tgoop.com/tmhrtegeeze/11749
Last Update:
[ታኅሣሥ 22 የአምላክ እናት ተአምሯን ለጻፈላት ለቅዱስ ደቅስዮስ በረከቷን የሰጠችበት]
✍ ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
💥 ደቅስዮስ የተወለደው በ607 ዓ.ም. ሲኾን ከጊዜ በኋላ የቶሌዶ ጳጳስ የሆነው አጎቱ ዩጄኒየስ በወጣትነቱ ቃለ እግዚአብሔርን ያስተምረው ነበረ። ከዚያም በ632 ዓ.ም አካባቢ የቶሌዶ ኤጲስ ቆጶስ ኤላዲዎስ ዲያቆን አድርጎ ሾሞታል። ከፍ ካለ በኋላ በቶሌዶ አቅራቢያ ወደሚገኘው የአጋሊያ ገዳም በመግባት የገዳሙ አበምኔት ኾነ። ከዚያም በ657 የቶሌዶ ሊቀ ጳጳስ ኾኖ ተመረጠ።
💥 ደቅስዮስ እመቤታችንን በፍጹም ልቡ ከመውደዱ የተነሣ በተቻለዉም ኹሉ ያገለግላት ነበር “ወእምንደተ ፍቅሩ አስተጋብአ መጽሐፈ ተአምሪሃ” ይላል ከፍቅሩም ጽናት የተነሣ ክብሯን፣ ንጽሕናዋን፣ ቅድስናዋን፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋን፣ ወላዲተ አምላክነቷን፣ ተአምሯን የሚናገር መጽሐፍን ሰበሰበ።
💥 ደቅስዮስ መሰብሰብ ብቻ ሳይኾን ድርሰትም ደራሲ ነበረ። ከጻፋቸው ከደብዳቤዎቹ ሁለቱ እና አራቱ ጽሑፎቹ አሁንም ድረስ አሉ። በተለይ የመዠመሪያው እና ዋናው ክፍል ስድስት ድርሰቶችን ያቀፈና ልክ እንደ ጀሮም ርሱም ሄልቪደስን ተቃውሞ ስለ እመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና የጻፈው "De virginitate perpetuâ sanctae Mariae adversus tres infideles" (On the Perpetual Virginity of Holy Mary) በመባል የሚታወቅ ሥራው ነው። ይኽ የደቅስዮስ መጽሐፍ ለ3 የተከፈለ ሲኾን "ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ" ዘላለማዊት ድንግል መኾኗን ይተነትናል።
💥 ቅዱስ ደቅስዮስ የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልናዋ የልጇ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት የሚገልጽ ምልክት እንደኾነ ሲገልጽ ልጇ እግዚአብሔር ነውና ብቻውን በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ሊወለድ ችሏል ብሏል።
💥 ደቅስዮስ እመቤታችንን በጽሑፉ ማርያም ብቻ ብሎ በስሟ አይጠራትም። ይልቁኑ ድንግሊቱ፣ የእኛ ድንግል ይላታል።
💥 ያን ጊዜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻለት “ይኽን መጽሐፍ ስለ ጻፍኽልኝ ደስ ብሎኛል” ብላው ባርካው ተሰወረች፡፡
💥 በተጨማሪም በ304 ዓ.ም. በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ሰማዕትነትን በተቀበለችው በቅድስት ሊዮካዲያ (Saint Leocadia) የከበረ ዐፅም ፊት ሲጸልይ በተአምራት ተነሥታ የአምላክን እናት ስላከበራት አመስግናዋለች።
💥 ቅዱስ ደቅስዮስም ይኽነን ኹሉ ካየ በኋላ እጅጉን በመደሰት ለእመቤታችን ክብር ምን መሥራት እንዳለበት በማሰብ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ያበሠረበት መጋቢት 29 ቀን የዐቢይ ጾም በመኾኑ ምክንያት ሰዎች ማክበር ያልተቻላቸውን በዓለ ብሥራትን ከልደት በዓል ስምንት ቀናት ቀደም በማድረግ ታኅሣሥ 22 ዕለት እንዲከበር ሥርዐትን ሠራ። በቶሌዶ በተደረገ ጉባኤ ለአምላክ እናት ክብር የተለየ የበዓላቷን ቀን ተደነገገ።
💥 ምእመናንም እጅጉን በመደሰት በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ እግዚአብሔር በማሕፀነ ማርያም የተፀነሰበትን በዓል ለውጥ በማሰብ በዓሉን በድምቀት አከበሩ፡፡ ያን ጊዜ በወርኃ ታኅሣሥ በ665 ዓ.ም. በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች እመቤታችን ለደቅስዮስ ለብቻው ተገልጻለት “ወዳጄ ደቅስዮስ ባንተ ደስ አለኝ፤ ሥራኽንም ወደድኊ፤ በዓሌን አክብረኽ ስለ እኔ ሰውን ኹሉ ደስ አሰኝተኻልና እኔም ዋጋኽን ልሰጥኽ እወዳለኊ ትቀመጥበትም ዘንድ ይኽነን ወንበር አመጣኹልኽ” በማለት በወንበሩም ላይ ማንም ሊቀመጥባት የሚቻለው እንደሌለ ነግራው ከርሱ ተሰወረች፡፡
💥 በሌላ ጊዜ ኤጲስ ቆጶሱ ደቅስዮስ ከምእመናን ጋር የእመቤታችንን መዝሙር ሲዘምሩ ከፍተኛ ብርሃን ወርዶ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲከብባት አብዛኞቹ ምእመናን ፈርተው ሲሸሹ ደቅስዮስ ከጥቂት ዲያቆናት ጋር ብቻ ቀረ። ያንጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም ደናግልን አስከትላ ወርዳ በኤጲስ ቆጶስ ዙፋን ላይ ተቀምጣ አየ። እመቤታችንም ደቅስዮስን ለታማኝነቱ አመስግናው እጅግ የተለየ ልብሰ ተክህኖ በበዓላቷ ላይ ብቻ እንዲለብስ ሰጥታው በእመቤታችን በዓላት ይለብሰው ነበር።
💥 ቅዱስ ደቅስዮስም በ667 ዓ.ም. ከዚኽ ዓለም በሕይወተ ሥጋ በተለየ ጊዜ እመቤታችን የባረከችውን ልብስ በቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት በክብር አኖሯት፤ ከርሱ በኋላ የተሾመው ኤጲስ ቆጶስ ግን ያችን ልብስ ሊለብሳትና በደቅስዮስም ወንበር ሊቀመጥ ወደደ።
💥 ቀሳውስትና መምህራን ግን የልብሷን ክብር በመንገር ይኽነን እንዳያደርግ ቢለምኑት ርሱ ግን ልክ እንደ ዖዝያን በድፍረት ልብሷን ለብሶ በወንበሩ በተቀመጠ ጊዜ ሐናንያና ሰጲራ በቅዱስ ጴጥሮስ ፊት ተቀሥፈው እንደሞቱ፤ ርሱም “ወድቀ በጊዜሁ እምላዕለ ውእቱ መንበር በቅድመ ኲሎሙ ሰብእ እለ ሀለዉ ውስተ ቤተ ክርስቲያን ወሞተ በእኩይ ሞት ወሕሡም ፈድፋደ” ይላል በዚኽ የድፍረት ኀጢአቱ ከዚያ ወንበር ላይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉ ሰዎች ኹሉ ፊት ወድቆ ክፉ አሟሟትን ሞቷል፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተደረገው ተአምር ሕዝቡ በመደነቅ ምስጉን እግዚአብሔርን በማመስገን አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችንን ስለ አደረገችው ተአምር እጅጉን አክብረዋታል፡፡ በግእዝ በብራና በተጻፉት ተአምረ ማርያም ላይ ይኽ የቅዱስ ደቅስዮስ ታሪክ ተሥሎ ማየት የተለመደ ነው።
💥 ከዚያ በኋላ የሰጠችው ልብስ ቢሰወርም ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ለደቅስዮስ ስትገለጥለት እግሯን ያሳረፈችበት ድንጋይ ግን በቶሌዶ ካቴድራል ጸሎት ቤት ውስጥ ይከበራል።
💥 ንጉሥ ዳዊትም እንደነ ደቅስዮስ ላሉ እመቤታችንን ለሚወዷት ኹሉ በምልጃዋ ከልጇ ስለምታሰጣቸው ታላቅ መንፈሳዊ በረከት መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ገልጦለት “ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ” (በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ) በማለት ከገለጠ በኋላ “ወትሠይሚዮሙ መላእክተ ለኲሉ ምድር” (በምድርም ኹሉ ላይ ገዢዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ) በማለት የሠያሜ ነገሥት፣ የሠያሜ ካህናት የክርስቶስ እናት መኾኗንና፤ ይኽነንም የአምላክ እናትነቷን ለመሰከሩ ለነ ደቅስዮስ ወንበር፤ ለነ ኒቆላዎስ ዐጽፍ፣ ለነ ቅዱስ ኤፍሬም “አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ” (አቤቱ የጸጋኽን ማዕበል ግታው፤ ወስነው) እስኪሉ ድረስ በቃል ኪዳኗና በአማላጅነቷ ያሰጠቻቸው ታላቅ በረከት መንፈሳዊ ሹመትና ብቃት መኾኑን አሳይቷል፡፡
💥 “ወይዘክሩ ስመኪ በኲሉ ትውልደ ትውልድ” (ለልጅ ልጅ ኹሉ ስምሽን ያሳስባሉ) በማለት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት በርሷ ወላዲተ አምላክነት በማመን የጸና ያለፈውና የሚመጣው ትውልድ ኹሉ “ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) እያለ የተቀደሰ ስሟን ሳይጠራ የሚውል ማንም እንደማይኖር ቅዱስ ዳዊት በመንፈሰ እግዚአብሔር ገላጭነት ተናግሯል (መዝ ፵፬፥፱-፲፯)፡፡
💥 ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በሕማማት ሰላምታው ላይ፦
“ማርያም ሀብኒ ልብሰ ትፍሥሕት ወተድላ
ከመ ወሀብኪዮሙ ቅድመ ምስለ መሐላ
ለደቅስዮስ ወለኒቆላ ሰላም ለኪ"
(ለኒቆላና ለደቅስዮስ ከቃል ኪዳን ጋራ አስቀድመሽ እንደሰጠሻቸው ሰላምታ የተገባሽ ማርያም የፍጹም ደስታና ተድላ ልብስን ስጪኝ) በማለት ተማፅኗታል፡፡
💥 የነገረ ማርያም ሊቃውንት የነበሩት አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ እመቤታችን ተአምሯን ሰብስቦ ላዘጋጀላት ለደቅስዮስ ታላቅ ጸጋን በቃል ኪዳኗ እንዳሰጠች ሲገልጹ፦
BY ✝️(ትምህርተ ግዕዝ)✝️
Share with your friend now:
tgoop.com/tmhrtegeeze/11749