tgoop.com/tikvahethmagazine/24019
Last Update:
ከ600 በላይ የሚሆኑ ማኅበራት እና ኮንተራክተሮች የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሰራንበትን ክፍያ በተባለው ቀን ውስጥ አልከፈለንም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
"እያንዳንዱ ማህበር እና ኮንተራክተር ከ 3 እስከ 40 ሚሊየን ብር ወጪ አድርጓል፤ ቤቶቹም አልቀው ነዋሪ ገብቶባቸዋል። ሆኖም ግን ክፍያ እስከአሁን አልተከፈለንም" ሲሉ ነው ቅሬታቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የገለጹት።
በተጨማሪም ቅሬታ አቅራቢዎቹ "ሥራውን በሁለት ሳምንት ውስጥ ካጠናቀቃችሁ በአንድ ሳምንት ውስጥ ክፍያችሁን እንፈፅማለን የሚል ቃል ገብተውልን ነበር" ሲሉ ክፍያቸው በጊዜ አለመፈጸሙን አስረድተዋል።
አያይዘውም፥ ''ሥራውን ካጠናቀቅን ከአንድ ወር በላይ ሆኖናል ከስራው አስቸኳይነት አንፃር በብድር ጭምር ነው የሰራነው" በማለት ክፍያው መዘግየቱ ጫና እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሽመልስ ታምራትን ጠይቀናል። ዋና ዳይሬክተሩ ለሁሉም ኮንትራክተሮች እና ማህበራቶች ክፍያቸውን ለመፈፀም ጥረት እያደረግን ነው የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በዝርዝር ምን አሉ ?
ዳይሬክተሩ የከተማ አስተዳደሩ በጫረታ የሚሸጡ የንግድ ቤቶችን ወደ መኖሪያ ቤት ለመቀየር የወሰነውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ የንግድ ቤቶችን በፍጥነት በመቀየር ለዜጎች ለማስረከብ የተለያዩ ማኅበራትንና ኮንተራክተሮችን ማሰማራቱን ገልፀዋል።
በዚህም ከ400 የማያንሱ ኮንትራክተሮች እና ማኅበራት እንደተሳተፉ እንዲሁም ሥራውንም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 57 ቀናቶች መውሰዳቸውን ዳይሬክተሩ አክለዋል።
ክፍያቸውን በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄ በከተማችን በተለያዩ ቦታዎች በኮርፖሬሽኑ ስር ባሉ ቅርንጫፎች አማካኝነት እንደ አፈፃፀማቸው የክፍያ ሰነዶቻቸው በሂደት እየመጣ እየተከፈላቸው ነው ብለዋል።
"ከሁሉም ቅርንጫፎች ሂደቱን ጨርሶ የመጣውን እየከፈልን ነው እስካሁን ከ270 በላይ ለሚሆኑ ኮንተራክተሮች እና ማህበራቶች ክፍያቸው ተሰጥቷቸዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ክፍያ ያልተሰጣቸው ኮንትራክተሮች እና ማኅበራቶች ደግሞ አፈፃፀማቸው በቅርንጫፎች ተገምግሞ ሂደቱን ጠብቆ ባለመምጣቱ መዘግየቱን ነው ያነሱት።
በቢሮ ደረጃ ቅሬታ ያቀረቡ ኮንትራክተሮች እና ማኅበራቶች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከልም ይህ ዘገባ እስከ በተጠናከረበት ድረስ የተከፈላቸው ስለመኖራቸውም ጠቁመዋል።
እስካሁን ክፍያ ላልተሰጣቸው ማኅበራቶች እና ኮንተራክተሮች ክፍያቸውን ለመክፈል በቢሮ ደረጃ እየተሰራ መሆኑንም ነው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የገለጹት።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፥ "ነዋሪውን ለመታደግ ሥራው በአስቸኳይ ሌት ከቀን ነው የተሰራው፤ ክፍያቸውም ቅደም ተከተላቸውን ተከትሎ እየተፈፀመ ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
#TikvahEthiopia
@tikvahethmagazine