tgoop.com/snthufdire/1504
Last Update:
-ከተወዳጀኋት በርካታ ቀን ሆነን ። ስራ ነው ያገናኘን ። መልከ-መልካምነቷ ቢስብም ፤ የግንባሯ መቋጠር አያቀርብም ።ቁጥብ ያለች elegant ነች።
አንድ ቀን መንገድ እየሄድን አንድ ጎረምሳ የአንዲትን ልጅ ቂጥ ቸብ አደረጋት ፤ ልጅቷ ተናደደች ፤ ልጁ ደግሞ አሽካካ ። በሰጨኝ ሰደብኩት ሰደበኝ ፤ ተገለገልን ፤ ቤተሳይዳ ደነገጠች ፤ ለማረጋጋት ሞከረች ፤ ተናደድኩ እንዴት እንደዚህ ይሆናል ።
ሰው ክቡር ነው። ሊያውም ያልደረሰብሽ ፤ ሊያውም የማታውቂው ፤ ሊያውም ሴት ልጅ
አልኩ ።
ንዴቴ ሲተን በግርምት ዝም ብላ ስታየኝ ፤ አየኋት ። በሌላ ቀን ስንገናኝ ከበፊቱ ትንሽ ቀረበችኝ ።
ደሞ በሌላ ቀን ፤ ከፊታችን የሚመጡ የተጎሳቆሉ እናትን ከኋላ ቀረት ብዬ ብር ሰጠኋቸው
ምርቃቴን ፣ በረከቴን ወስጄ ስመለስ ፤ ምን አድርገህላቸው ነው አንዲህ ተጎንብሰው
እጅ የሚነሱህ አለችኝ ።ምንም ብዬ አድበሰበስኩት ።
ፍጥጥ ፤ ፈርጠም ፤ ደረቅ ብላ ጠየቀችኝ ። መለመን አልጀመሩም እንጂ ኑሮ ከብዷቸዋል ፤ ቡና መግዣ ሳንቲም ነገር ሰጠኋቸው ይኸው ነው አልኳት ።
ሳይለምኑህ አለችኝ ?
አይናችንን ስንከፍት ፤ ከቃል በላይ ገፅታ ሁሉንም ይናገራል አልኳት ። ቃል አልተናገረችም ።
በሌላ ቀን ስንገናኝ ።
እጮኛ አለሽ አልኳት?? የለኝም ወንድ አላምንም አለችኝ !
በእርጋታ ለምን አልኳት ?
እ ዝም አለች
ዝም ብዬ ሳያት ቀጠለች
አባቴ ሃይለኛ ነው ። እናቴ ስታናደው በር ዘግቶ በቀበቶ ነበር የሚገርፋት ። እንፈራዋለን ። ይጮህብናል ። ዝም የሚል ነበር ፤ ሲስቅ እንኳን አይቼው አላውቅም ። እናቴ በጣም ታሳዝነኝ ነበር ። እኔን እንኳን እንደሚወደኝ ለማሳየት ቃል ሳያወጣ ፀጉሬን ነበር የሚያሻሸው ፤ በቃ እቺ የፍቅሩ ማሳያ አፅናፍ ነበረች።
ከቁጣ በስተቀር ገርፎኝ አያውቅም ግን እናቴ ሳበሳጫት ለአባትሽ ነው የምነገርው ስትለኝ ፤ ሽንቴ እንሲኪያመልጠኝ ነበር የምደነግጠው ፤ ብርገጋዬን ስለምታውቅ በቀላሉ በአባቴ አታስፈራራኝም ።
አንድ ቀን ለስራ ክፍለ-ሀገር በሄደ በአራተኛ ቀን መኪና ተገልብጦ የአባቴ በድን በሳጥን ተጀቡኖ መጣ ። ሃዘን ሆነ ። እናቴ በጣም ስታዝን ገረመኝ ፤ ይመታት ፤ ይቆጣት ፤ ትፈራው አልነበር እንዴ ለምንድን ነው እንዲህ የምታዝነው አልኩ ።
ጊዜ ሄደ ። እናቴ ኑሮ በጣም ከበዳት ። አበራ የሚባል ፤ ሴት ወሲብ ብቻ የምትመስለው ሸፋዳ አገባች ።
ኑሮ ቀለል አለን ፤ አበራ ቸር ነው ገንዘብ አይሰስትም ።ነገር ግን ባዳው መሆኔን እይታው ይነግረኛል ። እናቴ ከሌለች ይጎነትለኛል ፤ ይተሻሸኛል ፤ ወደ ራሱ ይስበኛል
እናቴ ተሳቀቀች ። እኔም ቤታችን እናቴ ከሌለች
ያለመደኝ ተናካሽ ውሻ ያለበት ግቢ ነው የሚመስለኝ ። ከአቅሜ በላይ ሲሆን ፤ የጭቅጭቃቸው ምክንያት ስሆን ፤ ትምህርቴን አቋርጬ ፤ መስተንግዶ ገባሁ ፤ ጥንጥ ቤትም ብቻዬን ተከራየሁ ።
ለካ ሁሉም አበራ ነው። ትንሽ ያወራኸው ፤ ፈገግ ያልክለት ወንድ ሁላ እራት ልጋብዝሽ ፤ ሌላ ቦታ እንገናኝ ፤ እንቀምቅም ፤ ልሳምሽ ፤ እንዋሰብ እንመቻች ፤ ወሬያቸው ቢቋጭ ፣ ቢገመድ ፣ ቢሰፋ ከዚህ አይዘልም ።
የወንዶች መስገብገብ ነው ወሲብን ወንድ ብቻውን የተለየ ደስታ የሚያገኝበት ያስመሰለው። ፍትወታችንን ያፈዘዘልን መንቀዥቀዣቹ ነው ።
ከከስተመሮቼ ቃለዓብ ደስ ይላል ። ረጋ ያለ ። ትንሽ ፈገግታ ፤ ከትንሽ ቲፕ ጋ የሚሰጥ ነው። በጣም ከብዙ ጊዜ በኋላ ተግባባን ።መደዋወል መገናኘት አበዛን ። በአባቴ ፍርሃት እና በአበራ ሴሰኝነት ፤በከስተመሮቼ ሴት አውልነት ተፅዕኖ የተበጃጀሁት ቤተሳይዳ በቃለዓብ ምክንያት አንድ አንድ ወንድ አለ ማለት ጀመርኩ ።
ትንሿ ቤቴ ይመጣል ። ተስፋ ፤ ገንዘብ ፤ክብር ፍቅር ፤ ትርጉም ሰጠኝ።
ወደድኩት ።ያቺ የወንድ ገላ የሚሸክካት ቤተሳይዳ
ገላዬ ከገላው ሲነካካ ፤ ሰውነቴ ይለዋወጣል ይቅበዘበዛል ፤ ይከፋፈታል ። እቅፍቅፍ አደርገዋለሁ ፤ ጉያው ውስጥ እገባለሁ ፤ አንገቴን ሲስመኝ ደስታ መላ አካሌ ላይ ሲርመሰመስ ይሰማኛል። ስንራከብ እና ውስጤ ሲጨርስ ሃሴት ሲያጥለቀልቀኝ ከፀጉሬ እስከ ጥፍሬ እርካታ ይመዘምዘኛል ።
ቃለአብን ወደድኩት ። እንደዚህ ከሆን አምስት ወር ከሰባት ቀን በኋላ ።
ቃለአብ ድንገት ጠፋብኝ ፤ ፈለኩት የለም።
በህልሜ አየሁት ፤ ቃዠው ለፈለፍኩ ፤ በአይነ ስጋ ዳግም ማግኘት ግን አልተቻለኝም ።
እጦት ፤ ናፍቆት ፤ ፍቅር ፤ ስጋት ተባብረው ከደቆሱኝ ከትንሽ እለት በኋላ አንድ ጓደኛው ሚስቱ እና ልጁ ጋ አሜሪካ መሄዱን በማያጠራጥር መልኩ ነገረኝ ።
ማርያም ደጅ ሄድኩኝ እና ለምን አልኳት ፤ እንዴት አንቺ እያለሽልኝ ከክፉ ነገር አልጋረድሺኝም ። እንዴት አላጋለጥሺውም ፤ ነገሩ እንደሆነብኝ ቢሆንበት ፤ የዘራውን ቢያጭድ ፤ እሱ ይጎዳል እንጂ እኔ ስብራቴ አይድን!!
ምነው ማርያም? ምነው? ምነው ብርሃኔ ? ከስንት አፈ ጮሌ ፤ ከሰንት መደለያ ቁስ አስመልጠሺኝ ፤ ምነው ዛሬ ተውሺኝ ምነው ማርያሜ ?!
እንዴት አንቺ እያለሽ ያመንኩት ፤ ራሴን የሰጠሁት ሲያጠፋኝ ዝም አልሺኝ እያልኩ አነባው ፤ አዘንኩ ተደበትኩ ። አሁን ጠባሳው ልቤ ውስጥ ተሰንዷል"
አለችኝ
-በገጠመኝ ባየሁት ፤ በሆነብኝ ምክንያት ወንድ አላምንም አለችኝ ። ብዙ ባገኘኋት ቁጥር ፤
የልቧን እውነት ባጫወተቺኝ ብዛት ፤ ከአባቷ ፣ ከእንጀራ አባቷ ፣ ከቦይፍሬንዷ በኋላ ፤ ዛሬም ፊት ለፊት የልቧን የሚሰማትን ልጅ ለማመን ዋዜማ ላይ ነች ። አንዳንድ ወንድ አለ ልትል ነው።
ማስታወሻ፦
ሰው መሆን እንዲህ ነው።
@snthufdire
BY ስነ-ፅሁፍ 'በቤተሰብ'
Share with your friend now:
tgoop.com/snthufdire/1504