tgoop.com/tmhrteorthodox/7537
Last Update:
[በዓለ ሆሣዕና]
✍በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ የተለጠፈ)
♥ ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ “ሆሻአና” ሲባል ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ክንፋቸው ትእምርተ መስቀል የሚሠራው ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸከሙት ጌታ በትሕትና ኾኖ ጀርባዋ ላይ ትእምርተ መስቀል ባለባት በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡
♥ ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ ሲጻፍ በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል፡፡
♥ ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት፤ ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታም ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” በማለት እንደ ማዕምረ ኅቡአትነቱ (የተሰወረውን ዐዋቂነቱ) በመንደሯ ውስጥ ስለታሰሩት አህያና ውርንጫ አስቀድሞ ይነግራቸዋል፡፡
♥ በተናቀች ግርግም በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ላምና አህያ ትንፋሻቸውን እንደገበሩለት፤ አኹንም በሰዎች በተናቀች አህያ በጌትነት ተቀምጦ እንዲመሰገንባት መርጧታል፡፡
❤ በልደቱ ማንም ያልገባባት የማይገባባት የሕዝቅኤል የታተመች መቅደስ የተባለች ዘላለማዊት ድንግል እመቤታችንን እንደመረጠ ዛሬም በሆሣዕና ማንም ሰው ያልተቀመጠበት ውርንጫ እንዲያመጡ አዘዘ።
♦ ከዚያም “ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ጌታ ርሱ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም እንዲያመጡ አዟቸዋልና።
♥ ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡” ይላል።
♥ ሊቁ አምብሮስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው የማሰር የመፍታት ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑን ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል።
♥ አምጥተው “ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”፤ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ። ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ በማለት መተርጉማን ይተነትናሉ፡፡ በተጨማሪም ልብስ በልጅነት ይመሰላልና የተገፈፍነውን የጸጋ ልብሳችን (ልጅነትን) ትመልስልናለህ ሲሉ ነው፨
♥ ቅዱስ ኤፍሬም ይኽነን ሲተረጉም "ልብሳቸውን አውልቀው ያነጠፉለት ሰዎች አሮጌውን ማንነታቸውን ትተው ዐዲሱን ልብስ ክርስቶስን መልበሳቸውን ያስረዳል። ሐዋርያ ጳውሎስ “አሮጌውን ሰውነት አስወግዳችሁ አዲሱን ሰው ልበሱት” እንዳለው (ኤፌ.4፣23) ይኸውም ጥምቀት ነው" ይላል።
♥ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ሲኾን መተርጒማነ ሐዲስ በትርጓሜ ወንጌል ላይ እንደሚገልጹት 14ቱን ጌታ በእግሩ ሲኼድ 2ቱን በአህያዋ፤ በውርንጫዋ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሷን ዞሯል፡- 14ቱ በእግሩ መኼዱ የ10ሩ ቃላት 4ቱ የ4ቱ ኪዳናት ምሳሌ፡፡ 2ቱ በአህያዋ መጓዙ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ፤ 3ቱን በውርንጫዋ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን መዞሩ የ3ትነቱ የአንድነቱ ምሳሌ ነበር፡፡
♥ ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በፍርሀት በረአድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት ርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በነርሱ ተቀመጠ። በተጨማሪም መተርጉማን እንዳመሰጠሩት በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡
♥ በተጨማሪም አህያ ሲፈጥራት በጀርባዋ ላይ ትእምርተ መስቀል ያላት ናትና ትእምርተ መስቀል ያለባት እእርሷ እንድትፈታ ማዘዙ ከ5 ቀን በኋላ በመስቀል ተሰቅሎ በሲኦል የታሠሩትን የሰው ልጆችን ነጻ ሊያወጣ መጥቷልና አህያን መርጧታል፨
♥ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚኽ ነገር በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡ ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡ ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት አመስጥሯል፡፡
♥ ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡ ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው (መዝ.49፡12)፡፡ በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡ እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡ ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲላቸውም እንደ አህያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡ ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጿል፡፡
♥ ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው ስንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ነበር። እንስሳዋ እንኳን ጌታ ቢቀመጥባት እንዲህ ክብር ያገኘች ከሆነ ያደረባቸው ቅዱሳንማ የሚገባቸው ክብር ምን ያህል ይሆን? ይልቁኑ 9 ወር ከ5 ቀናት በማሕፀኗ የተሸከመችው ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሰው የሆነውን አምላክ የወለደችው የቅድስት ድንግል ማርያም ክብርማ እጅጉን ታላቅ ነው።
❤ ጌታ የተቀመጠባት አህያ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባች ጌታ ያደረባቸው ምእመናን ደግሞ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይገባሉ።
BY 🇪🇹✝️የኦርቶዶክስ ንግስ በአላት ✝️🇪🇹
Share with your friend now:
tgoop.com/tmhrteorthodox/7537