tgoop.com/razielethiopia/998
Last Update:
Dn Yordanos Abebe (ገብሩ ለቅዱስ ዳዊት)
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱአምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖
❖ ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
✞ #አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) መደራ ✞
=>አቡነ ገሪማ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሮም ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸው መስፍንያኖስና ሰፍንግያ እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት
ነበሩ:: ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ፡፡
+እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን ይስሐቅ ብለው አሳደጉት:: ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ
ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ:: ለ7 ዓመታት ሕዝቡን በፍትሕ እያስተዳደረ: መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል::
+አንድ ቀን ግን ከግብፅ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው:: ላኪው #አባ_ዸንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ ንግሥና ምን ያደርግልሃል?
ይልቁኑስ በሰማይ ለዘለዓለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና"
የሚል ነበር::
+ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ:: ድንገት
ግን ቅዱስ_ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብፅ አባ ዸንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው::
+እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮዽያ መጡ:: ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው:: ሰውነታቸውን በገድል ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር::
+አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው አባ ዸንጠሌዎን አዘኑ:: ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ
የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ" አሉ:: አባ ይስሐቅ ግን "ሰዎች ብቻ አይደሉም: ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል" ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (800 ሜትር) ተጠራርጎ ሸሸ::
+ይሕንን የተመለከቱት አባ ዸንጠሌዎን
"ወልድየ_ይስሐቅ_ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ) አሏቸው:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮም "#አቡነ_ገሪማ" ተብለው ቀሩ፡፡
+አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም
ግሩም ነህ" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል::
+ጻድቁ ወንጌልን: ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል:-
1• ስንዴ ጠዋት ዘርተውት በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር "በጽባሕ ይዘርዕ: ወበሠርክ የአርር" እንዲል::
2• ጧት የተከሉት ወይን በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር::
3• አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጸበል ሆኖ ዛሬም አለ::
4• ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች::
5• አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን አቁመዋታል::
+ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን
ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው::
"ስምሕን የጠራ: መታሰቢያህን ያደረገ: እስከ 12 ትውልድ እምርልሃለሁ:: አንተ ግን ሞትን አትቀምስም" ብሏቸው ተሰወረ:: ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ #ብሔረ_ሕያዋን አድርሰዋቸዋል፡፡
✞ #አባ_ለትጹን_የዋህ ✞
=>ስመ ጥሩ ጻድቅ አባ ለትጹን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በግብጽ የተወለዱ:
¤በፍጹም ተግሣጽ ያደጉ:
¤ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን በሕገ ወንጌል የመሩ:
¤አንድ ቀን በሰሟት የወንጌል ቃል የመነኑ:
¤ገዳም ገብተው በትሕትና ለዘመናት ያገለገሉ:
¤በመጨረሻም ወደ ትልቅ ተራራ ወጥተው ተጋድሏቸውን የፈጸሙ ታላቅ አባት ናቸው::
+ከየዋሕነታቸው የተነሳ ኃጢአተኛ ሰው ሲያገኙ ራሳቸው ንስሃ ይገቡ ነበር:: አንዴ ግን እናቱን 10 ጊዜ በዝሙት ያረከሰ: ስትጸንስም መርዝ አጠጥቶ ጽንሱን በማሕጸኗ የገደለና በሥጋ ወደሙ ላይ የተዘባበተ ሰው ሊሞት ሲል ደረሱ::
+አጋንንት ሲዖል ታች ሲጥሉትም ተመለከቱ:: ኃጢአቱ ጭንቅ ቢሆንም የእርሱን ንስሃ ሊቀበሉ ጀመሩ: ከንስሃቸው
ጽናት የተነሳ ሞቱ:: ጌታችን ከሞት አስነስቶ "አትለምነኝ: አልምረውም" አላቸው::
+ጻድቁ ተስፋ አልቆረጡምና ቀጠሉ:: ለ2ኛ ጊዜ ሞቱ:: አሁንም ቀጠሉ: 3ኛ: 4ኛ: 5ኛ ጊዜም ሞቱ:: በ6ኛው ግን መፍትሔ መጣ:: ጌታችን አእላፍ መላእክትን አስከትሎ: ያችንም ኃጥእ ነፍስ ይዞ መጣ:: "ፍርዴ አይታጠፍምና
ወደ ገነት አላስገባትም:: ስለ አንተ ጽድቅና የዋሕነት ደግሞ ሲዖል አልጥላትም:: ስለዚሕም እንዳልተፈጠረች ትሁን" ብሎ እፍ
አለባት:: ፈጥና ወደ ትቢያነት ተቀየረች::
+ጻድቁም የፈጣሪያቸውን ቸርነት አድንቀው ሰገዱ:: ከብዙ ዘመናት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐረፉ::
✞ #አባ_ዸላሞን_ፈላሲ ✞
=>ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ገዳማውያን አንዱ አባ ዸላሞን የአባ ለትጹን ወዳጅ ነበር:: ይሕ ቅዱስ
ከአጋንንት ጋር በገጠመው ጦርነት ምክንያት ለየት ይላል:: ከ60 ዓመታት በላይ እንኳን ሳቅና ደስታ ቀና ብሎም ሰው አላየም::
+በነዚሁ ዘመናት ሁሉ ቅንድቡ እስኪላጥ አልቅሷል:: በዓለም ያሉ አጋንንት ሁሉ ተሰብስበው አሰቃይተውታል:: እርሱ ግን
በእግዚአብሔር ቸርነት: በወዳጁ በአባ ለትጹን ጸሎትና በትጋት አሸንፏቸው ዛሬ ዐርፏል::
=>ቸሩ አምላካችን ከታላላቁ ቅዱሳን ጸጋ በረከት ይክፈለን:: በምልጃቸውም ይቅር ይበለን::
=>ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ብጹዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
2.አባ ለትጹን ዐቢይ ወየዋሕ
3.አባ ዸላሞን ፈላሲ
4.ቅድስት አርሴማ ጻድቅት
5.ሰማዕታት እለ አኮራን
6፡ ፯፼ ፹፻ ሰማዕታት ማኅበረ ቅዱስ ተክለሃ ይማኖት
❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት
2፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
3፡ ቅዱሳን መክሲሞስ ወደማቴዎስ
4፡ ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ
+++ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና:: ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@razielethiopia
BY ራዚኤል ዘኢትዮጵያ
Share with your friend now:
tgoop.com/razielethiopia/998