tgoop.com/shamilunkamil/2350
Last Update:
እኚህ ሰው ማን ናቸው?
በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፣ አጀጋሪ በሌለው፣ ከ 6 ቱ አቅጣጫዎችና ከላይ ታቹ ስፍራ ሁሉ በተጥራራው
አሏህ እሳቸውን የሚሳደቡትን ፣ በሳቸው የሚንቋሹሹትን እና የሚያሾፉትን የሚገባቸውን እንደሚሰጣቸው በቁርኣን 15ኛው ምዕራፍ ላይ 95ኛው አንቀፅ ላይ እንዲህ ሲል ተናግሯል
((إِنَّا كَفَيْنَاكَ الْمُسْتَهْزِئِينَ)) سورة الحجر /95
((ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንልሃል፡፡))ሱረቱል ሂጅር15፥95
ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ ወጣትም ሆነ አዛውንት ስለ እሳቸው ሲወራ "ጆሮ ዳባ ልበስ" የሚል የለም። ሁሉ ስለ እሳቸው ሲወራ አዳሜ ሆነ ሔዋኔ ጆሮውን አስግጎ ይሰማል፥ ከሁሉም ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ የሚጠሏቸው ሳይቀር እንኳን ቢሆን ስለ እሳቸው ለመስማት እና ስለ እሳቸው ለማወቅ ይፈልጋሉ። ዝም ብለህ ሰው የተሰበሰበበት መሀል ገብተህ እና ድምጽክን ከፍ አድርገህ፦ "ሰኢድ" ብለህ ወይም ሌላ ስም ብትጣራ ፊቱን እና ትኩረቱን ወደ አንተ የሚያዞረው የጠራከውን ስም ባለቤት ብቻ ነው፥ ከሌለም ደግሞ ማንም ፊት እና ትኩረት የሚሰጥክ አይኖርም። ነገር ግን ሰው የተሰበሰበበት ስፍራ ሄደህ የእሳቸውን ስም ጠርተህ ንግግር ብትጀምር ሁሉም ፊቱን እና ትኩረቱን ወደ አንተ ያደርጋል፥ ትኩረት የማይሰጥህ የለም ቢባል ማጋነን እና ማበል አይሆንም። ስለ እሳቸው ለማወቅ የማይሰለፍ አይኖርም፥ እኚህ ሰው፦
1ኛ. የእልፍ አእላፋት መጻሕፍት ርዕስ በመሆን ብዙ ጸሐፊያን የከተቡላቸው ናቸው፣
2ኛ. በሁሉም ልብ ውስጥ በአሉታዊ ሆነ በአንታዊ በሁለት ወገን እንደተሳለ ሰይፍ ሰርስረው የገቡ ናቸው፣
3ኛ. አስተምህሮታቸው የተሟላ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ የሕይወት ዘይቤ በመሆኑ የዓለማችን ተግዳሮት ነው የተባለላቸው ናቸው፣
4ኛ. "የዓለማችን ቁጥር አንድ አውንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖ አሳዳሪ" ተብለዋል፥ ለሕሩያን አውንታ ተጽዕኖ እንዲሁ ለእኵያን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳዳሪ ናቸው፣
5ኛ. ስለ እርሳቸው ማንነት የገባው ሰው፦ "ሕይወትህን መስዋዕት አርግ" ቢባል ያለ አንዳች ማቅማማት ሕይወቱን እስከ ሞት የሚያደርግላቸው ናቸው።
6ኛ. በታሪክ ውስጥ እሳቸውን ለማነወር፣ ለማበሻቀጥ፣ ለማብጠልጠል ብዙ ጦማሪያን ጦምረዋል፣ ብዙ ኃያሲያን ኃይሰዋል፤ ብዙ ተቺዎች ተችተዋል፣ ብዙ ተሳላቂዎች ተሳልቀዋል። ቅሉ ግን የጦማሪያን ጦማር፣ የኃያሲያን ኂስ፣ የተቺዎች ትችት፣ የተሳላቂዎች ስላቅ ከሟቾች ጋር ሲያልፍ የእሳቸው ስም እና የሰዎችን ሕይወት የቀየሩበት መጽሐፍ እስካሁን አለ የተባለላቸው ናቸው።
እኚህ ሰው ማን ናቸው? አዎ! የዓለማቱ ጌታ የአሏህ መልእክተኛ እና የነቢያት መደምደሚያ ነቢዩ ሙሐመድ"ﷺ" ናቸው።
በእርሳቸው ላይ የወረደው ሐቅ ለሰዎች የሚጠቅም ስለሆነ በምድር 1400 ዓመት ቆይቷል፥ ባጢል ቢሆን ኖሮ በእንጭጩ ኮረፋት ሆኖ ተግበስብሶ ይጠፋ ነበር። ይሄም ቁርኣን ላይ በዚህ መልኩ ተገልጿል፦
((كَذَٰلِكَ يَضْرِبُ اللَّهُ الْحَقَّ وَالْبَاطِلَ ۚ فَأَمَّا الزَّبَدُ فَيَذْهَبُ جُفَاءً ۖ وَأَمَّا مَا يَنفَعُ النَّاسَ فَيَمْكُثُ فِي الْأَرْضِ ۚ كَذَٰلِكَ يَضْرِبُ اللَّهُ الْأَمْثَالَ)) سورة الرعد / 17
((እንደዚሁ አላህ ለእውነት እና ለውሸት ምሳሌን ያደርጋል። ኮረፋቱማ ግብስብስ ኾኖ ይጠፋል፥ ለሰዎች የሚጠቅመውማ በምድር ላይ ይቆያል፡፡ እንደዚሁ አላህ ምሳሌዎችን ይገልፃል፡፡)) ሱረቱ ረዕድ\13፥17
የነቢያችን ﷺ መላ እሳቦት ከሰው ቢሆን ኖሮ በጠፋ ነበር ግን የነቢያችን ﷺ ግልጠተ-መለኮት ከፈጣሪ ስለሆነ ገና በእንጭጭነቱ የመካህ ቁሬይሾች፣ የመዲና በኑ ቁረይዛህ፣ የሮሙ ባዛንታይን በዕውቀት መሞገት ሲያቅታቸው በጉልበት ሊያጠፉት ሞክረው አልተሳካላቸው። ከርሞም ሆነ ዘንድሮም እሳቸው ላይ ለሚሳለቁትን ተሳላቂዎች አሏህ በቅቶላቸዋል፥ በእርሳቸው ላይ የወረደውን የአሏህን ብርሃን በአፎቻቸው ለማጥፋት ቢፈልጉ እና ቢጠሩም አሏህ ብርሃኑን ገላጭ ነው፦
((إِنَّا كَفَيْنَاكَ الْمُسْتَهْزِئِينَ)) سورة الحجر /95
((ተሳላቂዎችን ሁሉ እኛ በቅተንልሃል፡፡))ሱረቱል ሂጅር15፥95
((يُرِيدُونَ لِيُطْفِئُوا نُورَ اللَّهِ بِأَفْوَاهِهِمْ وَاللَّهُ مُتِمُّ نُورِهِ وَلَوْ كَرِهَ الْكَافِرُونَ)) سورة الصف /8
((የአሏህን ብርሃን በአፎቻቸው ሊያጠፉ ይሻሉ፥ ከሓዲዎቹ ቢጠሉም እንኳ አላህ ብርሃኑን ገላጭ ነው፡፡)) ሱረቱ ሶፍ \61፥8
ይህንን ብርሃን ለማጥፋት እፍ ባሉ ቁጥር እያነደዱት መሆኑን ይዘነጋሉ፥ ኢሥላም በፍጥነት መጠነ-ሰፊ የእድገት መርሓ-ግብር እየታየበት ያለው በምዕራባውያን መሆኑ እፍ ባሉ ቁጥር የሚያነዱበት ውጤት ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን! አሚን።
فِدَاكَ أَبِي وَأُمِّي يَا رَسُول اللَّه
“ፊዳከ አቢ ወኡሚ ያ ረሡሉሏህ”
“የአሏህ መልክተኛ ሆይ እናት እና አባቴ ፊዳ ይሁንሎት”
:¨·.·¨: ❀
`·. ሻሚል-shamil
https://www.tgoop.com/shamilunkamil
BY ሻሚል - shamil
Share with your friend now:
tgoop.com/shamilunkamil/2350