Telegram Web
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
የሰብስክራይበር ቁጥር እስኪሞላ እናሟሚቃለን

https://youtube.com/@tesfaab_teshome_offical?si=Xyt0J6tsqJM6LNN4
"ብርቱካን አልታገተችም። አልተደፈረችም። ሁሉም ነገር ሀሰተኛ ድራማ ነው" የሚለውን ዶክመንተሪ ሳናላሞጥ ብንውጥ እንኳን መሰረታዊው እውነት አይቀየርም።

መሰረታዊው እውነት ፥ ዜጎች ይታገታሉ ፣ ሴቶች ይደፈራሉ ፣ ንፁሃን ይጠቃሉ። ለዚህ ሁሉ በደል ፍትህ አይሰጥም!

ብርቱካን የውሸት ድራማ ሰርታ ቢሆን እንኳን ሀገራችን ያለችበትን የወንጀል አረንቋ አይሸሽግም!


@Tfanos
"ቡ ዳ" የሚባል ነገር አለ ወይ? እውነት ለመናገር አለ ብዬ ለማመን እቸገራለሁ። መኖሩን የሚያምኑ ሰዎችን ግን መቃወም አልፈልግም።

ይልቅ ምን ይገርመኛል?

አማኝ ሰዎች ፈሪ ሲሆኑ ይገርመኛል። በእግዚአብሔር የሚያምኑ ፥ እግዚአብሔር ይጠብቀኛል የሚሉ ለሰይጣን ያላቸው የተጋነነ ፍርሃት ይገርመኛል።

እንደው ሰው ሆነ ብሎ ራሱን ለአደጋ እንዲያጋልጥ አይመከርም። አማኝ ስለሆነ ብቻ ያለ ማስተዋል ይኑር አይባልም። ነገር ግን ከቁጥጥሩ ውጭ በሆነ ሁኔታ እግዚአብሔር አይጠብቀውም?

ልጆች ሆነን ደጅ ላይ የተደፋ ውሃ እንድንፈራ ይነገረን ነበር። "ድግምት ይሆናል" ይሉናል። ሳስበው ይገርመኛል።

ቡ ዳ ፥ ድግምት ፥ መተት... ወዘተን የመሳሰለ ነገር አለ ብላችሁ የምታምኑ ነገሩን እንድትዳፈሩ አልጠብቅም። ግን ደግሞ የምታምኑት አምላክ ከእንዲህ ያለ ነገር እንደሚጠብቃችሁ አትርሱ።

ፎቶ ስትለጥፉ ፥ የተደፋ ውሃ ስትረግጡ... ወዘተ ለቡዳ አልያም ለአንዳች አይነት ድግምት እንደምትጋለጡ የምታምኑ ሰዎች የአምላክ ጥበቃ ላይ ጥርጣሬ ያላችሁ ይመስላል።

ከአምላክ ጥበቃ በላይ የሰይጣን ጥቃት የሚያሳስበው ሰው ከልቡ አማኝ አይመስለኝም!


@Tfanos
የምር ሰይጣን ያስፈራል?
* * *

ኤቲስት ነህ? እንግዲያውስ አንተ ሰይጣንን አትፈራውም። ምክኒያቱም ሰይጣን የለምና።

አማኝ ነህ? እንግዲያውስ አንተ ሰይጣንን አትፈራውም። ምክኒያቱም የአምላክህ ጥበቃ ከሰይጣን ማጥቃት ይበልጣልና።

ፈሪ ከሆንክ ግን....

አንድ ሰው በእግዚአብሔር ህልውና ካመነ ፥ እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ካለ በኋላ ሰይጣን ዋና አጀንዳው የሚሆነው እንዴት ነው? በእግዚአብሔር እያመኑ ለሰይጣን መንቀጥቀጥ የእግዚአብሔርን አቅም መጠርጠር ነው። ቅጥ ያጣ ሰይጣናዊ ፍርሃት መለኮታዊ ጥበቃ ላይ እርግጠኝነት ማጣት ነው።

አንድ ሰው ኤቲስት ከሆነም ሰይጣንን መፍራት የለበትም። ኢ አማኒ የሆነ ሰው የሰይጣን ህልውና ላይ እምነት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ የሌለ ነገር አያስፈራውም።
አማኝ ለሆነው ደግሞ አምላኩ ስለሚጠብቀው ስጋት ሊሰማው አይገባም።

ብዙ ሰው መተት ፥ ድግምት ፥ ሟርት ፥ እርግማን ወዘተ ያስጨንቀዋል። መደበኛ ህይወቱን ለመምራት እስኪቸገር ድረስ እንዲህ ባሉ ሃሳቦች ይመሰጣል። ዙሪያውን የሚፈራ ደንጋጣ ይሆናል።

እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች የሰይጣን ናቸው። አማኝ ደግሞ ለሰይጣን ካለው ፍርሃት ይልቅ ለአምላኩ ያለው እምነት መላቅ አለበት።

አንድ ሰው ክርስቲያን ነኝ ካለ በሌላ ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ እያለ ነው። እንግዲህ ክርስቲያን ነኝ ለሚል ሰው መቅረብ ያለበት ጥያቄ "በእውነት የኢየሱስ ተከታይ ነህ ወይ?" የሚል መሆን አለበት።

ኢየሱስን የሚከተል ሰው የህይወቱ ማዕከል ኢየሱስ ነው። ኢየሱስን የህይወቱ ምሶሶ ያደረገ ሰው ቡዳ አያስጨኝቀውም ፥ መተት አያሳስበውም ፥ ድግምት አያሰጋውም። ሰይጣንን አይፈራም።

ሰይጣን ያለው አቅም ከእናንተ አቅም ሊበልጥ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ጥያቄው የሰይጣን የማጥቃት አቅም ከአምላካችሁ ጥበቃ ይበልጣል ወይ? መልሱን ለእናንተ።

ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ስለ ድግምት የሚጨነቀው እንዴት ነው? የቡዳ ነገር የሚያሳስበው ለምንድነው?

ዲያቢሎስ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ቢዞር እንኳን ጌታችሁ እንደሚጠብቃችሁ አታውቁም?

የምር አማኝ ናችሁ? አማኝ ከሆናችሁ የሰይጣን ነገር ብዙ አያስጨንቃችሁ።
እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ ከሰይጣን ይልቅ ሀጢያትን ይፈራል። ምክኒያቱም ሀጢያት የገዛ ፈቃድን ይፈልጋልና!

እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ 666 ወይም ኢሉሚናቲ እያለ አይሳቀቅም። የአለም መጨረሻ በቀረበ ቁጥር የሚሳቀቅ እርሱ ክርስቲያን አይደለም። ክርስቲያን አለም ብትጠቀለል "ጌታዬ ዳግመኛ ሊመጣ ነው" ብሎ ሀሴት ያደርጋል። አለም መጨረሻዋ ሲቀርብ "ማራናታ" ይላል እንጂ 'ኢሉሚናቲዎች... ገለመሌ አይልም።

አሰላለፋችሁን ለዩ። ሰይጣን የሚያስበረግጋችሁ እምነታችሁን መርምሩ

በእርግጥ ልንክደው የማንችለው አሳዛኝ እውነት አለ። አንዳንድ ሰዎች አማኝ የሆኑት ከእግዚአብሔር ሉአላዊነት በላይ የሰይጣን ነገር አስፈርቷቸው ይመስላል።

Nb ሃሳቤን ለማብራራት ከእስልምና ማጣቀስ ያልፈለግኹት ስለ እስልምና በቂ ግንዛቤ ስለሌለኝ ነው። በማላውቀው ጉዳይ ማብራራት አሪፍ አልመሰለኝም።

ሙስሊሞች መልካም በዓል

Via ተስፋኣብ ተሾመ


@Tfanos
አብይ ዛሬ ሰባት አመት ሞልቶታል። ምናልባት ከዚህ በኋላ ሌላ ሰባት አመት በመንበር ይቆይ ይሆናል።

በዘመነ አብይ ድህነት ተባብሷል ፥ ሰላም ቅንጦት ሆኗል ፥ ጦርነት መደበኛ ህይወታችን መስሏል ፥ ስራ ጠፍቷል ፥ ኑሮ ተወዷል.... ወዘተ

ይህ ሁሉ ቢሆንም አብይ ከዚህ በኋላ በስልጣን ይቆያል።

በየአቅጣጫው የአብይ ተቃዋሚዎች በዝተዋል። ታክሲ ውስጥ ድንገት መንግስትን የሚያብጠለጥል ሰው መስማት የተለመደ ነው። በኦሮሚያ የኦሮሞ ነፃነት ጦር ከመንግሥት ጋር እየተፋለመ ነው። ፋኖ ከአገዛዙ ጋር እየተዋጋ ነው። ህወሃት ከፌደራል መንግስት ጋር ሲዋጋ መክረሙ ይታወቃል።

አንዳንዱ በሀይል ፥ አንዳንዱ በሰላማዊ መንገድ መንግስትን እየተፋለመ ነው።

ቢሆንም አብይ በስልጣን ይቀጥላል።

አብይ ሎተሪ ደርሶት በስካር ገንዘቡን ያጠፋ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። የድጋፍ መሰረቱን ንዷል ፥ ደጋፊዎቹን በትኗል። ቢሆንም በስልጣን ይቀጥላል።

"አንድ ሀሙስ የቀረው መንግስት" የሚል ፕሮፖጋንዳ ለጆሮ ደስ ቢልም አውነቱን አይቀይርም።

ደርግ በተቃውሞ መሃል 17 አመት ቆይቷል። ኢህአዴግ እያብጠለጠሉት 27 አመት ገዝቷል። አብይ እየሰደቡት ሰባት አመት ሞልቶታል።

ስድብ ፥ ማብጠልጠል የሚቀይረው ነገር የለም።

ህዝብ መተባበር ካልቻለ ፥ የጋራ አጀንዳ ካልቀረፀ ፥ አብሮ ካልተሰለፈ አንባገነን አገዛዝን አያሸንፍም።

የአብይ ተቃዋሚዎች እልፍ ናቸው። ነገር ግን መተባበር አይፈልጉም። አንባገነኖች ዋነኛ ሀይላቸው የማይተባበር ህዝብ ነው።

መተባበር እስኪኖር ድረስ አብይ በመንበሩ ይቆያል። ምናልባት ሌላ ሰባት ፥ አስር ፥ አስራ አምስት አመት....


@Tfanos
አንድ ሰው ስንት ነው?
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

አንዳንዶች "ጠቅላይ ሚኒስተሩ አንድ ግለሰብ ነው። እሱ ላይ ትችት ማብዛት ለውጥ አያመጣም። አንድ ሰው ቢቀየር የሚለወጥ ነገር የለም" ይላሉ።

በእርግጥ ጠቅላዩ አንድ ሰው ብቻ ነው? በፍፁም አይደለም። በግለሰብ ደረጃ አንድ ግለሰብ ነው። በስልጣን ደረጃ ግን ብዙ ነው።
ዝርዝር ጉዳዮችን ትተን የሐገሪቱን ሕገመንግሥት እናጣቅስ።

የጠቅላይ ሚኒስተሩን ስልጣን እና ሃላፊነት የሚዘረዝረው የሕገመንግስት ክፍል አንቀፅ 74 ነው። የኢፌድሪን ሕገመንግሥት ያነበበ ሰው በቀላሉ እንደሚገነዘበው ጠቅላይ ሚኒስተር የሚሆን ሰው የተከማቸ ስልጣን ይኖረዋል። የተከማቸ ስልጣን እና ከፍተኛ ሃላፊነት ከፍ ያለ ተጠያቂነትን ቢወልድ አግባብ ነው!

ሕገመንግስታችን በአንቀጽ 74 ንዑስ አንቀፅ 1 እንደሚናገረው ከሆነ ጠሚው ጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው። ይህን በልባችን አኑረን ሌሎች አንቀፆችን እንመልከት።

የሚኒስተሮች ምክር ቤት አባላትን በእጩነት አቅርቦ እንዲያስመርጥ ስልጣን አለው። ደግሞም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ፥ የሚኒስተሮች ምክር ቤት መሪ፥ የሚኒስተሮች አስተባባሪ እና ወካይ ነው።

አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 የውጭ ፖሊሲን ጠቅላይ ሚኒስተሩ በበላይነት እንደሚያስፈፅም ስልጣን ይሰጠዋል። ይህ ማለት የሐገሪቱ ቀዳሚ ዲፕሎማት እንደማለት ጭምር ነው።

ዋና ኦዲተር ፥ ኮምሽነሮች ፥ የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንትን መርጦ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያፀድቃል። (ንዑስ አንቀፅ 7)

በንዑስ አንቀፅ ሁለት እና ንዑስ አንቀፅ ሰባት ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሲቪል ሹመቶችን የመስጠት ስልጣን አለው። (ንዑስ አንቀፅ ዘጠኝ)

ከለይ የተጠቀሱ ነጥቦች ምን ይነግሩናል?

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስተሩ አንድ ግለሰብ ነው። ነገር ግን ሚኒስተሮችን የሚሾም ፥ ጦሩን የሚያዝ ፥ ከፍተኛ ሹመቶችን የሚሰጥ ፥ የውጭ ፖሊሲ ዋነኛ አስፈፃሚ ፥ሚኒስተሮችን የሚሰበስብ ደግሞም የሚወክል ፥ ከዋና ኦዲተር እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሚሾም ግለሰብ ነው። ይህን ሁሉ እንዲያደርግ ሕግ ይፈቅድለታል።

እውነት ነው፥ ጠሚው አንድ ሰው ብቻ ነው። ነገር ግን በሕገመንግስቱ መሰረት ከብዙ ሰዎች የላቀ ስልጣን እና ሃላፊነት ያለበት ግለሰብ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስተርነት መንበር በሚሊየኖች ሕይወት እና በቢሊዮን ገንዘቦች የሚወስንበት ቦታ ነው።

"እሱ ምን ያድርግ?" የሚል የየዋህ ጥያቄ ላላቸው ሰዎች ሕገመንግስት መልስ አለው። አድራጊ ፈጣሪዎችን እንዲሾም እና እንዲያዝ ስልጣን የተሰጠው ግለሰብ ምን ያድርግ አይባልም።

ምናልባት "ሕገመንግስቱ በስርኣቱ አልተከበረም" የሚል ክርክር መግጠም ለሚወድ ሰው ሕገመንግሥት መልስ ይሰጣል።
በአንቀፅ 74 ንዑስ አንቀጽ 13 መሰረት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ሕገመንግሥት የማክበር እና የማስከበር ሃላፊነት አለበት። ስለዚህ መሰረታዊ የሕገመንግስት ጥሰት ቢፈፀም በንዑስ አንቀፅ 13 የተሰጠውን ሃላፊነት ጠቅላዩ አልተወጣም ማለት ነው።

በእርግጥ ጠሚው አንድ ሰው ነው። ነገር ግን የተከማቸ ስልጣን እና ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለበት ግለሰብ ነው። ትልቅ ሃላፊነት ትልልቅ ተጠያቂነት ቢያስከትል ተፈጥሯዊ ስለሆነ "እሱ ምን ያድርግ?" የሚለውን አይረቤ ሙግት ማቆም ያስፈልጋል!


@Tfanos
@Tfanos
ደርዘን ጥያቄዎች የመጀመሪያ ክፍል ዛሬ ተለቋል።

እንግዳዬ ቤተማሪያም ተሾመ ነው።

ታቦተ ፅዮን በኢትዮጵያ ነውን?
የሰለሞን ቤተመቅደስ ቀጣዩ የጦርነት ሰበብ ቢሆንስ?
ደራሲያንና ሽልማት
ትዳርና ወጣትነት
የመሳሰሉ አጀንዳዎችን አውርተናል።

ግቡና ተመልከቱ። አስተያየት አስፍሩ። ሁሉንም አስተያየት እናነባለን።

ቢቻላችሁ ዩቲዩብ ቻናሌ ስር አስተያየት ፃፉ። ማየት ባይመቻችሁ እንኳ አስተዋውቁ።

በቀጣይ ስራዎች ውስንነቶችን እያስተካከልን ጥሩ ነገሮችን እያሳደግን እንቀጥላለን

https://youtu.be/yT_YeT24Z-4
"በግል ልንገርህ ብዬ ነው ፥ ዩቲዩብህ ላይ እንዲህ አይነት ጉድለት አለ። በቀጣይ አስተካክለው"

"በኮመንት መስጫ አስተያየት ከምሰጥ በውስጥ ብፅፍልህ ይሻላል፥ በቀጣይ እንዲህና እንዲያ ያለ ነገር ጨምርበት"

ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች በውስጥ የፃፉልኝ ነው። አንዳንዶቹ በአደባባይ ማበረታቻ በግል ደግሞ ማስተካከያ ነግረውኛል።

በውነቱ ደስ ትላላችሁ።

በግል ማስተካከያ ለነገራችሁኝ ሁሉ በአደባባይ ምስጋናዬ አቀርባለሁ
ቢላል ለምን ሞተ?
* * *

ስምንት ቀን ስንት አመት ነው? ሃዘን ያጠላበት አንድ ቀን በስንት አመት ይመነዘራል? ፍስሃ ከተቀላቀለው ግማሽ ዘላለም እና ሃዘን ከደቆሰው አንድ ሳምንት ረዥሙ የቱ ነው?
ሰቆቃ ቀንን ዘልዛላ ያደርጋል፤ ህይወት ምሬት ሲጫናት የሰኣት አጋማሽ ከአእላፍ ቀናት ይልቅ ይረዝማል።

አይሻ ከሳምንት በፊት ወጣት ነበረች። ሃዘን ሲደቁሳት በቀናት እድሜ አሮጊት መሰለች። ቀይ መልኳ ጠቆረ፥ ፊቷ በማዲያት ተወረረ፥ ሃዘን አጎሳቆላት፥ መጎሳቆሏ አጎበጣት፥ ከናፍሮቿ ተሰነጣጠቁ፥ በረዶ መሳይ ጥርሶቿ ዝገት ያገኛቸው መሰሉ።
ከስምንት ቀናት በፊት ከነ አይሻ ቤት አቅጣጫ በተሰማ ከባድ ጩኸት ሰፈሩ ተናወጠ። ተሯሩጠን ቤታቸው ስንደርስ አይሻ በድንጋጤ በድን ሆና ቆማለች። ልጇ ዲና ቀሚሷን ጨምድዳ ይዛ በሃይል ታለቅሳለች።

"ምንድነው የተፈጠረው?" ግራ ገባኝ
"ቢላል... ቢላል... ቢ ላ ል" ያቤፅ ተንተባተበ
"ቢላል ምን ሆነ?"
"ቢ... ላል...." ትንፋሽ አጠረው
"ቢላል ምን ሆነ?" ትዕግሥት አጣኹ
"ቢላል...... ራሱን አጠፋ"
"ኢናሊላሂ..."

ዲና በሃይል ጮኸች።

ዲና፥ መልከመልካሟ፥ ትንሿ አበባ፥ ፍልቅልቋ ኮከብ ከፍ ባለ ድምፅ አለቀሰች።
ይህ ከሆነ ሳምንት አለፈው።

ወዳጃችን ቢላል፥ ታታሪው ሰራተኛ፥ የአባትነት ተምሳሌቱ፥ እውነተኛው አፍቃሪ፥ ከልግስና የማይጎድለው፥ ለዲኑ የሚታመነው..... ወንድማችን ቢላል ላይመለስ አንቀላፋ፥ከራሱ ተጣላ፥ በገዛ እጁ ራሱን አጠፋ።

ከአንድ አሏህ በቀር ማንም ቢሆን በሰው ነብስ ላይ የመወሰን ስልጣን እንደሌለው ቢያውቅም ከመርህ አፈነገጠ። ከሚታመንለት እውነት ጋር ተላለፈ።

"ስራ ጠፍቷል። ቤተሰብ ለማስተዳደር እየተቸገረ ነበር" ያቤፅ ከቀብሩ ማግስት ሃዘን በሰበረው መንፈስ ሆኖ አናገረኝ።
"መተጋገዝ እንችል ነበር፥ ራሱ ላይ መፍረድ አልነበረበትም"
"የሰውን እጅ ማየት ያታክታል። እንደቢላል አይነት ኩሩ እና ታታሪ ሰው ራሱን ለጥገኝነት አሳልፎ መስጠት አይሆንለትም። እርሱ መለገስን እንጂ የሰውን እጅ ማየትን አያውቅበትም፥ ከጎዶሎው ላይ ቀንሶ ለሌሎች ቸርነትን ያደርጋል እንጂ ለጎደለው ነገር የሰው እጅ አያይም"
"ቢሆንም ..." ሃሳቤን በእንጥልጥል ተውኩት
ሳምንት አለፈ። ወጣቷ አይሻ አረጀች፥ ፅጌሬዳዋ ጠወለገች፥ ሃዘን አጎሳቆላት፥ ውበቷ ከሸፈ፥ በሳምንት እድሜ ከወጣትነት ወደ እርጅና ተሸጋገረች።

* * *
"ይኼ ቆሻሻ መንግስት ቢላልን ነጠቀን" ያቤፅ ደነፋ
"ምን አልክ?" የሰማሁትን ማመን አልሆነልኝም። ጆሮዬን በአጭበርባሪነት ጠረጠርኩት
"ቢላልን የቀማን መንግስት ነው"
አሁንም ጆሮዬን ማመን ስላልቻልኩ 'ሰልሰው እስቲ' ማለት ቃጥቶኝ ነበር። 'ያቤፅ አብዶ ይሆን' የቅፅበት ጥያቄ አቃጨለብኝ።
"ቢላል ለምን የሞተ ይመስልሃል?" ጠየቀኝ
"ኑሮ ስለከበደው" መለስኩ
"ኑሮ ለምን ከበደው?" ተኮሳተረ
"ሲሚንቶ ስለተወደደ፥ የግንባታ እቃዎች ዋጋ ስለናረ፥ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ክፉኛ ስለተጎዳ፥ የግንባታ እንቅቃሴ መቋረጥ ስለጀመረ ፥ ግንበኛው ጓደኛችን ላይ ስራ አጥነትን አመጣበት። ስራ ማጣቱ ኑሮውን አከበደው። ይኸው ነው" ሁለታችንም የምናውቀውን ነገርኩት
"ይኽ ለምን ሆነ?"

......

#ነገን_ፍለጋ መፅሐፍ ላይ የተወሰደ። ሙሉውን ከመፅሐፉ አንብቡ


@Tfanos
"ጅብ ቢያነክስ ፥ እስኪነክስ"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

አንዳንዴ ደግነት የማታለያ ወጥመድ ይሆናል፥ ታማኝ መስሎ መታየት የጠንቃቆችን ትጥቅ ያስፈታል ፥ አንዴ ያመነን እንዲጠራጠር ማድረግ ብዙ አቅምን ይጠይቃል።
አንዳንድ ቸርነቶች ወጥመድ ናቸው፥ አንዳንድ በጎነቶች ከክፋት ይመነጫሉ ፥ አንዳንድ ጥሩነቶች የመጨረሻ ግባቸው ጥፋት ነው።

ሮበርት ግሪን "The 48 Laws of Power" የሚል መፅሐፍ አለው። መፅሐፉ ሰዎችን አታሎ በስልጣን መገኘትን ፥ አጭበርብሮ መከበርን ፥ በተንኮል መንገድ ተፅዕኖ መፍጠርን ይሰብካል። የማታለያ መንገዶችን የሚሰብክ መፅሐፍ ነው። ፖለቲከኞችን መረዳት ለሚፈልግ ሰው ጥሩ ትምህርት ይሰጣል።

መፅሐፉ ላይ ከሰፈሩ 48 ሕጎች መካከል 12ኛው ሰዎችን በልግስና ተግባር እንዴት ማታለል እንደሚቻል ያትታል። "አንድ የቅንነት እርምጃ ብዙ የጥፋት እርምጃን ይሸፍንልሃል" ይላል።

ከመፅሐፉ 2 ምሳሌዎችን እንምዘዝ

ሀ፥ ፍራንቼስሶ ቦሪ በ1695 አ.ም የሞተ የተዋጣለት አስመሳይ ሰው ነው።የሚላን ሰው ሲሆን በአንድ ወቅት ወደ አምስተርዳም አቀና። ለታማሚዎች እርዳታ በማድረግ ይታወቃል ፥ ያለ ምንም ክፍያ ምክር ይለግሳል ፥ ለድሆች ገንዘብ ያድላል፥ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ክፊያ አይቀበልም። በአጭሩ ባለ ግርማ-ሞገስ ደግሞም ቸር ሰው ነበር።

ክእለታት በአንዱ ይህ ደግ ሰው ጠፋ። ሰዎች ፈልገው አጡት።
ከመጥፋቱ በፊት ግን በርካታ ሰዎች ገንዘባቸውን እና ውድ አልማዞቻቸውን በአደራ እርሱ ዘንድ አስቀምጠው ነበር። ምክኒያቱም እርሱ በጎ ሰው ስለሆነ እምነት ይጣልበታል። ሲጠፋ እምነቱን ይዞ ኮበለለ። በአደራ የተቀመጠውን ሀብት ይዞ ተሰወረ።

ደግ ሰው መስሎ ከርሞ ሌባ ሆኖ ጨረሰ!

ጅብ ቢያነክስ ፥ እስኪነክስ!

ምሳሌ ለ

ግሪኮች በትሮይ ጦርነት ጊዜ ጠላታቸውን ድል የነሱት በስጦታ በኩል ነው።
ብዙ ጀግኖቻቸውን ሰውተው የትሮይን ግንብ ማፍረስ አልቻሉም። ከበባቸው ድልን አላዋለደላቸውም ነበር። ከእላታት በአንዱ መፍትሔ ፈጠሩ፥ ስጦታን እንደ ወጥመድ የመጠቀም መፍትሔ!

ለትሮጃኖች በስጦታ የሚቀርብ ግዙፍ የእንጨት ፈረስ ገነቡ። ፈረሱ በውስጡ ወታደሮችን መደበቅ የሚችል ነው። ፈረሱን በከተማው መግቢያ በር ላይ አቆሙት ፥ ትሮዮች ፈረሱን ሲመለከቱ ከአማልክት የተላከላቸው ስጦታ መሰሏቸው ወደ ውስጥ አስገቡት።... ከዚህ በኋላ ትሮጃኖች ሀሴት አደረጉ። በሉ ፥ ጠጡ ሰከሩም። ሲተኙ ከፈረሱ ውስጥ የተደበቁ ወታደሮች ወጥተው አጠቋቸው።

አንዲት ስጦታ የጦርነትን አቅጣጫ ወሰነች። በብዙ መስዋዕትነት ያልተፈታ ወገብ ተፈታ ፥ የማይሸነፍ የመሰለው ተሸነፈ... የስጦታ ወጥመድ!
ተገዳዳሪ ጠላት በስጦታ ይታለላል። ስጦታን እንቢ ማለት ለጥቂት ሰዎች ብቻ የተሰጠ ፀጋ ሳይሆን አይቀርም።
አንዳንዴ ደግነት የማታለያ ወጥመድ ይሆናል፥ ታማኝ መስሎ መታየት የጠንቃቆችን ትጥቅ ያስፈታል ፥ አንዴ ያመነን እንዲጠራጠር ማድረግ ብዙ አቅምን ይጠይቃል።

እርግጥ የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም። ነገር ግን የፈረሱ ሰጪ ልብ መታየት አለበት።

የስጦታ ፈረስን ጥርስ አለማየት ጨዋነት ሲሆን ፥ የሰጪውን የልብ ዝንባሌ መመርመር ደግሞ ብልሃት ነው። ብልሃት እና ጨዋነት አብረው ይሄዳሉ!


@Tfanos
የትግራዩ ጦርነት ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበት ነው። ጦርነቱ ባካለለባቸው አከባቢዎች ማለትም በትግራይ በአማራ እና በአፋር ክልል እስከ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል ፥ መቶ ሺዎች ተደፍረዋል ፥ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል... ዛሬ በዩቲዩብ ቻናሌ በዚህ ጉዳይ ያሰናዳሁት ፕሮግራም ይለቀቃል።

ለሌሎች ብታጋሩ እና በዩቲዩብ ቻናሌ ስር አስተያየት ብታጋሩ እወዳለሁ

(አሁን ለማየት ጊዜ ባይኖራችሁም ሼር አድርጉ😎

https://youtu.be/Oo5JzKIkjZ4
ኢቲቪ በብርቱካን ጉዳይ ሌላ ዶክመንተሪ ሰርቷል።

የመንግስት አክቲቪስቶች ፥ የመንግስት ሚዲያዎች ወዘተ የሚሰሩት ስራ በጣም ያስቃል። መንግስታቸውን ለመደገፍ በሚሄዱበት ርቀት በራሳቸው ላይ ግብ ያስቆጥራሉ። ራሳቸውንና መንግስታቸውን መሳቂያ ያደርጋሉ።

ፕሮፖጋንዳ እውቀት ይፈልጋል። በእውቀት የሚሰራ የሞያ ስራ ነው። የሕዝብ ንቃተ ህሊና ፥ ወቅታዊ ሁኔታ ፥ መሬት ላይ ያለ ተጠባጭ እውነታ ፥ የተፎካካሪ ሁኔታ ወዘተ ከግምት ገብቶ ነው ፕሮፖጋንዳ የሚሰራው።

ባለፉት አመታት የመንግስት ሚዲያዎች እና የመንግስት አክቲቪስቶች የሚሰሩት ስራ ሲታይ ያስቃል። ከእያንዳንዱ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በኋላ ትርፉቸው የህዝብ መሳለቅ ነው። ከአማካይ በታች ንቃተ ህሊና ያለውን ሰው እንኳ የማያሳምን ስራ ነው የሚሰሩት።

እንግዲህ ያለፉት አመታት የመንግስት የፕሮፓጋንዳ (የህዝብ ግኑኝነት) ደካማነት ጥቂት ነገሮችን ይነግረናል።

1ኛ ፥ ህዝብን ይንቃሉ። በተራ ድራማ ህዝብን እናታልላለን ብለው ያስባሉ።

2፥ ከስህተት መማር አይችሉም። በየጊዜው በሚሰሩት ስህተት ህዝብ ቢሳለቅባቸውም ከጥፋታቸው ለመማር የሚረዳ ልብ የላቸውም።

3፥ እውቀት አጠሮች ናቸው። የህዝብ ግኑኝነት ስራ የሚፈልገው እውቀት ፥ ልምድ ፥ ስትራቴጂ ወዘተ የላቸውምና በአቦሰጡኝ ይረግጣሉ።

4፥ እውነት የላቸውም። ለህዝብ ግኑኝነት ስራ የሚያቀርቡት ውሃ የሚያነሳ እውነት ፥ የስራ ውጤት ወዘተ ስለሌላቸው የልጅ ድራማ ላይ ያተኩራሉ...

እንድናምናቸው በለፉ ቁጥር ቀጣፊነታቸው እየተገለጠ ነው።


VIA ተስፋኣብ ተሾመ

@Tfanos
@Tfanos
ያየ ሰው ሽመልስ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ደራሲ ነው። 'ጎቲም ሲሞን' የሚል የልብ ወለድ መፅሐፍ አለው። የዛሬ 10 አመት አከባቢ ነው ያነበብኩት። በዛ መፅሐፍ ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለውን ፍላጎት በደንብ አሳይቷል።

ከፋና ሬዲዮ ጀምሮ እከታተለው ነበር። ትንታኔዎችን የሚያቀርብበት መንገድ ደስ ይለኛል። ENN ሲገባ ቋሚ ተከታታዩ ሆንኩ። አብይ ወደ ስልንጣን ሲመጣ ከመንጋው ጋር አልተነዳም። ነገሮችን በጥንቃቄ ለመከታተል ሞክሯል። ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ ቀድሞ ተገንዝቧል።

ENN ሲዘጋ ወደ ናሁ ቴሌቪዥን ገባ። እዛም እከታተለው ነበር።

ኢትዮ ፎረም ገና ጥቂት ተከታይ እያለው ጀምሮ እከታተላለሁ። (ኢትዮ ፎረም ላይ ከአበበ ባዩ ይልቅ በብዛት የምሰማው የያሰውን ነው)
በነገራችን ላይ በሐገራችን ያሉትን የሁሉንም ፅንፍ ሚዲያዎች በተቻለኝ መጠን እከታተላለሁ።

Omn፥ ርዕዮት ፥ ኢትዮ ፎረም ፥ ኢቲቪ ፥ ኢትዮ 360 ፥ የሃሳብ ገበታ ፥ ኩሽ ማዲያ፥ ምንግዜም ሚዲያ... ወዘተ። ሁሉንም እሰማለሁ። ከሁሉም የምቀበለው ደግሞም የማልቀበለው አለ።

ያየሰው ሽመልስ መፅሔት ላይ ሲፅፍ ብዕር ይታዘዝለታል። ቴድሮስ ፀጋዬ እና ያየሰው ሽመልስ ከሚጋሩት ፀጋዮች መካከል አንዱ የፅሐፍ ችሎታ ይመስለኛል። ሁለቱም ጥሩ ፀሐፊ ፥ ጥሩ ተናገሪ ፥ ጥሩ ጠያቂ ናቸው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሩ የህዝብ ግኑኝነት ባለሞያ ያስፈልጋቸዋል። እንደ ያየሰው አይነቱ ሰው ለእንዲህ አይነት ስራ የሚመች ይመስለኛል።
ብልፅግና ፓርቲ በማህበራዊ ሚዲያ ፥ በሜይንስትሪም ሚዲያ ወዘተ ብዙ ፕሮፖጋንዲስቶች አሉት። እኒያ ሁሉ ቢጨመቁ የያየሰውን ሩብ ያህል ተፅዕኖ አይፈጥሩም። በእሱ ፊት ሁሉም ደካማ ናቸው። ምክኒያቱም እሱ በማንበብ አቅም ፥ በፅሉፍ ችሎታ ፥ በስል አንደበት ፥ ሃሳቡን በማደራጀት አቅም ይበልጣቸዋል።

አንዳንድ ሰዎች ያየ ሰውን በወገንተኝነት ይከሱታል። ለምን እንደሚከሰስ ይገባኛል። ግን ያየሰውን በወገንተኝነት የሚከሱ ሰዎች ከእሱ መማር ያለባቸው ቁም ነገር አለ። እሱ በሚሰራበት አቅም ልክ እነሱ ለሚወግኑለት አካል ለመስራት ይጣሩ።

መውጫ ፥

ያየሰው ፈገግ የሚያሰኙኝ አገላለፆች አሉት።

1፥ አብይ አህመድ በሙስሊሙ ኢድ ጊዜ እንደ ሙስሊም በክርስቲያኑ በዓል ጊዜ እንደ ክርስቲያን መሆን መለያው ነው። ይሄን አይቶ ያየሰው "ለፋሲካ ጊዜ የኢየሱስ ወታደር ፥ ለአረፋ ጊዜ የአሏህ ወዛደር" ብሎታል።

2፥ አብይ ወደ ስልጣን የመጣ ጊዜ ከእግሩ ስር መነጠፍ የፈለጉ የአማራ ኤሊቶች ነበሩ። የአብን ሰዎች ፥ የብአዴን ሰዎች ፥ ዛሬ ተቃዋሚ የሆኑ አክቲቪስቶች ወዘተ። እኚህ ሰዎች ያኔ አብይ ሲጋራ ሲያጬስ ቢመለከቱ 'የኔን መዳፍ መተርኮሻ አድርገው' ይሉት ነበር። ያየሰው እኚህን አደር ባዮች "የአብይ አማራ" ብሎ ይጠራቸዋል።

3፥ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ላይ በብዛት ይወድቃሉ። ለወደቁ ተማሪዎች ቀጣይ እጣ ፋንታ ማንም ግድ አይሰጠውም። ይሄን የታዘበው ያየ ሰው "ብርሃኑ ነጋ ሲጥላቸው ብርሃኑ ጁላ ያነሳቸዋል" አለ።

ዞሮ ዞሮ ፥ ፕሮፖጋንዳ መስራት የምትፈልጉ ፥ ዜና መስራት የምትወዱ ወዘተ ከያየሰው ተማሩ።


@Tfanos
ፍልስፍና ምንድነው?

አንዳንዶች ፍልስፍና ፀረ ሐይማኖት እና ፀረ ባህል ይመስላቸዋል። በእርግጥ ፍልስፍና ምንድነው? ፍልስፍና ምን ይጠቅማል?

የዛሬው ደርዘን ጥያቄዎች አጀንዳ ፍልስፍና ነው። እንግዳዬ Yonas Tadesse Berhe ነው።

አድምጡት። ብትችሉ ለሌሎችም አጋሩ። አስተያየታችሁን በቻናሌ ስር ብትሰጡም እወዳለሁ

https://youtu.be/j_-sAO2DwYc
2025/04/13 07:18:47
Back to Top
HTML Embed Code: