tgoop.com/ortodoxtewadochannal/4199
Last Update:
ንስጥሮሳውያን ማናቸው
ንስጥሮሳውያንን ለመረዳት በመጀመሪያ ስለ ንስጥሮስ እንመልከት። ንስጥሮስ በ5ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ ሲሆን በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን የተማረና ከ 428 እስከ 431 የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የነበረ ነው። ነገር ግን በ431 ዓ.ም በተካሄደው ሶስተኛው የቤተክርስቲያን ጉባኤ ተወግዞ ከጵጵስናው የተሻረ ነው።
ንስጥሮስ የተወዘገው በኤፌሶን ጉባኤ በ431 ሲሆን ይህም የሆነው የቤተ ክርሰቲያን መከፋፈል ሳይመጣ ነው። ማለትም ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ፣ ምስራቅ ኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ የሚባሉት መከፋፈሎች ሳይመጡ በፊት፣ የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን (early church) በሚባለው ዘመን ነው።
የንስጥሮስ አስተምህሮ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና እመቤታችን ድንግል ማርያም ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ እመቤታችን ድንግል ማርያም የአምላክ እናት አይደለችም የሚል ነበር። እንዲሁም ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ ነው የሚል ነበር።
ይህም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ አምላክ ሆኖ አልተወለደም የሚልን ሀሳብ የሚፈጥር ነው። ጌታችን አምላክነቱ እና ሰውነቱ አንድ ሳይሆኑ የተነጣጠሉ ናቸው የሚል ነው። ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ የሚያሳንስ (እሱ ስላለ ጌታችን የከፈለልን ዋጋ አይቀንስም)፣ እመቤታችን ድንግል ማርያምንም ክብሯን የሚቀንስ ነው (እሱ ስለተናገረ ክብሯ አይቀንስም)።
በዚህም ምክንያት በፈረንጆች አቆጣጠር በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ከተማ ሶስተኛው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ተደረገ። ከ200 በላይ አባቶች ጳጳሳት፣ ከሮም፣ ከእስክንድርያ፣ ከአንጾኪያ ከሁሉም ቦታ የመጡ አባቶች በተኙበት ጉባኤ ንስጥሮስ ተወገዘ። የጵጵስና ማዕረጉም ተሻረ። የሱን አስተምህሮ የሚከተሉ ሁሉም ተወገዙ።
በዚህም ንስጥሮስና ተከታዮቹ ጠፉ። ነገር ግን አስተምህሮው አልጠፋም ነበር። በ451 በተካሄደ ጉባኤ የግሪክና የላቲን ቤተ ክርስቲያናት የሱን አስተምህሮ በተዘዋዋሪ ተቀበሉ። በአፋቸው ንስጥሮስ የተወገዘ ነው ቢሉም ግን የተቀበሉትን በተዘዋዋሪ የንስጥሮስን ሁለት ባህርይ አስተምህሮ ነው። ይህን የተቃወሙትም የኦሪየንታል ቤተክርስቲያናት ከነሱ ተለዩ።
ሌሎችም የንስጥሮስ ተከታዮች ነበሩ። ይህም በምዕራብ ሶርያና ምስራቅ ኢራቅ አከባቢ የምትገኘው የ"ምስራቅ" ቤተክርስቲያን ተከታዮች ነበሩ። ይህ ቤተክርስቲያን ከዛን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬም የቆየ ሲሆን የንስጥሮስን አስተምህሮ በቀጥታ የሚቀበሉ እና ንስጥሮስንም እንደ ቅዱስ የሚቆጥሩ ናቸው።
ታዲያ ይህ ከላይ ያየነው አባት የዚህ ቤተክርስቲያን አባል ነው። ከልደቱም ጀምሮ በዚህች ንስጥሮሳዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበረ ሲሆን በዚያም ዲቁና እና ክህነት ያገኘ ነበር። በኋላ ላይ ግን ከዚያም በመለየት የራሱን ቸርች የከፈተ ሰው ነው።
እንደ ቻናሌ የዚህን ሰው የኋላ ታሪክ ሳልመረምር መልክቱን በመልቀቄ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
@ortodoxtewadochannal
@ortodoxtewadochannal
BY ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መንፈሳዊ አገልግሎት
Share with your friend now:
tgoop.com/ortodoxtewadochannal/4199