኩያት ፍትወታትና ከክፋቶች ሁሉ የሚያጠሯት እነዚህ ናቸው::”

ያን እኁም እንዲህ ብሎ ተናገረው ፦ “ልጄ ሆይ ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መሥዋዕትና መባዕ አድርጎ እስኪያቀርበው ድረስ አባቱን እንደ ታዘዘው እንደ ይስሐቅ ሁን ፤ እርሱ ለአባቱ በመታዘዙ በቤተ ክርስቲያን መዝገብ ውስጥ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ተጽፏልና፡፡ ❞

🕊

የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡

ይቆየን !


💖                      🕊                      💖
💛
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊       [   ምክረ ቅዱሳን   ]        🕊

▷   "  መንፈሳዊ የድካም ዓይነቶች ! "

[    💖   አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ   💖    ] 

[                        🕊                        ]
-------------------------------------------------

❝ ድካሜንና መከራዬን እይ ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።

ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል። ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር። አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ። ❞

[   መዝ.፳፭፥፲፰  ]


🕊                       💖                     🕊
🕊

[ † እንኳን ለቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

🕊 † ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ † 🕊

†  ልደት  †

† መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ [ከአረማዊ ጋብቻ] አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት ፳፬ [24] ቀን በ፲፪፻፮ [1206] ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፳፬ [24] ቀን በ፲፪፻፯ [1207] ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

† ዕድገት †

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን [ብሉያት: ሐዲሳትን] ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::

† መጠራት †

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት [ተክለ ሥላሴ] ይሁን:: ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

† አገልግሎት †

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ [ጽላልሽ] አካባቢ ብቻ በ፲ [10] ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ፪ [2] መልክ ነበራት::

፩ኛ. ዮዲት [ጉዲት] በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
፪ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ
ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን [ጠንቋዮችን] አጥፍተዋል::

† ገዳማዊ ሕይወት †

† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ፫ [3] ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ፲፪ [12] ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ፯ [7] ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ፯ [7] ዓመታት: በአጠቃላይ ለ፳፮ [26] ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ [ዞረሬ] ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ፳፪ [22] ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም ፮ [6] ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ፯ [7] ዓመታት ጸልየዋል::

† ስድስት ክንፍ †

ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

ከወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ :-

- በቤተ መቅደስ ብስራቱን
- በቤተ ልሔም ልደቱን
- በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
- በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
- በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::

በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::

† በዚያም :-

- የብርሃን ዐይን ተቀብለው
- ፮ [6] ክንፍ አብቅለው
- የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
- ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
- ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
- ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
- "ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

† ተአምራት †

የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
- ሙት አንስተዋል
- ድውያንን ፈውሰዋል
- አጋንንትን አሳደዋል
- እሳትን ጨብጠዋል
- በክንፍ በረዋል
- ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

† ዕረፍት †

† ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው: መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ፺፱ [99] ዓመት: ከ፰ [8] ወር: ከ፩ [1] ቀናቸው ነሐሴ ፳፬ [24] ቀን በ፩፻፮ [1306] ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: ፲ [10] ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

† በዚህ ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለ፳፪ [22] ዓመታት የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው ለ፯ [7] ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስባለች::

[ † ጥር ፳፬ [24] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
፪. ቅድስት ማርያ ግብጻዊት
፫. ታላቁ አባ ቢፋ
፬. አባ አብሳዲ ቀሲስ
፭. ቅዱሳን ጻድቃነ ሐውዚን

[ † ወርኀዊ በዓላት ]

፩. አቡነ ዘዮሐንስ [ዘክብራን ገብርኤል-ጣና]
፪. ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ
፫. ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ
፬. ቅዱስ ሙሴ ጸሊም
፭. ቅዱስ አጋቢጦስ
፮. ሃያ አራቱ ካህናተ ሠማይ

" በድካም : አብዝቼ በመገረፍ : አብዝቼ በመታሠር : አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት : ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት : በራብና በጥም : ብዙ ጊዜም በመጦም : በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: " † [፪ቆሮ ፲፩፥፳፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
🕊                       💖                     🕊


[ ጻድቅ ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ]

🕊                       💖                     🕊

በዚህ ዕለት አባታችን ተክለ ሃይማኖት ለ22 [ ፳፪ ] ዓመታት የቆሙበት ቀኝ እግራቸው መሠበሩንና በአንድ እግራቸው ለ7 [ ፯ ] ዓመታት ቆመው መጸለያቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስባለች።

[ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሥላሴን በማመን ተተከለ [ ተገኘ ]። በማስተዋል ስሙት ፣ በጸጥታ እና በርጋታም ሆናችሁ አድምጡት። በጌታው የሠርግ ቀን [ በዕለተ ምጽዓት ] በመከራው ከሚገኘው ደስታ ትሳተፉ ዘንድ ፣ የነፍስ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ብላችሁ መጥራት ይቻላችሁ ዘንድ በመገዛት ፣ በማኅሌት እና ኅሊናን በመሰብሰብ በዐሉን አክብሩ። ]

[ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ]

ሰዳዴ ጽልመት አባታችን ቅዱስ ተክለሐይማኖት

❝ አንተ የደከምክበት ያ መልካም አዝመራ
እንክርዳድ ሞላበት ተክለ አብ ቶሎ ና
አውሬው ሰልጥኖብን ተፍገምግመናል
ኪዳን የሚጠብቅ አባት ያስፈልጋል፡፡ ❞


🕊                       💖                     🕊
                       †                       

  [  🕊  ድምፀ ተዋሕዶ   🕊  ]  

🍒▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬🍒               

[  ሕይወት የሚገኝባቸው የቅድስት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርቶች በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በድምፅ ይቀርባሉ።  ]

[   ሳምንታዊ መርሐ-ግብር   ]

🕊             
             
❝ ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል ? ቃልህን በመጠበቅ ነው። ❞  [ መዝ . ፻፲፱ ፥ ፱  ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[ ሕይወተ ወራዙት [ የወጣቶች ሕይወት ! ]

             [   ክፍል -  አሥር  -    ]

            💖   ድንቅ ትምህርት  💖

[ በመምህራችን በቀሲስ ኅብረት የሺጥላ ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

      [    መንፈሳዊ ንጽሕናን መጠበቅ    ]


የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል። ❞ [ ምሳ.፩፥፴፫ ]


🕊                        💖                      🕊
                             👇
🕊

[  † እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ [ ፒሉፓዴር ] ዓመታዊ የተአምር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊  †  ቅዱስ መርቆሬዎስ ኃያል  †  🕊

† ለክርስትና ሃይማኖት የሚከፈል ትልቁ ዋጋ ሰማዕትነት ነውና ቤተ ክርስቲያን ለምስክሮቿ ሰማዕታት ልዩ ክብር አላት:: ከኮከብ ኮከብ እንዲበልጥ ሁሉ ከሰማዕታትም ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ቅዱስ መርቆሬዎስን የመሰሉት ደግሞ ክብራቸው በእጅጉ የላቀ ነው::

ቅዱስ መርቆሬዎስን ብዙ ጊዜ ሊቃውንት "ካልዕ [ ሁለተኛው ] ሊቀ ሰማዕታት" ሲሉ ይገልጹታል:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-
በ፪ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮም ግዛቶች በአንዱ [ አስሌጥ ] ከአባቱና ከሚስቱ ጋር የሚኖር "አሮስ" የሚሉት ሰው ይኖር ነበር:: ሚስቱ ደም ግባት የሠመረላት: እርሱም ደግነት ያለው ሰው ቢሆኑም የሚያመልኩት ግን ጣዖትን ነበር::

አንድ ቀን አሮስ ሚስቱን ከቤት ትቶ ለአደን ከአባቱ ጋር ወጣ:: እንደ ልማዳቸው ወጥመዱን አስተካክለው ተደበቁ:: የወጥመዱ ደወል ሲያቃጭል: "እንስሳ ተያዘልን" ብለው ሲሯሯጡ ዐይናቸው ያየው ነገር በድንጋጤ እንዲፈዙ አደረጋቸው:: ፪ ገጻተ ከለባት በወጥመዱ ውስጥ ተይዘው ነበር::

እነዚህ ፍጡራን ሰዎች ናቸው:: ግን ባልታወቀ የተፈጥሮ አጋጣሚ እንደዚህ እንደ ሆኑ ይታመናል:: ግን እጅግ ግዙፍ: ከአንገታቸው በላይ እንደ ውሻ: ወገባቸው እንደ ሰው: ጉልበታቸው እንደ አንበሳ ሲሆን ታችኛው እግራቸው የጋለ የናስ ብረት ነው የሚመስል::

እነዚህን ፍጡራን ሰማያዊ ካልሆነ ምድራዊ ፍጡር አይችላቸውም:: አንበሳና ነብርን እንኩዋ እንደ ጨርቅ በጣጥሰው ይጥሏቸው እንደ ነበር ይነገራል:: ዐይናቸው እንደ እሳት ይነድ ስለ ነበር ማንም ትክ ብሎ ሊያያቸው አይችልም:: ምሥጢራቸውን ግን የሚያውቀው የፈጠራቸው አምላክ ነው::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና:- አሮስና አባቱ ባዩአቸው ጊዜ ደንግጠው ወደቁ:: ገጻተ ከለባቱ የብረት ወጥመዱን እንደ ክር በጣጥሰው የአሮስን አባት በቅጽበት በሉት:: አሮስን ሊበሉት ሲሉ ግን ድንገት ቅዱስ መልአክ ወርዶ በእሳት ሰይፍ አጠራቸው::

"ከእርሱ የሚወጣ ቅዱስ ፍሬ አለና እንዳትነኩት" አላቸው:: ወዲያውም መልአኩ ያንን ኃይለኝነታቸውን አጠፋው:: በዚህ ጊዜ ፪ቱም ወደ አሮስ ሒደው ሰገዱለት:: አሮስም ወደ ቤቱ ወስዶም ደበቃቸውና የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ነገራት::

ጥቂት ቆይታም ጸንሳ ወለደች:: ልጃቸውን ፒሉፓዴር [ ፒሉፓተር ] ሲሉ ስም አወጡለት:: ትርጉሙም "መፍቀሬ አብ - የአብ ወዳጅ" ማለት ነው:: ከዚያም አሮስ ሚስቱን : ልጁንና ፪ቱን ገጻተ ከለባት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዶ ተጠመቀ::

አበው ካህናት እሱን "ኖኅ" : ሚስቱን "ታቦት" : ልጁን ደግሞ "መርቆሬዎስ" ሲሉ ሰየሟቸው:: መርቆሬዎስ ማለትም "ገብረ ኢየሱስ ክርስቶስ - የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ" እንደ ማለት ነው::

ከዚያም ደስ እያላቸው: ክርስቶስን እያመለኩ: ነዳያንን እያሰቡ: ልጃቸውን መርቆሬዎስን አሳደጉ:: ነገር ግን የገጻተ ከለባት ወሬ በመሰማቱ ንጉሡ "ካላመጣሃቸው" አለው:: ኖኅ ጸልዮ ወደ ኃይለኝነታቸው መልሷቸው ስለነበር ፊታቸው ገና ሲገለጥ ብዙ አሕዛብ በድንጋጤ ሞቱ::

ንጉሡም ስለ ፈራ ኖኅን የጦር መኮንን አደረገው:: በጦርነት ጊዜም ገጻተ ከለባቱ ኃይላቸው ስለሚመለስ ተሸንፎ አያውቅም ነበር:: አንድ ጊዜ ግን 2ቱን ገጻተ ከለባት ንጉሡ አታሎ ወሰዳቸው:: ሃይማኖታቸውን ሊያስክዳቸው ሲል "እንቢ" በማለታቸው አንዱ ሲገደል ሌላኛው አምልጦ ጠፋ::

በዚያ ወራትም ኖኅ ለጦርነት ወጥቶ ተማረከ:: ንጉሡ ደግሞ ታቦትን "ላግባሽ" ስላላት የ፭ ዓመት ልጇን ቅዱስ መርቆሬዎስን ይዛ ተሰደደች:: በስደት ጥቂት እንደ ቆየች ግን ባሏን ኖኅን አየችው::

እርሷ ብታውቀውም እርሱ ዘንግቷት ነበር:: በሁዋላ ግን በሕጻኑ መርቆሬዎስ አማካኝነት ማስታወስ በመቻሉ ደስ አላቸው:: በዚያው በሮም ዙሪያ ሳሉም አንዱ ገጸ ከልብ መጥቶ አገኛቸው:: በዚህም ምክንያት በስደት ሃገርም መኮንን ሆኖ ተሾመ::

በዚያም ቤተ ክርስቲያንን አንጾ: ቤቱን ቤተ ነዳያን አድርጐ ኖኅ ለዓመታት ኖረ:: ቅዱስ መርቆሬዎስ ወጣት ሲሆንም ወላጆቹ ታቦትና ኖኅ ዐረፉ:: እርሱ ከባልንጀራው ገጸ ከልብ ጋር ሆኖ በጾምና ጸሎት ሲኖር ስለ አባቱ ፈንታ የጦር መሪ አደረጉት::

በጦርነትም እጅግ ኃያል: በሰው ዘንድም ፍጹም ተወዳጅ: የጾምና የጸሎት ሰው ሆነ:: ያን ጊዜ ግን ዳክዮስ ንጉሡ ክርስቶስን በመካዱ ምዕመናን ላይ ሞት ታወጀ:: በጊዜው ደግሞ የበርበር ሰዎች በሮም መንግስት ላይ ጦርነትን በማንሳታቸው ዳኬዎስና ቅዱስ መርቆሬዎስ ለጦርነት ወጡ::

ነገር ግን በርበሮች እንደ አሸዋ ፈሰው ብዛታቸውን ሲያይ ንጉሡ ደነገጠ:: ለማግስቱ ቀጠሮ ተይዞ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲጸልይ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሰይፍ ሰጠው::

በማግስቱም "ምን ይሻላል?" ሲባል ቅዱስ መርቆሬዎስ "እኔ የክርስቶስ ባሪያ ነኝና ብቻየን እቋቋማቸዋለሁ" ቢል ሳቁበት::

እርሱ ግን በጥቁር ፈረሱ [ አብሮት ያደገ ነው ] ተጭኖ በርበሮችን "ጠብ ይቅርባችሁ: በሰላም ሒዱ" ቢላቸው ተሳለቁበት:: ያን ጊዜም ጸሎት አድርሶ የመልአኩን ሰይፍ ሲመዘው ብዙዎቹ ወደቁ:: ከበርበሮችም ለወሬ ነጋሪነት እንኩዋ የተረፈ አልነበረም::

ነገሩ በሮም ሲሰማ ታላቅ ሐሴት ሆነ:: ዳሩ ግን ከሃዲው ዳኬዎስ "ድሉ የጣዖቶቼ የነ አዽሎን ነው" በማለቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሲያዝን አደረ::

በ፫ኛው ቀንም "ለጣዖት ሠዋ" የሚል ትዕዛዝ ከንጉሡ ዘንድ መጣ:: ቅዱሱ ግን ወደ አደባባይ ሔደ:: የክብር ልብሱንና መታጠቂያውን አውልቆ በንጉሡ ፊት ወረወረው::

"ሃብትከ ወክብርከ ይኩንከ ለኃጉል:: ሊተሰ ክብርየ ክርስቶስ ውዕቱ:: [ ለእኔስ ክብሬ ክርስቶስ ነውና ንብረትህ ለጥፋት ይሁንህ ]" ሲልም ንጉሡን በአደባባይ ዘለፈው:: ዳኬዎስም በቁጣ እሳት አስነድዶ: የብረት አልጋውንም አግሎ ቅዱስ መርቆሬዎስን በዚያ ላይ አስተኛው::

ያም አልበቃ:: ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲደበድቡት ደሙ ፈሶ እሳቱን አጠፋው:: ለዚያ ነው ሊቃውንት :-

"አመ አንደዱ ላእሌከ ውሉደ መርገም::
እምቅሡፍ አባልከ እንተ ውኅዘ ደም::
አርአያ ዝናም ብዙኅ አጥፍኦ ለፍህም::" ያሉት::

ከዚያም ወስደው ወኅኒ ቤት ውስጥ ጣሉት:: ክርስቶስን ያስክደው ዘንድ በረሃብ: በግርፋት: በእሳት: በስለትም አሰቃየው:: በመጨረሻ ግን አሰቃይተው እንዲገድሉት ወደ እስያ ሰደደው:: በስፍራውም ብዙ አሰቃይተው ኅዳር ፳፭ ቀን አንገቱን ሰይፈውታል::

እርሱ ካረፈ በሁዋላም የተባረከ ፈረሱ ለዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል:: አረማውያንንም ከአፉ በወጣ እሳት አጥፍቷል:: ተአምረኛውና ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ መርቆሬዎስ በ፪ መቶ [200] ዓ/ም እንደ ተወለደ: በ፪ መቶ ፳ [220] ዓ/ም መከራ መቀበል እንደ ጀመረና በ፪ መቶ ፳፭ [225] ዓ/ም ሰማዕት እንደሆነ ይታመናል::
ሰማዕቱ በዚህች ዕለት : በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያኖችን ያሰቃይና ይገድል የነበረውን ዑልያኖስን ያጠፋበት መታሠቢያ ይከበራል::
የቅዱሱ ክብር ታላቅ ነው !

† አምላከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በከበረ ቃል ኪዳኑ ይጠብቀን:: ከርስቱም አያናውጠን:: ከበረከቱም ይክፈለን::
ቸሩ እግዚአብሔር እድሜ ለንስሃ ዘመን ለፍሥሃ አይንሳን::
[   † ጥር ፳፭ [ 25 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕተ ሮሜ
፪. ቅዱሳን ባስልዮስና ጎርጎርዮስ
፫. ብፁዕ አባ ዼጥሮስ ጽሙድ [ለምጽዋት ራሱን የሸጠ አባት]
፬. ቅዱስ ሰብስትያኖስ ሰማዕት
፭. ቅዱስ አስኪላ ሰማዕት

[   † ወርሐዊ በዓላት     ]

፩. ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፪. ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፫. ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፬. አቡነ አቢብ
፭. አባ አቡፋና

" የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና . . . " † [ ዕብ.፲፩፥፴፭ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2025/02/02 02:40:04
Back to Top
HTML Embed Code: