tgoop.com/tmhrtegeeze/10187
Last Update:
#መጻጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሣምንት)
በዐቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት መካከል አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚያነሣ በመሆኑ ነው፡፡ «38 ዓመት የታመመውን መጻጉዕን ኢየሱስ አዳነው» እንዲሁም ልጁ የታመመበት የመቶ አለቃው "ጌታዬ በቃልህ እዘዝ ልጄ ይድናል፡፡ በቤቴ ጣርያ ሥር አንተ ልትገባ አይገባህም" አለው። "ጌታ በሚያልፍበት መንገድ አንድ ዕውር ፈውሰኝ" ብሎ ጮኸ የሚመሩት ሰዎች ዝም በል አሉት፡፡ ዕውሩ ግን እምቢ ብሎ "የዳዊት ልጅ ጌታ ይቅር በለኝ ዕርዳኝ" እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ "በሰንበት ኢየሱስ መጻጉዕን ተነሥ አልጋህን ተሸከም ባለው ጊዜ ቀኑ ሰንበት ነበረ፡፡ መጻጉዕም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንበት ፈውሷልና "በሰንበት ድውያንን ፈወሰ የዕውራንንም ዓይኖች አበራ" እያለ 38 ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ሲማቅቅ የኖረውን መጻጉዕንና ሌሎቹን በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን፣ ዕውር ማብራቱን፣ አንካሶችን ማርታቱን፣ ልምሾዎችን ማዳኑን፣ አጋንንትን ማውጣቱን፣ ወዘተ እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ዕለቱና ሳምንቱ መጻጉዕ ተብሏል፡፡
ስለዚህም ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በነዚህ ሁሉ ታሪኮች የመጻጉዕንና የሌሎቹን ሕሙማን ሁሉ ደኅንነት ታሪክ እንረዳለን፡፡ የሰንበቱም ስያሜ ልብ ወለድ አጠራር ሳይሆን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢርና የጾመ ድጓውን ይትበሀል ተከትሎ የተሰየመ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
#የዕለቱ_ምንባቦች፦
1ኛ. የቅ.ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላ. 5÷1-26
2ኛ. የቅ. ያዕቆብ መልእክት 5÷14-20
3ኛ. የሐዋርያት ሥራ 3÷1-12
#የዕለቱ_ምስባክ፦
መዝ 4ዐ(41)÷3
እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ
ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ
አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ።
(እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፡፡ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል እኔስ አቤቱ ማረኝ፡፡) መዝ 4ዐ÷3 የሚለው ይሆናል፡፡
#የዕለቱ_የወንጌል፦
በዮሐንስ ወንጌል 5፥1-25 ድረስ ያለው ነው፡፡
ያንን ተስፋ ያልነበረውን በሽተኛ ከደዌ ሥጋው ፈውሶ ሕይወትን የሰጠው አምላክ፣ እኛንም በውስጥ በአፍአ ካለብን ደዌ ሥጋና ደዌ ነፍስ እንዲፈውሰን፤ ቁስለ ኃጢአታችንን እንዲያደርቅልን፣ በሕይወትና በጤና እንዲጠብቀን የእርሱ የጌታች ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
•➢ ሼር // SHARE
https://www.tgoop.com/tmhrtegeeze
BY ✝️(ትምህርተ ግዕዝ)✝️
Share with your friend now:
tgoop.com/tmhrtegeeze/10187