tgoop.com/sratebetkrstyane/9638
Last Update:
ኅዳር ጽዮን
"ጽዮን" ማለት "ጸወን አምባ፣ መጠጊያ" ማለት ነው:: ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል፡፡
ኅዳር ፳፩ ቀን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታቦተ ጽዮንን ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦቱ አድርጎ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ያላትን ድርሻ በስፋት ታስተምራለች፡፡
ነቢዩ ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጸልዮና ጹሞ ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈበትን ጽላት ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ታቦት ‹ታቦተ ጽዮንን› እንደተቀበለ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡
ታቦተ ጽዮን ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸችበት ምክንያት የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ንጽሕና ለማመልከት ነው፡፡ በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ የተለበጠች መሆኗ ደግሞ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል የመሆኗ ምሳሌ ነው፡፡
ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ወቅት በታቦቷ ፊት በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ ለእግዚአብሔር በዝማሬ ምስጋና አቅርቧል፡፡ ‹‹ለንጉሥ ዳዊትም “እግዚአብሔር የአቢዳራ ቤት የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ባረከ” ብለው ነገሩት፡፡
ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ራሱ ከተማ በደስታ አመጣት፡፡ ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ሰባት መሰንቆ የሚመቱ መዘምራን ነበሩ፤ በሬዎችንና በጎችን ይሠዉ ነበር፡፡ ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት በገና ይደረድር ነበር›› እንዲል፤ ነቢዩ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት የተቀኘው ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናችን ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያመስገን ነው፡፡ (፪ሳሙ.፮፥፲፪-፲፬)
ታቦተ ጽዮን እስራኤል የዮርዳኖስን ባሕር ለመሻገር በተቸገሩ ጊዜ ነቢዩ ኢያሱ እግዚአብሔር አምላክ በነገረው መሠረት ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው በሕዝቡ ፊት ወደ ዮርዳኖስ እንዲሄዱ ነገራቸው፤ እነርሱም እንደታዘዙት አደረጉ፤ ታቦቱን የተሸከሙት የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ፤ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በዮርዳኖስ መካከል በደረቅ መሬት ጸንተው ቆመው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ እስራኤል ሁሉ በደረቅ መሬት ተሻገሩ፡፡ (ኢያ. ፫፥፩-፲፯)
እስራኤላውያን በመካከላቸው የቃል ኪዳኑ ታቦት በያዙ ቁጥር በጦርነታቸው ሁል ጊዜ ያሸንፉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤል ስለበደሉት እንዲሁም የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በደላቸውና ክፋታቸው ስለበዛ ታቦተ ጽዮን ተማርካ ወደ ፍልስጥኤም ሄደች፡፡ በዚያ በአሕዛብ ምድርም ልዩ ልዩ ተአምራትን እያደረገች ፍልስጥኤማውያንን ስለአስጨነቀቻቸው የፍልስጥኤማውያን አለቆች የቃልኪዳኑን ታቦት ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶችን አስይዘው ወደመጣችበት በሠረገላ አድርገው በክብር ሸኝተዋታል፡፡ (፩ኛ.ሳሙ. ፭፥፩-፲፭)
ሀገራችን ኢትዮጵያም በንግሥተ ሳባ አማካኝነት ለታቦተ ጽዮን መቀመጫ እንድትሆን የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኗል፡፡ ይህም እንዲህ ነበር፤ ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ጥበብ ለማድነቅ ምድረ እስራኤል ድረስ መጓዟን ተከትሎ ከንጉሡ ቀዳማዊ ምኒልክን ፀነሰች፡፡
ቀዳማዊ ምኒልክ ከአደገ በኋላ አባቱን ሊጠይቅ ሂዶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ አብረውት አንድ ሺህ ሁለት መቶ እስራኤላውያን የበኩር ልጆች፣ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት በአዛርያስ የሚመሩ ሌዋውያን ካህናትም አብረውት ለጉዞ ተነሡ፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትንና ሌሎች በርካታ ቁሳቁሶችን ይዘውም ነበር።
ነገር ግን ታቦተ ጽዮንን አዛርያስና ካህናቱ ተማክረው ቀዳማዊ ምኒልክ እንኳን ሳይሰማ በምሥጢር ይዘዋት ሊመጡ ተስማሙ፡፡ ዕቅዳቸውን ለማሳካት በታቦተ ጽዮን አምሳያ ሌላ ታቦት አዘጋጅተው ለመሄድ በሚነሡበት ዕለት ሌሊትም ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት ሄዱ፡፡
ከቤተ መቅደስ ሲደርሱም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበርና የቤተ መቅደሱ በር ተከፍቶ እና ውስጡም በብርሃን ተሞልቶ ታቦተ ጽዮንም ከመንበሯ በመነሣት ከፍ ብላ አገኟት። በዚህም የአምላክን ፈቃድ ተረድተውና እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በፍጥነት ይዘዋት ወጡ፡፡ በአምሳያዋ የሠሩትንም ቅርፅ በመንበሩ ላይ አስቀምጠው ሄዱ።
የንጉሡ ወታደሮች በፍጥነት ቢጓዙም ቀዳማዊ ምኒልክ እና አዛርያስ ታቦተ ጽዮንን ይዘው ሲጓዙ እጅግ ፍጣን ስለበር ሊደርሱባቸው አልቻሉም። መጽሐፈ ክብረ ነገሥት ይህንን ሲጠቅስ ‹‹ከመሬት አንድ ክንድ ያህል ከፍ ብለው ይሄዱ ነበር›› በማለት ይገልጸዋል። ባሕረ ኤርትራን ከተሻገሩና ግብፅ ከደረሱ በኋላ ዕረፍትን ባደረጉ ጊዜ አዛርያስ ለቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ይዘዋት እንደመጡ ነገረው፡፡
አያይዞም ‹‹አንተም ብትሻ ታቦቷንም ወደ ሀገሯ ልመልሳት ብትል አትችልም፤ አባትህ ሰሎሞንም ሊወስዳት ቢመጣ አይሆንለትም›› አለው። ከቦታ ቦታ ይዣት እንቀሳቀሳለው ቢልም ያለ ፈቃዷ ምንም እንደማያደርግና ሁሉ ነገር በአምላክ መልካም ፈቃድ እንደሚፈጸም ነገረው። ቀዳማዊው ምኒልክም ይህን ሲሰማ ተደሰተ፤ ሕዝቡና ሠራዊቱ በሙሉ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ከግብፅ ምድር ወጥተው እስከ ኢትዮጵያ በታላቅ እልልታና ሆታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ።
ኅዳር ፳፩ ቀን አክሱም በደረሱ ጊዜም እናቱ ንግሥተ ሳባ ተቀበለችው፤ ደስታና እልልታውን ተመልክታ ያገኙት ነገር እንዳለ ብትጠይቀው ታቦተ ጽዮንን እንዳመጧት ነገራት፡፡ የእርሷም ደስታ እጥፍ ድርብ ሆነ። ታቦቷንም በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስቀመጡአት፡፡
ከዚያም ዘመን ጀምሮ በየዓመቱ ኅዳር ፳፩ ቀን ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙ ታላላቅ ተአምራትን በማሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታከብራለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
ምንጭ፤
ክብረ ነገሥት ተርጓሚ ሥርግው ገላው (1994 ዓ.ም)
መዝገበ ታሪክ ቊጥር 1 (መምህር ኅሩይ ኤርምያስ)
BY ✝️ስርዓተ ቤተክርስቲያን መመሪያ ✝️
Share with your friend now:
tgoop.com/sratebetkrstyane/9638