Telegram Web
+#አዋልድ_መጻሕፍት_ለሃይማኖት_ማስረጃ_ኾነው_አይጠቀሱምን?+++

[] የሚጠቀሱ አሉ፤ የማይጠቀሱም አሉ!

አንዳንዴ ገድላትም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ለማስረዳት ይጠቀሱ ይኾናል።

ለምሳሌ በሃይማኖተ አበው " ቅዱስ ባስልዮስ ... ስለ ቦሊጣ ሰማዕት በተናገረው ድርሳኑ ስለኛ እግዚአብሔር በሰው መካከል ተገለጠ፤ ብሉይ ሥጋን ለማደስ ቃል ሥጋ ኾነ፤ ባሕርያችንንም ገንዘብ አደረገ፤ የኃጢአት ምርኮኞችን ነጻ የሚያወጣቸው፥ ከበደለኞች ጋር ተቈጠረ፤ በጨለማ ውስጥ ለነበሩ ሰዎች እውነተኛ ፀሐይ ወጣላቸው፤ የማይታመመው በመስቀል ላይ ታመመ፤ ሕይወት እርሱ ሞተ፤ ብርሃን በሲኦል ተገለጠ፤ የተቀበሩትን የሚያነሣ እርሱ ከሙታን ጋር ተቈጠረ ብሎ ተናገረ" ይላል። (ሃይ ዘባስልዮስ ምዕ 96፥42)።

- "የቤተ ክርስቲያን ዐምድ ቅድስ ባስልዮስም ስለ ኢየሉጣ ሰማዕት በተናገረው ድርሳኑ አምላክ ስለኛ ሰው ኾነ፤ በሰው መካከል ተመላለሰ፤ ከተገፉት ጋር የሚገፋ ኾነ፤ የተጎዱትን ያድን ዘንድ ረዳት ለሌላቸውም ረዳት ይኾናቸው ዘንድ ይህን ኹሉ ሠራ፤ ቀድሞ ሥጋ ያልነበረው ዛሬ ሥጋን ተዋሐደ፤ ተሰቀለ፤ ሕይወት እሱ በሥጋ ሞተ፤ ብርሃን እሱ ወደ ሲኦል ገባ፤ ይህም ኹሉ የኾነው አዳምና ልጆቹም ስለ ተጎዱ ነው አለ" እንዲል። (ሃይ ዘዮሐንስ (የአንጾኪያ፣ የሶርያ፣ የባቢሎን ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ) ምዕ 114፥20)።

- አድማሱ ጀንበሬ በአጽንዖት የሚሉን አለ፦ "ሃይማኖተ አበው፣ አፈወርቅ፣ ቄርሎስ፣ ፍትሐ ነገሥት፣ 14ቱ ቅዳሴያት፣ ፊልክስዩስ፣ ማር ይስሐቅ፣ አረጋዊ መንፈሳዊም ሠለስቱ ምዕት በፍትሐ ነገሥት ከቈጠሯቸው ጋር አንድ ኾነው ይቆጠራሉ። ቅዱሳት መጻሕፍት ይባላሉ።" ይላሉ። (አድማሱ ጀንበሬ፣ ኰኵሐ ሃይማኖት፣ 2012 ዓ.ም፣ ገጽ 176)። ለአበው የትርጓሜያት መጻሕፍትና ሥርዓተ አምልኮትን የሚፈጸምባቸው የሥርዓት መጻሕፍትን እንዲሁም ኅብስትና ወይን ቀርቦ ወደ አማናዊው ቅዱስ ሥጋና ደም (ቅዱስ ቍርባን) የሚለወጥበት ጸሎት የሚከወንበትን የቅዳሴያት መጻሕፍት እንዴት በጥንቃቄ እንደ ጠቀሷቸው ልብ እንበል። እነዚህን አዋልድ መጻሕፍት እንደ መሠረታዊ መጻሕፍት አድርገው መጥቀሳቸውን ልብ ማለት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ በጒሜ ትምህርት የሚሰጥበትን የምንኲስናን ሕይወት ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀውን መጽሐፍም ትልቅ ቦታ እንዳለው ይጠቁሙናል። አድማሱ ጀንበሬ ፕሮቴስታንታዊውን መናፍቅ "... እንግዲህ የእግዚአብሔርን አምላክነት ከሚናገሩት መጻሕፍት ውስጥ ይህ ሰው የጻፈው ነው፤ ይህም አዋልድ ነው፤ አልቀበልም ማለት የተሳሳተ ንግግር መኾኑን ትረዳ ዘንድ ..." ይላሉ። (እንደ ላይኛው ገጽ 168)። እንዲሁ በመሰለን ተነሥተን ይሄን አልቀበልም፣ ይህን እቀበላለሁኝ እያልን በመጻሕፍት ተጽፈው ለተቀመጡ ምንባባት የራስን አእምሮ መጣኝ ወይም መዛኝ ከማድረግ ስሑት አካሄድ እንድንወጣ ይመክሩናል። ማንኛውንም ሃይማኖታዊ ጉዳይ በራስ መረዳት ልክ አድርጎ መጓዝ ኦርቶዶክሳዊ አካሄድ ካለመኾኑም በተጨማሪ መዳረሻው በትዕቢት እሾህ ተወግቶ በክሕደት ገደል ውስጥ መግባት ነው።

አድማሱ ጀንበሬ መልክአ ማርያምን ጠቅሶ ለሚተቸው ፕሮቴስታንት ሲመልሱ "ከዚህ ከፍ ብሎ በሚገኘው መሥመር መጻሕፍት ማታለያ አዋልድ የተባሉ ልብ ወለድ መነኰሳቱ ሰበኩት ብለህ አዋልድ መጻሕፍትን ስትነቅፍ ተናግረህ ነበረ። እኛ ከጸሎት በቀር ለሃይማኖትና ለምግባር ምስክር አድርገን የማንጠቅሳቸውን መልካ መልኮችን በቂ ምስክሮች አድርገህ ከጠቀስክልኝ ከላይ የተናገርከውን አዋልድ መጻሕፍት ማታለያ መባላቸው ቀርቶ ባንተው ቃል ተሠይመው ለምስክርነት የበቁ እውነተኞች መጻሕፍት መኾናቸውን ማረጋገጥህን አስተውል። እንግዲህ አንተ የጠቀስካቸውን አዋልድ ምናልባት እኔ የጠቀስኩልህ እንደ ኾነ ቅር እንዳይልህና ሰው እንዳይታዘብህ አደራ" ይላሉ። (እንደ ላይኛው ገጽ 85-86)። ይህ ደግሞ በአንድ በኩል እንደ መልካ መልኮች ዓይነት መጻሕፍት የተዘጋጁበትን ዓላማ የሚያሳስብ ነው በሌላ በኩል አዋልድ መጻሕፍትን አልቀበልም የሚሉ መናፍቃን ያን አናምንበትም ያሉትን መጻሕፍት ጠቅሰው የመሞገት ሥልጣን እንደ ማይኖራቸው አመልካች ነው። እንግዲህ መጻሕፍትን ባልተጻፉበት ዐውድ መገምገም ፍጹም ስሑት የኾነ አካሄድ መኾኑን ልብ ከማለት ጋር አዋልድ መጻሕፍትን የማይቀበሉ መናፍቃን ለማዘናጋት የሚሄዱበትን መንገድ መለየት ያስፈልጋል።

ሌላው እዚህ ጋር ልብ ማለት የሚገባን የጸሎት መጻሕፍት ኹሉ ለሃይማኖት አስረጅ ተደርገው አይጠቀሱም ግን አይባልም። ለምሳሌ ውዳሴ ማርያም፣ 14 ቅዳሴያት፣ ... ሊጠቀሱ ይችላሉና። በኦርቶዶክስ የምናምነውን እንጸልያለን የምንጸልየውንም እናምናለን የሚለውን መሠረታዊ ሐሳብ ቸል የምንል አይደለምና። ዶግክትሪናችንን በራሱ እንደምንጸልየው ልብ ማለት ይገባልና። ጸሎተ ሃይማኖት ብለን የምንጸልየውም ለዚህ ማሳያ መኾኑ ግልጽ ነውና። መሠረታዊ ዓላማቸው ግን ርእሰ ጉዳያቸውን ማዕከል ያደረገ መኾኑን ልብ ማለት ይገባል። የተለያዩ ዓይነት አዋልድ መጻሕፍት አሉ ማለታችንም ከርእሰ ጉዳያቸው አንጻር ነው። ዋና ጉዳይ ያደረጉትን ትተን ወደ ሌላ ወስደን ቸኩል ድምዳሜ ውስጥ መግባት አይጠበቅብንም።

በቦሩ ሜዳ ላይ ሦስት ልደት የሚል ከመጻሕፍት ምንጭ አምጣ ሲባል "በደብረ ብርሃን በሚገኝ ተአምረ ማርያም ላይ አለ" ማለቱ ትችትን ያመጣበት ተአምረ ማርያምን አንቀበልም ለማለት ወይም አያስፈልግም ለማለት ሳይኾን ሃይማኖታዊ ዶክትሪንን ለማስተማር ታቅዶ የተጻፈ አይደለም ለማለት ነው። የተአምር ማርያም ዋና ዓላማው እግዚአብሔር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አድሮ ያደረገውን መክራት ማሳየት እንጂ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን ማስተማር አይደለምና። ብዙ ጊዜ Missing the point Fallacy (ነጥቡን የመሳት ስሕተት) ይሠራል። አዋልድ መጻሕፍት ሲጠኑ ከተጻፉበት መሠረታዊ ሐሳብ አንጻር ይገመገማሉ እንጂ ወደ ሌላ ዘወር ተደርገው ሊገመገሙ አይገባም። ተአምር የሚታየው ከታምር አንጻር ነው፤ ገድልም ከገድል አንጻር፤ ሌላውም ከዚያ አንጻር እንጂ ገድልን ሃይማኖተ አበው፥ ሃይማኖተ አበውንም ገድል አድርጎ ማሰብ መሠረታዊውን ነጥብ መሳት ነው። የቦሩ ሜዳው ጒባኤ አዋልድ መጻሕፍት ብዙም ጥቅም እንደሌላቸው አስረጅ ሳይኾን እንዲያውም እጅጉን ጠቃሚ መኾኑን ጠቋሚ ነው። ኹለት ልደት የሚለው በዋነኛነት ትክክል መኾኑ የተረዳው በሃይማኖተ አበው ባሉ ምንባባት ነውና። ሃይማኖተ አበው ደግሞ ቍጥሩ ከአዋልድ መኾኑ ግልጽ ነው። ከዚያ ውጭ ያልተባለን ማለት አግባብ አይደለም። ይህም ማለት ተአምረ ማርያምን ሃይማኖተ አበው አድርጎ ከማሰብ ነጥብን ከመሳት ስሕተት መጠበቅ ይገባል።

ታምራትን በተመለከተ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የቅድስት ማክሪንን ሕይወት ሲጽፍ የሰጠው ጠቃሚ አስተያየት አለ። ይኸውም፦ "በጣም ትንሽ እምነት ያላቸውና በእግዚአብሔር ስጦታ የማያምኑ ሰዎች ወደ መጎዳት እንዳይመጡ፥ በዚህ ምክንያት ታላቅ ታምራትን መጻፍ ትቼያለሁኝ፤ ስለዚህ እንደማስበው ከኾነ አስቀድሜ ያልኹት የማክሪንን ታሪክ መጽሐፍ ለመፈጸም በቂ ነው።" ይላል። (The Life of SAINT MACRINA BY Gregorry, BisHop of Nyssa /Translated, with introduction and notes, by Kevin Corrigan p.54)። ይህ እንግዲህ አስተውሎት ያለበት ጥንቃቄ ነው። ይህን ሊቁ ማለት በፈለገበት መንፈስ ብቻ ኾነን የምንረዳው እንጂ ታላላቅ ታምራት በዐሥራው መጻሕፍት ውስጥ ተጽፈው ስለምናገኝ
1
ምእመናን እንዲረዱ ማድረግ የሚገባን መሠረታዊውን የታምራትን አረዳድ ነው። ተአምር በቃ እንደ ተአምር የሚወስዱት መኾኑን ልብ ማለት ይገባል። መቼስ ተአምራትን እንደ ተለመደ ክስተት አድርገን ብቻ እንውሰዳቸው ካልን ትልቅ ችግር ውስጥ የምንገባ መኾኑን አንዘነጋም። አረዳዳችን ካልተስተካከለ ኦርቶዶክሳዊ መኾን አንችልም። ሕሊናችንን አበዋዊ ለማድረግ መጣር ይጠበቅብናል። የአበውን አረዳድ ትተን በኛ መጠን ልክ ብቻ ነገሮችን የምንቃኝ ከኾነ መጽሐፍ ቅዱስንም ቢኾን የመቀበል ዕድላችን አናስ ይኾናል። ስለዚህ በጣም በጥንቃቄ እና በእርጋታ በትሕትናም ኾኖ አካሄድን መመርመር ያስፈልጋል።

መርሳት የሌለብን ነገር "አዳኛችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አምላክን ያለምንም እንከን የወለደች የአምላክ እናት እና ቅዱሳን የሚያደርጉትን ልዩ ተአምራት በንጽሕና፣ በፍጹም እምነት በፍጹም ነፍስና በፍጹም ልብ ኾነው የማይቀበሉ ነገር ግን ይህን ማድረግ አይችሉም በማለት የሚያሾፉ፣ በራሳቸውም ሐሳብ አጣመው የሚተረጒሙ፣ በራሳቸው ሐሳብ ብቻ የሚመዝኑ፣ ውግዘት የሚገባቸው መኾናቸውን የሚጠቁሙ ምንባባት ኹሉ አሉ። (The Synodikon of Orthodox)። በተአምረ ማርያም መቅድም ላይ ያለውንም ግዝት የምናውቀው ነው። ስለዚህ ስላልመሰለን ብቻ ቸኩለን ሌላ ባዕድ ነገር ለማምጣት ባንጥር መልካም ነው።

¤ በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ ያሉ ጸነን የሚሉ ምንባባት ይውጡን?

ጸነን የሚሉ ምንባባት ይውጡ ከማለት ይልቅ የሚሻለው አረዳዳቸውን ማወቅ ነው። ትክክል ቢኾኑ እንኳን ጸነን ስለሚሉ እያሉ በራስ የመረዳትና የማሰብ መጠን ልክ አድርጎ ማሰብ ወደ ከባድ ሌላ ስሕተት ሊወስድ ይችላልና። ኹሉን ነገር በራሱ መጠን ልክ አድርጎ ማሰብ የሚፈልግ ሰው እንዴት ኾኖ ኦርቶዶክስ ሊኾን ይችላል? ይህ ሰው ኋላ ሃይማኖትን በራሱ መጠን ልክ አድርጎ ወደ መረዳት እንደማይወርድ ማን እርግጠኛ ይኾናል? የአረዳድ መንገዱ ስሑት ከኾነ ያን አቅንቶ መሠረታዊ በኾነው የክርስትና ትምህርት መሠረት ላይ እምነቱን እንዲተክል ማድረግ ይገባል እንጂ እምነቱን በሥነ አመክንዮው ልክ አድርጎ እንዲያስብ የሚያደርግ በር መክፈት ተገቢ አይደለም።

ለምሳል "ፍጥረት ኹሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ" የሚል ንባብ ያየ ሰው ኦርቶዶክሶች ቅድስት ድንግል ማርያም ያመልኳታል ከሚለው ቀድሞ በንጹሕ ልቡና አረዳዱን ይፈልጋል። አይ ይሄ ንባቡ ጸነን ይላልና ይውጣ ቢባል፤ ይህን አካሄድ የለመደ ሰው ምን ሊኾን ይችላል? ደረቅ ንባብ እያየ መልእክቱን ከመፈለግ ይልቅ ይጸናልና ይውጣ ወይም አልቀበልም ወደ ማለት አይወርድምን? እነ መርቅያንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ቆነጻጽለው የሉቃስ ወንጌል ላይ ወስዶ የጣላቸው፣ እነ ሉተርን በሕሊናዬ ውስጥ ካለው ሐሳብ ጋር ይጋጫል ብሎ ከማሰብ የተነሣ የያዕቆብን መልእክት ገለባ መልእክት ለማለት የዳረገው ምን ኾኖ ኖሯል? ሌሎች ብዙ መናፍቃን እስካኹን ድረስ ውጭ አውጥቶ የጣላቸው ምንድን ነው? በራሳቸው ልክ መጥነው ማሰባቸውና የራሳቸውን አረዳድ እንዳለቀለት እውነት ማቅረባቸው አይደለምን?

ሊቁ አባ ጀሮም "መርቅያንና ባሲሊድስ፣ እና ሌሎችም መናፍቃን ኹሉ... የእግዚአብሔርን ወንጌል ገንዘብ አላደረጉም። ... ወንጌል ማለት ትርጒሙ (ሐሳቡ፣ መልእክቱ) ነው እንጂ ገጸ ንባቡ ነው ብለን አናስብም፤ በውጫዊ ቆዳው ሳይኾን በውስጣዊ ይዘቱ፣ በስብከቱ ቅጠሎቹ ላይ ሳይኾን በትርጒም ሥሩ ነው እንጂ። በዚህ ኹኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያነቡትና ለሚሰሙት በእውነት የሚጠቅማቸው የሚኾነው ያለ ክርስቶስ የማይነገር ሲኾን ነው፥ ከአባቶች አስተምህሮና አረዳድ ሳይለይ የቀረበ ሲኾን ነው፥ የሚሰብኩት ሰዎች ያለ መንፈስ ቅዱስ የማይናገሩ ሲኾኑ ነው። ... የክርስቶስን ወንጌል በተጣመመ አተረጓጎም የሰዎች ወንጌል እንዳናደርግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ ጥንቃቄ መናገር ታላቅ አደጋ አለው።" እንዲል። (in Galat, I, 1. II. M.L. XXVI, c. 386) (ያረጋል አበጋዝ (ዲያቆን)፣ መድሎተ ጽድቅ ቅጽ 2፣ 2013 ዓም፣ ገጽ 176)። እንግዲህ አዋልድ መጻሕፍት የዐሥራው መጻሕፍት ልጆች ናቸው ካልን ልጅ አባቱን በሚመስልበት መንገድ እናየዋለን እንጂ በደረቁ ስሕተት ይገኝባቸዋልና እያልን ባላወቅነው ኹሉ በድፍረት መናገር ድፍረትም አለፈ ሲልም ነውርም ነው።

የአንድን ሰው አረዳዱን ኦርቶዶክሳዊ እስካላደረግነው ድረስ ምንም ያህል ዝቅ ብንል ላይረዳ ይችላል። ከዚያ ይልቅ ራሱን ብቁ ገምጋሚና አስተካካይ፤ የሃይማኖታዊ ጉዳይ ሚዛን በማድረግ ስሕተት ውስጥ እንዳይወድቅ ልንጠነቀቅለት ይገባል። መሠረታዊውን አስተምህሮ የተረዳ ነው፤ ምንም ነገር አያናውጸውም። የተኛውንም ንባብ ከወንጌል እውነታ አንጻር ነው የሚያየው እንጂ በውስጡ ባለ ምናባዊ ሥዕል ችግር አይፈጥርም። አምላክ ሰው ኾነ የሚለው እኛን የማይረብሸን ሙስሊሞችን ግን ለመቀበል የሚከብዳቸው በእነርሱ መጠን ውስጥ አድርገው ስለሚያስቡት ነው። የማስረጃ ዓይነት ቢጠቀስላቸው እንደ ተረት የሚቆጥሩት የተዘጋ አረዳድ ስላለ ነው። ይህን ዝግ የኾነ አረዳድ ካልከፈትንላቸው ነጻ ሊወጡ አይችሉም። ልክ እንዲሁም የኑፋቄ ዝናም ዘንቦባቸው፣ የክሕደት ጎርፍ ውስዷቸው ከእውነተኛው በረት ውጭ የነበሩ አካላትም መጀመሪያ ማጥራት ያለባቸው አረዳዳቸውን ነው። ንባብ ላይ ብቻ እየሄዱ መለጠፍን ማቆም አለባቸው። "ንባብ ይቀትል ወትርጓሜ የሐዩ ሕይወተ" ንባብ ይገድላል ትርጓሜ ሕይወትን ይሰጣል የሚለውን ልብ ይበሉት።

ይህን አካሄድ ትተን ይህን አልቀበልም ይውጣ ይጸናል ዓይነት አካሄድ ከጀመርን ለኔ የሚታየኝ መርቅያን ነው። ጌታችን "በኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል፤ ከእኔም የሚበልጥ ያደርጋል" ሲል ስናነብ ይህ በጣም ይጸናል፤ ተገላበጠ እኮ! ፍጡር ፈጣሪ የሚያደርገን እንዴት ያደርጋል? ከዚያም ብሶ ፈጣሪ ከሚያደርገው በላይ ያደርጋል ይባላልን? ኧረ ይሄስ ይውጣ ሊባል ነውን? "ሰላምን ላመጣ የመጣው አይምሰላችሁ ሰይፍን እንጂ" ሲል ስናነብ እንዴ ጨካኝ ነው ማለት ነውን? ይህን እንዴት ያደርጋል ልንል ነውን? "ከኔ አብ ይበልጣል" ሲል ታዲያ ከአብ የሚያንስ ከኾነ እንዴት ልናመልከው እንችላለን? ይህ ንባብ ያሰናክላልና በሌላ ግልጽ ንባብ ይቀየርልን ልንል ነውን? ጌታ በወንጌል "ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጧቸው በፊቴም እረዱአቸው" ሉቃ 19፥27 ስላለ ግድያን እየበረታታ ነውና ይህ ምንባብ ይውጣ ይባላልን?
መዝ 136፥9 "ሕፃናቶችሽን በዓለት ላይ የሚፈጠፍጥ ብፁዕ ነው" ይላል። ይህ ንባብ ጸነን ያለ ነውና ለመረዳት ስለሚያስቸግር ይውጣ ሊባል ነውን? "ኀጥእ የጻድቅ ቤዛ ነው፤ በደለኛም የቅን ሰው ቤዛ ነው፡፡" ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ ምሳ 21፡18፡፡ ኀጥእ እንዴት የጻድቅ ቤዛ ነው ይባላል? ስንኳንስ ኀጥእ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ጻድቃን ስንኳን ቤዛ አይባል ይሉ የነበሩ ይህን ንባብ እንዴት ሊቀበሉ ይችላሉ? እንግዲህ እንዲህ እያልን ከሄድን የሚቀረን ምንድን ነው? የምንደርሰውስ ወዴት ነው? ስለዚህ ጭንቀታችን መኾን ያለበት ንባብ ላይ ሳይኾን አረዳድ ላይ ነው ሊኾን የሚገባው።
ይህ ማለት ግን ደጋግሜ እንዳልኹት በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያሉን በሙሉ ከዳር እስከ ዳር ምንም ችግር ስለሌ ተቀበሉ ማለት አይደለም። እንዲህም ያለ የለም፤ ያልተባለን ነገር እንደ ተተባለ አድርጎ ማቅረብም Straw man Fallacy ነው። ማን ነው እንዲያ ያለው? ማንም እንዲያ ሊል አይችልም። ሌላው ቀርቶ አንድ በሌላ ቤተ እምነት የቆየ ሰው ኦርቶዶክስ መኾን ሲፈልግ በአእማደ ምሥጢራት አምኖ ተምሮ ምሥጢራትን ፈጽሞ አካል ይኾናል እንጂ አዋልድ መጻሕፍትን በአጠቃላይ ትቀበላለህ አትቀበልም እየተባለ አይጠየቅም፤ እንዲያ እንዲጠየቅ የሚያዝ ሕግም ሥርዓትም የለም። በሌለበትና ባልተባለው በድፍረትና በምንአለብኝነት "ገድላት ድርሳናትን አልቀበልም ማለት ትችላለህ ችግር የለውም ዓይነት አካሄድ ከየት የመጣ ነው?" የሌለ ነገር እየተባለ እንዴት ውዝግብ ይፈጠራል? ይህን አካሄድ ብንተወውና ትክክለኛ በኾነውን መንገድ ትምህርቱን በሥርዓቱ ብናቀርብ መልካም ነው። ሌሎችም ያላሰቡትን ጥያቄ እየፈጠርን ባናደክማቸው መልካም ነው። በአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ ስሕተት ሊኖር እንደሚችል ማሳያ በማቅረብ እንቋጭ።


አዋልድ መጻሕፍት እና አንዳንድ ስሕተቶች

1) የትርጒም ስሕተት ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ አንቀጸ ብርሃን ላይ

«ወኢያኀትዉ ፡ ውስቴታ ፡ ማኅቶተ ።»

በዛሬው ጥቆማዬ ለማሳየት የፈለኩትና በብዙ ቦታ ያገኘኹት የመጀመሪያው የትርጕም ግድፈት፥ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት በኾነው አንቀጸ ብርሃን ላይ ይገኛል። ክፍለ ጸሎቱም፥ በልሳነ ግእዝ፦ «አንቲ ፡ ውእቱ ፡ ተቅዋም ፡ ዘወርቅ ፡ ዘኢገብራ ፡ እደ ፡ ኬንያ ፡ ዘሰብእ ። ወኢያኀትዉ ፡ ውስቴታ ፡ ማኅቶተ ። አላ ፡ ለሊሁ ፡ ብርሃነ ፡ አብ ።» የሚለው ነው።

ትርጕሙም፦ «የብልኻተኛ እጅ ያልሠራት፣ በውስጧም መብራት የማያበሩባት የወርቅ መቅረዝ አንቺ [ማርያም] ነሽ። የአብ ብርሃን ይበራባታል እንጂ፤» ወይም፦ «የብልኻተኛ እጅ ያልሠራት የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ። በውስጧም መብራት አያበሩባትም። እርሱ የአብ ብርሃን ይበራባታል እንጂ፤» ማለት ነው።

በዚኽ ክፍለ ጸሎት፦ «የማያበሩባት» መባል የሚገባው ቃል፥ በብዙ መጻሕፍት፦ «የሚያበሩባት» ተብሎ ተተርጕሟል። ግእዙ፦ «ወኢያኀትዉ» እያለ፥ «የሚያበሩባት» ብሎ መተርጐም አለማስተዋል ነው። ከቃሉም ባሻገር፦ «አላ ለሊሁ ብርሃነ አብ» የሚለው ሐረግ ራሱ ትርጕሙን ያመላክታል። ምሥጢሩም፦ ‹መቅረዝ› በተባለች እመቤታችን ማርያም ላይ፥ የእግዚአብሔር አብ ብርሃን [ወልድ] እንደሚበራባት እንጂ ሌላ መብራት እንደማያስፈልጋት ያጠይቃል። ‹የአብ ብርሃን› የተባለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነገር ግን ይኼን ምሥጢር በሚያፋልስ አገላለጽ፦ «የሚያበሩባት» ተብሎ ተተርጕሟል። (ኤፍሬም የኔሰው (ዲ/ን)፣ የትርጒም ግድፈቶች በጸሎት መጻሕፍት በሚል ካዘጋጀው ጽሑፍ የተወሰደ)

«ዘሠረፀ ፡ እምአብ ፡ ወእምወልድ ፡ ዘነሥአ ።»

በኀሙሱ ሰይፈ ሥላሴ፥ በግእዙ ጸሎት፦ «አአምን ፡ ሥልሰ ፡ በመንፈስ ፡ ቅዱስ ፡ ዘወፅአ ፡ እምአብ ፡ ወእምወልድ ፡ ዘነሥአ ፡ ከመ ፡ ይቀድሶ ፡ ለኵሉ ፡ ዐለም ።» የሚል ኀይለ ቃል አለ። ትርጕሙም፦ «ዐለሙን ኹሉ ይቀድሰው ዘንድ ከአብ በሠረፀ፣ ከወልድ በተሰጠ መንፈስ ቅዱስ አምናለኹ፤» ማለት ነው። እኔ ባየኋቸው አንዳንድ መጻሕፍት ላይ ግን፦ «.... ከአብ እና ከወልድ በሠረፀ (በወጣ) በመንፈስ ቅዱስ አምናለኹ፤» ተብሎ ተተርጕሟል። የዶግማ ተፋልሶን የሚያመጣ የተሳሳተ አተረጓጐም ነው። (ኤፍሬም የኔሰው (ዲ/ን)፣ የትርጒም ግድፈቶች በጸሎት መጻሕፍት በሚል ካዘጋጀው ጽሑፍ የተወሰደ)

-ግእዙ አንድ ባሕርይ የሚለውን ኹለት ባሕርይ ብለው መጽሐፈ ባሕርይ ላይ የተረጎሙት ንባብ አለ። ስሕተት ነው። ክሕደት ነውና።

- ንሕነሰ ነአምን ከመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኅቡራነ ህላዌ ወኅቡራነ መንግሥት ኅቡራነ ራእይ ወኅቡራነ መለኮት፦ እኛ ግን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ 'በአካል አንድ' በመለኮት አንድ እንደ ኾኑ ..." ይላል። በዚህ መንባብ ውስጥ ሥላሴ በአካል አንድ መኾናቸውን የሚገልጽ የለም። ይህ ዳኅፅ ነው። ጠማማ ልቡና ያለው ያነበበው እንደ ኾነ አባ ጊዮርጊስን ባላሉት እንዳሉት አድርጎ ሊናገር ይችል ይኾናል።
(ኅሩይ ኤርምያስ (መ/ር፣ ተርጓሚ)፣ 2001 ዓ.ም፣ ምዕራፍ ስድስት የጥምቀት ምንባብ፣ ገጽ 73)።

2) ሥርዋፅ ኾኖ የገቡ አሉ። ለምሳሌ፦

- በሚያዝያ 10 በሚነበበው ስንክሳር ላይ የተቀመጠው ‘“ወሰብአ ኢትዮጵያሰ ኢይሲሙ ሊቀ እማዕምራኒሆሙ’ /የኢትዮጵያ ሰዎች ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ/ የሚልን በ318ቱ ሊቃውንት የተነገረ አንቀጽ በመተላለፋቸውና በንጉሥ ሐርቤ ዘመን ጵጵስናን በመጠየቃቸው ምክንያት ድርቅ መቅሠፍት ሆኖ ወረደባቸው’ የሚል የሐሰት ታሪክ አንዱ ነው፡፡ ይህንን የውሸት ታሪክ ግብፃውያኑ ሆን ብለው ኢትዮጵያን ለማስፈራራት የጨመሩት አንቀጽ ቢሆንም የ318ቱ ሊቃውንትን ቃል የምታከብረዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ያለ ጥያቄ አምና ተቀብላው ኖራለች፡፡

የሚገርመው ግብፃውያኑ ይህንን የሐሰት ትርክት ሲጨምሩ ያበላሹት ሦስት መጻሕፍትን መሆኑ ነው፡፡ አንደኛው መጽሐፈ ስንክሳር ፣ ሁለተኛው ፍትሐ ነገሥት ሦስተኛው የኒቅያ ጉባኤ ድንጋጌ ነው፡፡ ይህንን ሥራ በወቅቱ ከነበሩት ጳጳስ ጋር ተስማምቶ የሠራው የፍትሐ ነገሥት አስተጋባኢ Safey Ibn Al-Assal (13 Ad) ነበረ፡፡ ይህንን ስኅተት የግንቦት 2009 ዓ.ም. ርክበ ካህናት ላይ የብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማን ቀደምት ጥናታዊ ጽሑፍ እንደማስረጃ በመጥቀስ ከስንክሳር እንዲወጣ ወስኖአል፡፡ በመጻሕፍት ላይ ‘በሊቃውንት ጉባኤ ታርሞና ተስተካክሎ የወጣ’ የሚል አንቀጽ በመጻሕፍት ላይ የምናገኘው ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ የኖረ አሠራር ስለሆነ ነው፡፡

የሚገርመው በእኛ ቤተ ክርስቲያን ይህ ውሳኔ ከመወሰኑና ከመታረሙ አስቀድሞ ግን የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ባሳተመችው የፍትሐ ነገሥት አዲስ ቅጂ ላይ ‘ይህንን የኢትዮጵያ ሰዎች ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ’ የሚል አንቀጽ ስኅተት መሆኑን በመግለጽ አብራ እንደሚከተለው ከእርማት ጋር አሳትማዋለች :-

‘The Ethiopians are not to have a Patriarch from their scientists or by their own choice alone because their patriarch should be under the hand (authority) of the one on the chair of Alexandria’ [This again is wrong, because the council of Nicea did not have any knowledge of Ethiopia which did not have a bishop at the council and did not have a bishop until St. Athanasius ordained Fremenatous for them after the council of Nicea]

‘ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው መካከል በራሳቸው ምርጫ ብቻ ፓትርያርክን ሊሾሙ አይገባቸውም፡፡ ምክንያቱም ፓትርያርካቸው በእስክንድርያ መንበር ሥልጣን ሥር መሆን ይገባዋል’ [ይህም ዳግመኛ ስኅተት ነው ፤ ምክንያቱም የኒቅያ ጉባኤ በጉባኤው ወቅት ጳጳስ ስላልነበራት ኢትዮጵያ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያም ቅዱስ አትናቴዎስ ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ ፍሬምናጦስን እስከሾመላት ድረስ ጳጳስ አልነበራትም] (Al Magmou Al-Safawy Le Ibn Al Assal – The Collection of
1
Church and Civil Laws, 13th Century A.D. page 6) (ሄኖክ ኃይሌ (ዲ/ን)፣ ተአምረ ማርያምና አንዳንድ ጉዳዮች)

- በራእየ ማርያም ውስጥ የዘረኝነት በሽታ የጸናበት አካል ያልኾነ ሥርዋጽ አስገብቷል። ራእየ ማርያም መጀመሪያ የተጻፈው በግሪክ ሲኾን ወደ ሀገራችን ከመምጣቱ በፊት ወደ ዐረብኛ ተተርጉሟል። ከ39 በላይ የራእየ ማርያም ቅጂዎች ይገኛሉ። ወደ አማርኛ የተተረጎሙ የ1961 የተስፋ ገብረ ሥላሴ ትርጉም ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ አላገኘኹትም ይላሉ። 1985 በተስፋ ገብረ ሥላሴ የተተረጎመ እና በ2007 በአክሱም ማተሚያ የተተረጎመ አመሳክረው ጥናት አቅርበዋል። (አምሳሉ ተፈራ (ቀሲስ፡ ዶ/ር)፣ ነቅዓ መጻሕፍት፣ 2011 ዓ.ም፣ ገጽ 294-302)

- "ማክሰኞና ሐሙስ እባብን የገደለ እንደ ዐርባ ቀን ሕፃን ይኾናል" የሚል ትምህርት የመጣው በደብረ አስቦ ለነበሩ ገዳማውያን ዋናዎቹ ፈተናዎች እባብና ዘንዶ ስለ ነበሩ ነው። በዚያ ዘመን ዕባቡንና ዘንዶውን መታገሥ፣ አልፎም ማጥፋት ጽናትን ማሳያ ነበርና። (ዳንኤል ክብረት፣ ኢትዮጵያዊው ሱራፊ፣ 2011 ዓ.ም፣ ገጽ 660፣ የግርጌ ማስታወሻ 1974)። ይህ አባባል በመጀመሪያ ቅጅ ላይ የለም፤ ሥርዋፅ ኾኖ የገባው ኋላ ነው። የገባው ግን ከላይ የተገለጸውን ሐሳብ ለማስጠበቅ ነበር። መናፍቃን ግን ይህን ለጥጠው "እባብን የገደለ ይጸድቃል" እያልን እንደ ኾነ ለማስቆጠር ይጥራሉ። ይህ ግን Straw man Fallacy (ያልተባለን ነገር እንደ ተባለ አድርጎ የማሰብ ስሕተት) ነው። ይህ አካሄድ ቅንነት የሌለው ጥላቻንና ማነወርን ማዕከል ያደረገ ስሑት አካሄድ ነው።

- በዚቅ ላይ ደግሞ "ኦ አምላክ መርቆሬዎስ ዘአሠርገውከ ሰማየ " የሚል ንባብ በሥርዋፅ ገብቶ መገኘቱን ልብ እንላለን። የተሐድሶ መናፍቃንም እንዲህ ብለን እንደማናምንና ይህ ሥርዋፅ እንደ ኾነ ቢረዱም የመስማት ፍላጎት የሌላቸውና እነርሱ የሚሉትን ብቻ እንድንቀበል የሚፈልጉ ስሑታን ስለ ነበሩ ያልኾኑ ነገሮችን ሲያራግቡ ተመልክተናል። ሌሎችም ይህን የመሰሉ ጉዳዮች ሊገኙ ይችላሉ። ያን ኦርቶዶክሳዊ በኾነ መንገድ በጉዳዩ ላይ በሥርዓትና በጥንቃቄ ጥናት ለሚያደርጉ በጉዳዩ ብዙ ለቆዩበት ለነ ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ዓይነት ለቀቅ ብናደርግ መልካም ነው። በኹሉ ነገር ላይ ራስን አዋቂ አድርጎ ያውም በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ንባብና ጥናት ሳያደርጉ ኦርቶዶክሳዊ ባልኾነ መንገድ አዋልድ መጻሕፍትን እያዩ ደረቅ ትችት ማቅረብ አግባብ አይደለም። ደረጃን እና አቅምን በመረዳት በማያውቁት ነገር በመሰለኝ ከማውራት እንቆጠብና ብዙ ዓመታትን በሥነ ድርሳናት ለቆዩት አካላት በአክብሮት ቦታውን ለቀቅ ብናደርግ መልካም ነው። በችኩልነትና በድርቅና የቤተ ክርስቲያን አረዳድ ኹሉ በኔ በር በኲል ሲያልፉ ነው የሚያገኙት ከሚያሰኝ አካሄድ ብንቆጠብ መልካም ነው።

የአዋልድ መጻሕፍት ምንነት፣ ዓይነት፣ ጥቅም ...! እንዳይሰፋ ትቼው እነሆ ይህን አቀረብኹላችሁ።

✍️ዲያቆን ዮሐንስ ጌታቸው እንደጻፈው
👍3🙏1
በሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ፶ አዳዲስ አማኞች በጥምቀት ከብረው የሥላሴ ልጅነት አገኙ።

የካቲት ፪/፳፻፲፯ ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ

በሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት በአናሌሞ ወረዳ ቤተ ክህነት በወጎ ወጌላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ፶ ኢ አማንያን በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የሀዲያና ስልጤ ፤ የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት ተጠምቀው የሥላሴን ልጅነት አግኝተዋል ።

በዕለቱም ብፁዕነታቸውን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ንጉሤ ባወቀ ፣ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

©ብሕንሳ ሚዲያ
አንዳንድ ነገሮች (ከራሳችን ጋር ሆነን በጽሙና ብናስብባቸው)

1. ኑ*ፋ*ቄ (heresy) እና ስህተት (error) አንድ ናቸው? አንድ ካልሆኑስ ልዩነታቸውን እንዴት እንረዳዋለን? ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ውስጥ ለሁለቱም በምን ዓይነት ሁኔታ መልስ ስትሰጥ ኖረች?

2. አንድን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት "የቤተ ክርስቲያን ነው" የሚያስብለው ወይም "ይህ የሊቅ አስተያየት ብቻ ነው" የሚያሰኘው ምንድነው? ከዚህ አንጻር የተቀደሰው ትውፊት ድርሻ (ሥልጣን) እስከምን ድረስ ነው?

3. የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በአብነት ጉባኤያት መማር እና በነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች መማር የትምህርት አቀራረብ ስልት ነው ወይስ በራሱ "የትምህርት ይዘት" ነው? ስልት ከሆነስ "ፍጹም" የሚባል አቀራረብ አለ? ሁለቱም መንገዶች ለእንግዳ ትምህርት ያላቸው ተጋላጭነት ላይ ምን ዓይነት መረዳት መያዝ ይገባናል? አንድን ትምህርት "እንግዳ" የሚያሰኙት ነገሮች ምን ምን ናቸው?

4. ክርስቲያን ኹሉ ራሱን ከኑ*ፋ*ቄ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ሌላውን ከኑ*ፋ*ቄ የመጠበቅ ኃላፊነት የማነው? የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለዚህ ምን ይለናል? ማነው መልስ የሚሰጠው?

5. ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች እርስ በእርስ ስለ እምነታቸው የሚወያዩበት "ስሜት"፤ ክርስቲያኖች ከሌላ ቤተ እምነት ሰዎች ጋር ስለ እምነት ከሚነጋገሩበት "ስሜት" ጋር አንድ መሆን ይገባዋል?

✍️ዲያቆን ሚኪያስ አስረስ እንደጻፈው
👍41
👍2
አክሲማሮስ ዘ ቅዱስ ባስልዮስ
በአርባምንጭ ከተማ የጥምቀት ክብረ በዓልን ምክንያት አድርገው በታቦት ላይ ሲሳለቁ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል
***

የ2017 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን ምክንያት አድርገው በቃልኪዳኑ ታቦት ላይ የስላቅ ቪዲዮ በመስራት በእምነት ላይ ለማሾፍ የሞከሩ ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ጥፋተኞቹ የሚገባቸውን ያህል ትክክለኛ እና ሚዛናዊ ፍርድ እንዲያገኙ ሊሰራ ይገባል።

ይህን ተግባር የፈጸሙት አካላት በወፍጮ ቤት ውስጥ የጉልበት እና የቀን ሥራ የሚሰሩ ሲሆን ከልጆች ጀርባ ሆኖ የሚዘውረው እጄታ የማን እንደሆነ የምናጣራ ይሆናል።

የጸጥታ አካለትም ጉዳዩን ይዘው ውጤቱን ለህዝብ ይፋ የማድረግ ግዴታ አለባችሁ!!!ክብር የማይታለፍ መስመር ነው። ይኼ አርባምንጭ ነው። ተከባብረን አብረን ልንኖር ብቻ የተስማማንባት ከተማ ናት።

@Kune Demelash kassaye -Arba Minch
👍1
2025/09/01 00:41:27
Back to Top
HTML Embed Code: