tgoop.com/sewmehonEth/170
Last Update:
🙏ሰላም ለእናንተ ይሁን እንዴት አደራችሁ🙏
የሰው ዋጋው ስንት ነው?
ዛሬ ጠዋታ ወደስራ ሳመራ በአይኔ ያየውትን አሳዛኝ ክስተት ላካፍላችሁ፡፡ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ጠዋትና ማታ ዝናብ መመታት የተለመደ ነው፡፡ ጠዋት እንደወትሮዬ ከትራንስፖርት እንደወረድኩ ወደ መስሪያ ቤቴ የምታደርሰኝን የ5 ደቂቃ የእግር መንገድ በፍጥነት መራመድን ተያይዣለው፡፡
ትንሽ እንደተጓዝኩ ግን ቃሊቲ ውሃ ልማት አልፍ ብሎ ኮርኪ ፋብሪካ ፊት ለፊት ብዙ ትራፊክ ፖሊሶች ብዙ ፖሊሶች በድንጋጤና በወከባ ቆመው ተመለከትኩ፡፡ ብዙ ትራፊኮችን በመመልከቴ እና በቦታው ብዙ የቆሙ ከባድ ተሽከርካሪዎችን በማየቴ ነገሩ ከህገ-ወጥ ጭነት ጋር የተያያዘ ነው ስል አሰብኩ፤ ግን በጣም በትልቁ ተሳስቼ ነበር፡፡
ወደ እነሱ እንደተጠጋውም በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው አስከሬን በአይኔ አየው፤ ለዛውም እንደ እንሰሳ ተቀጥቅጦና ተወግቶ ተገድሎ ደሙ ሙሉ መሬቱን ሸፍኖ፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም በቦታው የነበሩ ፖሊሶችና ትራፊኮች ከውሃ መውረጃ ትቦ ውስጥ አውጥተን ካነበብነው መታወቂያው ላይ አገኘን ባሉት መረጃ ተማሪ ነው አሉ፡፡ መሬት ላይ ከጎኑ ወድቆ የተገኘ የላፕቶፕ ቦርሳም አለ፡፡
ብቻ ይሄ ሰው ወጣትም ይሁን ሽማግሌ፤ ህፃንም ይሁን አዋቂ፤ በጨለማ ተገሎ እንደ እንሰሳ መሬት ላይ ተጥሎ ስጋውን ዝናብ ሲደበድበው አድሯል፡፡
ይህን ሰው በግፍ የገደሉት የሰይጣን ሙሽሮች ምንም የተለየ ምክንያት ይኑራቸውም አይኑራቸውም ክቡር የሆነውን የሰው ነፍስ ያጠፉተ ለምድራዊ ጥቅም ፣ ቁስ ወይም ገንዘብ ሲሉ ነው፡፡
እውነት ግን የሰው ዋጋው ስንት ነው?
✔የሰው ነፍስ በደቂቃ ከሚጠፋ ገንዘብ ታንሳለችን?
✔የሰው ነፍስ ከአንድ ስማርት ፎን ታንሳለችን?
✔ የሰው ነፍስ ወድቆ ከሚሰበር ኮምፒውተር አንሳ ነውን?
ኧረ እንደው ሲጀምር የሰው ልጅ ከምንስ ጋር በምን መለኪያ ይወዳደራል?
✍ውድ ጓደኞቼ ጠባቂ አንድ አምላክ ቢሆንም እራሳችንም የተቻለንን ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ ኪሳችን ውስጥ ያለን 50 ብር ለመውሰድ ሊገለን ጩቤ የሚያወጣ ወሮ በላ ያለበት ዘመን ላይ ደርሰናልና በግዜ ወደየቤታችን እንግባ፡፡ ወንድማዊ ምክሬ ነው፡፡ ፈጣሪ ማስተዋል የሚችል አእምሮን ለሁላችን ይስጠን፤ እንደቀልድ በየሜዳው ደማቸው የሚፈሰውን እህት ወንድሞች ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑር፡፡
🙌መልካም ቀን🙌
Join and share 👉 @sewmehoneth
BY ሰው መሆን 🇪🇹
Share with your friend now:
tgoop.com/sewmehonEth/170