Telegram Web
እመቤታችን ጥንተ አብሶ የለባትም!!!

አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኃጢያት (ጥንተ አብሶ ያላገኛት)፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት፣ ከመውለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች፣ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ ሀሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች፣ከተለዩ የተለየች፣ ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት። መኃ 4፥7 ምልዕተ ጸጋ፣ምልዕተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽ!ተብላ በመላእክት አንደበት በቅድስናዋ ትመሰገናለች
ሉቃ 1፥28-30።እመቤታችን በውስጥ በአፍአ
በነፍስ በሥጋ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል።

አምላክን ለመውለድ፣ ያስመረጣት፣ ያበቃት፣ ድንግልናዋ ንጽሕናዋ ነው። ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው።

እንዲያው ለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ (መንፈስ ቅዱስ ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጠበቃት) የሚለው ምንድን ነው? በሉቃ 1፥28-38 ያሉትን የቅዱስ ገብርኤል ብሥራታዊ ቃላት በኃላፊና በትንቢት የግስ ዐመላቸው በመዘርዘር የዐቀባን መሠረትነት ያስረግጣሉ። ጸጋን የተመላሽ ሆይ የሚለው ቃል በኃላፊ (past tense) እንጅ በትንቢት (future tense) አልተነገረም፣ ማለትም ወደፊት ጸጋን ይሞላብሻል፣ ከሴቶችም ሁሉ የተባረክሽ ትሆኛለሽ አላላትም። እንደገና መልአኩ በሰላምታው መደንገጧን አይቶ ማርያም ሆይ
በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻል አትፍሪ
አላት። አሁንም የመላአኩ ማረጋጊያ ዐረፍተ ነገር ኃላፊ እንጅ ትንቢት አይደለም፣ አግኝተሻል
አላት እንጅ ወደፊት ታገኛለሽ አላላትም። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ከመፀነሷ በፊት ወይም ወደዚህ ዓለም ከመምጣቷ በፊት ጀምሮ መርገመ ሥጋ፣ መርገመ ነፍስ ያልነበረባት መሆኑን ያሳያል።
ኤርምያስን በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሸሃለሁ ኤር1፥5 ሲል ለነቢይነት ለመረጠው ኤርምያስ ይህን ያህል ክብር የሰጠ አምላክ ለእናትነት የመረጣትን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ አንጽቶ ቀድሶ ለመጠበቅ ምን ይሳነዋል?
ከቅዳሴ ማርያም ንጽሕናሽን ባወቀ ጌዜ መልአኩን ላከ አለ እንጅ ሊያነጻሽ መልአኩን ላከ አላለም።ቅዱስ ኤራቅሊስ በሃይማኖት አበው የዮሴፍ የእመቤታችን ንጽሕና አለመረዳት ሲገልጽ "ከንጹሕ ዘር የተፈጠረች
ድንግል የእግዚአብሔር ማደሪያ እንድትሆን
አላወቀም።ቅዱስ ቄርሎስ በሥጋ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም፣ከአብርሃም፣ከዳዊት፣ከተገኘ ባሕሪይም ኃጢያት የሌለበት በነፍስ በሥጋም
ፍጹም የሆነ አካልን ሊዋሐደው ፈጠረ እንደሚል በመጥቀስ የእመቤታችን ንጽሕና ጥንቱን በማኅፀነ ሀና ስትፈጠር ከጽንሰቷ ጀምሮ እንጂ ከመልአኩ ብሥራት ወዲህ እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ለእናትነት የመረጣት ማደሪያውን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ከኃጢያት፣ከርኩሰት ከእድፈት፣ሁሉ ጠብቋታል።የሰው ልጆች የተያዙበት በአዳም በደል ወይም በራሳቸው በደል ምክኒያት የረከሱበት የኃጢያት ቅሬት መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የለባትም አላገኛትም።ምክኒያቱም እርሱ ለራሱ ማደሪያ
አድርጎ ስለመረጣት ነው።
እመቤታችን ቅድመ ዓለም በአምላክ ኅሊና ታስባ የኖረች፣የአዳም ኃጢያት ያልነካት፣ለአዳም ድኅነት ምክኒያት የሆነች፣ንጽሕተ ንጹሐን፣ቅድስተ ቅዱሳን፣በመሆኗ በሥጋም በነፍስም ፍጽምት
ትባላለች።ፍጽምት ማለት እንከን እና ጉድለት
የሌለበት ማለት ነው።ስለዚህ ቅድስት ድንግል
ማርያም የአዳም ኃጢያት የሌለባት በሥጋም
በነፍስም ንጽሕት በመሆንዋ መንፈስ ቅዱስ
ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ያ!በዘር የሚተላለፍ የመጀመሪያ በደል ፣ጥፋት ወደርሷ እንዳይተላለፍ ጠብቋታል።ሉቃ 1፥28፤መኃ 4፥12።
© መ/ር ፍሬው እውነቱ።
4👍1
ቅዱስ ላሊበላ ቤ/ክ እግድ አወጣ
👍1
#ስለ_ወንድማችን_አክሊል_አንዳንድ_ነገሮች!

በመጀመሪያ አክሊልን ያወኩት በቲክቶክ ሲያስተምርና ለመ*ና*ፍ*ቃን መልስ ሲሰጥ ነው። በዚህ ረገድ በጣም የሚበረታታ ሥራን ሠርቷል፤ እየሠራም ይገኛል። በሚያቀርባቸው የሃይማኖት ትምህርቶች በቲክቶክ የሚከታተሉትን በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ ብዙ ምእመናንን አጽንቷል፤ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲረዱ ረድቷቸዋል። ይህም ብቻ ሳይኾን በኑ*ፋ*ቄ እሳት የነደዱትን መ*ና*ፍ*ቃንንም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል፤ አሁንም እያበረከተ ይገኛል። ይህን አገልግሎቱን የተረዳ ሰው ይጸልይለታል፤ እግዚአብሔር ከክፉ እንዲጠብቀው ያስበዋል።

እንደሚታወቀው አንድ ሰው አንድ መልካም ሥራ ሊሠራ ሲነሣ ብዙ ፈተናዎች ሊገጥሙት እንደሚችል ግልጽ ነው። ይህ ፈተና በመጀመሪያ ከራስ የሚመነጭ ነው። ይኸውም ስለ ራስ ያለ ቦታና ደረጃ ለወጥ እያለ የመሄድ ፈተና ቀዳሚው ነው። ይህ በእንዲህ ዓይነት ትጉህ አገልግሎት ላይ ባሉ ኹሉም ላይ ማለት እስኪቻል ድረስ የሚመጣ ፈተና ነው። ይህን ፈተና ተፈታኞቹ አንዳንዴ ላይረዱት ኹሉ ይችላሉ፤ አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ ይህ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በምናቀርበው ነገር የተደሰቱ አካላት የሚያቀርቡልን ገነን ያለ ምስጋናና አክብሮት ሌላው የሕይወት ፈተና ይኾናል። ከእነዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ የበጎ ነገር ኹሉ ጠላት የኾነ ሰይጣን የሚያመጣብን ሰወር ያለ ወይም ግልጽ የኾነ ፈተና ይኖራል። ይህን መረዳት ተገቢ ነው። እንግዲህ ይህን በአጭሩም ቢኾንም ከግምት ውስጥ በማስገባት በአገልግሎት ላይ ላሉ ወንድሞቻችን ልንጸልይና ከእኛ እንደ ክርስቲያን የሚጠበቅብንን ልናደርግ ይገባል።

ኹለተኛው ነጥቤ - የወንድሜን አኬን አካሄድ ማዕከል ያደረገ ይኾናል። ይኸውም በአንድ በኩል አንድን ነገር ለማስረዳት የሚገልጽበት መንገድ ጸነን ማለት ሲኾን በሌላ በኩል ተደጋጋሚ ጊዜ ያቀረባቸውን የስሕተት ትምህርቶችን የሚመለከት ነው። እኔ ከእርሱ ጋር በአካል በተደጋጋሚ ጊዜ ባወራን ጊዜ ያገኘኹትና እንደ ወንድም ደጋግሜ መክሬው ግን እስካሁን አቋም አድርጎ የያዛቸው የስሕተት ትምህርቶችን በቅደም ተከተል ላስቀምጥ፦

1) ነገረ ክርስቶስን በተመለከተ ያቀረበው ስሕተት ነው።
ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው ወራት አብን አምልኳል የሚለው አንደኛው ሲኾን ሌላኛው ካረገም በኋላ አኹን አብን ያመልካል ብዬ አምናለሁ ብሎኛል። ይህን በተመለከተ እጅግ ስላስደነገጠኝ በጣም ለምኜዋለሁኝ። እባክህን ይህ ክሕደት ነው ተስተካከል ብዬዋለሁኝ በጓደኞቹ ፊት በጉዳዩ የምችለውን ኹሉ ለማለት ሞክሬያለሁኝ። እርሱ ግን ሚዲያ ላይ ከእንግዲህ ወዲህ አላነሣውም ቢኾንም ግን አቋሜ ነው ብሎኝ ነበር። ለዚህ ስሕተት መነሻ ያደረገውም ዮሐ 4፥21-22 ላይ ቅዱስ ቄርሎስ ያብራራውን እና አምብሮስ ዘሚላን ያለውን ነበር። በአቅሜ ለማስረዳት ሞክሬ ነበር። ያልኩትን አሁን አሻሽሎት ከኾነ ተመስገን ነው የምለው። ካልሆነ ግን በፍቅርና ክርስቲያናዊ በኾነ መንገድ እንዲያስተካክል ተማኅጽኖዬን በትሕትና በአደባባይ አቀርባለሁኝ።

2) ለኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋሕዶ በኋላ አብ አምላኩ ነው የሚል አንዲት አጠር ያለች ቪዲዮ ሠርቶ ያ ቪዲዮ በብዙዎች ዘንድ ውዝግብን ፈጥሮ እንደ ነበር አስተውሳለኹኝ። ሙስሊሞችም አኬ ማለት ባልፈለገው መንገድ አጣመው ሲያራግቡት ነበር። ወንድማዊ በኾነ መንገድ በተደጋጋሚ ይህንም ጉዳይ በተመለከተ አውርተናል። ቪዲዮውንም እንዲያጠፋ ጽኑ ልመናዬን ከተግሣጽ ጋር በአካል አቅርቤለታለሁኝ። ኋላ ሌሎች መምህራንም ኾነን ተሰብስበን መክረነው ያን ቪዲዮ እንዳጠፋ ነግሮኝ ነበር። አቋሙ ግን እንደ ጸና ቀጥሏል። አብ ለኢየሱስ ከተዋሕዶ በኋላም አምላኩ ነው ማለት ምን ማለት ነው? ሥግው ቃል አንድ ከኾነና ሥጋን በመዋሐዱ ምክንያት ሥግው ቃል ፍጡር ነው የማይባል ከኾነ እንዴት ለሥግው ቃል አብ አምላኩ ሊባል ይችላል? በመጻሕፍት አምላኩ የተባለውን በጥንቃቄ ኾነን ቃል የተዋሐደው ሥጋ ፍጡር መኾኑንና ከተዋሕዶም በኋላ ያ ሥጋ አለመለወጡን ለማስረዳት መኾኑን እንገልጻለን እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ ቃል የተለየው ዕሩቀ መለኮት የኾነ ሥጋ እንዳለ አድርገን አናምንም።

ወንድሜ አክሊል ግን "ቃል የተዋሐደው ሥጋ ስላልተለወጠ አሁንም ያንሳል" ብሎ እንደሚያምን ነግሮኝ ነበር። አምላኬም ያለው በሥጋው ነው፤ ሥጋው ያንሣልና ብሎኝ ነበር። ይህ ደግሞ ምንታዌ ነው። ሥጋ ምንም እንኳን ፍጡርነቱን ባይለቅም ከተዋሕዶ በኋላ ከቃል ስለማይለይ ያንሣል አይባልም። ያንሣል የሚለውን ስሑት ትምህርት አባቶቻችን አውግዘዋል። አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር፤ ሊቃውንት በመዝገበ ሃይማኖት ይህ ትምህርት የልዮናውያን እንደ ኾነና በኛ ዘንድ ተቀባይነት እንደ ሌለው አንሥተዋል። ሥጋው ያንሣል ማለት በአንድ በኩል ከመለኮቱ ተለይቷል የሚያሰኝ ሲኾን በሌላ በኩል ያመልካል እንጂ አይመለክም የሚያሰኝ ነው። ይህ ደግሞ ተቀባይነት የለውም። በቀጥታ ምንታዌን የሚያስረዳ ነውና ይልቅስ በአበው ትምህርት ያለው ሥጋ ያለመለያየት በተዋሕዶ ከቃል ጋር አንድ ስለ ኾነ ይመለካል የሚል ነው።

3) ከመ*ና*ፍ*ቃን ጋር ሲወያይ "ለሥግው ቃል አንድ ፈቃድ እንዳለው ነገር ግን የሥጋ ፈቃድ ለመለኮት ፈቃድ ለዘላለም ሲገዛ እንደሚኖር" በተደጋጋሚ ጊዜ አንሥቶ ስምቼዋለሁኝ። ይህም የምሥራቅ ኦርቶዶክሶች ትምህርት ነው። እነርሱ ኹለት ፈቃድ አለ፤ አንዱ ገዥ (የመለኮት ፈቃድ) ሌላኛው ተገዥ (የትስብእት ፈቃድ) ብለው ያምናሉ። መነሻቸው የባሕርይ ተዋሕዶ ስለሌለ ከኹለት ባሕርይ ኹለት ፈቃድና ኹለት ግብር ይመነጫል የሚል አቋም ስላላቸው እንዲያ ብለው ያምናሉ። እኛ ግን ከኹለት ፈቃድ የተገኘ አንድ ፈቃድ ብለን ስለምናምን በሥግው ቃል ውስጥ የምንከፋፍለው ፈቃድ የለም። ፈቃዱ ከኹለት የተገኘ አንድ ነው። ይሄ የመለኮት ይህ ደግሞ የትስብእት ተብሎ ተለያይቶ ፈጽሞ አይነገርም። ይህን አድማሱ ጀንበሬና በመድሎተ አሚን፤ አለቃ አያሌው መች ተለመደና ከተኩላ ዝምድና በሚል መጽሐፋቸው አንሥተውታል። አንዳንድ ቅዱሳን ሊቃውንት በጥንቃቄ የሥጋ ፈቃድ እንዳልጠፋ ለማስረዳት ያነሡት እንጂ እንደ ኬልቄዶናውያን ከፋፍሎ አንዱ ገዥ ሌላው ተገዥ በሚያሰኝ መንገድ እንድንረዳ ለማድረግ ፈጽሞ አይደለም።

4) "ቃል የተዋሐደው የጎሠቆለ ሰውነትን ነው" ብሎ አውርተንበት ነበር። ይህን የሚመስል አገላለጽ ያቀረቡ ሊቃውንትን ሐሳብ እንዴት መረዳት እንዳለብን አስረድቼው በጊዜው ከዲያቆን ብርሃኑ አድማስም ጋር እንዲያወሩ አድርጌ መ/ር ብርሃኑ በዚህ እና በእመቤታችን ጉዳይ (የጎሠቆለ ሰውነትን ለብሳለች አልለበሰችም በሚለው) ጽሑፍ ጽፎ በቴሌግራም ልኮለት ነበር። እኔም ከመ/ር ብርሃኑ አስቀድሜ ተው አክሊል አካሄድህ ጥሩ አይደለም ብዬ ረዘም ያለ የማብራሪያ ጽሑፍ ከዓመት ከስድስት ወር በፊት ልኬለት ነበር፤ በተጨማሪ መምህር ግርማ ባቱን ጉዳዩን ነግሬያቸው ተገናኝተው እንዲነጋገሩ አሳስቤ የላኩለትንም ጽሑፍ ለመምህር ግርማ አያይዤ ልኬ አሳይቼው ነበር። ወንድሜ አክሊል ግን እስካሁን ከአቋሙ አልተንቀሳቀሰም።
ሌላውን ለጊዜው እንተውና እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ ትምህርቶች ላይ ስሕተት ተፈጥሯል። እነዚህን ስሕተቶች ቢያርም መልካም ነው። እግዚአብሔር ወንድማችንን ከክፉ ነገር ኹሉ ይጠብቅልን። እንዲህ ዓይነት ስሕተቶችንም እንዲያርም እግዚአብሔር ኃይሉን ያድልልን። ምናልባትም አሁን ላይ እነዚህን ስሕተቶቹን አርሟቸውም ሊኾን ይችላል። ከኾነም እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው። እንዲህ አላልኩም ቢል እንኳን ደስታዬ ወደር የለውም። ዋናው ጉዳይ መስተካከሉ ነውና። አኹንም አቋም ኾኖ የተያዘ ከኾነ ግን ትልቅ ችግር ነው። ወንድም እኅቶቻችን ሆይ በአገልግሎት ተሠማርተን ላለነው ለኹላችንም ከወደዳችሁን ከልብ ጸልዩልን፤ ክፉ ሰይጣን ቀስ አድርጎ እንዳይጥለንና እንዳያጠፋን የእውነት የኾነ ልባዊ ጸሎት ያስፈልገናልና። ፍቅራችሁን እኛን ሊያድንና ሊጠቅመን በሚችል መንገድ ግለጹ እንጂ ሊጎዳን በሚችል መንገድ አታድርጉት።

ቸር ሰንብቱ!
✍️ዲያቆን ዮሐንስ ጌታቸው እንደጻፈው
👍5
ስለ ሃይማኖታዊ ውይይት አንዳንድ ነገሮች

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያው ሃይማኖታዊ ክርክሮች በረከት እያሉ መጥተዋል። እነርሱን ተከትሎ ደግሞ በአንድ ቤት ውስጥ ባሉትም መካከል ውይይቶች አለፍ ሲልም መነቃቀፎች አንዳንድ ጊዜም ደግሞ በእወቀትም ይሁን ያለዕውቀት መጠላለፍ የሚመስሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ይታያል። በእንዲህ ያለው ጊዜ ማድረግ የሚገባን ምንድን ነው የሚሉ ድምፆችም ይሰማሉ። የምናደርገው ነገር በዚህ ጊዜ በዚያ ጊዜ የሚባልበት መሆኑ ባይቀርም በእኔ እምነት በአግባቡ ከተጠቀምንበት እና ከተማርንበት ከሁሉም ልንጠቀም እና መንገዳችንን ትክክል የሆነልን እርሱኑ ልናጸና ፈንገጥ ያልነው ወይም የመንገድ ጠርዝ በመርገጥ የተንሸራተትን ካለንም ልንመለስ እና በመሐል መንገድ እንድንጓዝ ሊጠቅመን ይችላል። እጅግ በትንሹ ከሰማኋቸው ተነሥቼ አጠቃላይ መርሕ ተኮር ሁኔታዎች በዚህ ጽሑፍ ልጠቁምና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ በመከራከሪያ ነጥቦቹም ላይ ላክል እችላለሁ። ከዚህ በፊት “አድማሱ ጀንበሬ ሕይወቱ እና ትምህርቱ” የሚለው መጽሐፍ ሲታተም በመቅድምነት የወጣ አጭር ጽሑፍ ላይ ከንባቦቼ ከቀራረምኩት የተወሰኑ ሀሳቦችን ማጋራቴ ይታወቃል። እነዚያን ያላየ ቢያያቸው አንድ ነገር እንኳ የሚጠቅም ሊያገኝ ይችላል ብዬ አምናለሁ። እነዚያን ያነሣሁበት ምክንያት ግን እነዚህን ጉዳዮች የእነዚያ ቀጣይ አድርጋችሁ እንድትወስዷቸው ለማሳሰብ ያህል ነው።

በውይይትም ሆነ በክርክር ውስጥ ያለን አገልጋዮች ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡን ጉዳዮች መካከል

1) በራስ ማስተዋል አለመደገፍ

በመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱስ ከተጻፉት ታሪኮች፣ ምክሮች እና ትርጓሜዎች መካከል አንደኛው በራሳቸን መረዳት፣ ማስተዋል (reasoning) ላይ እንዳንደገፍ እና በዚህ ምክንያት ወደ ፈተና እናዳንገባ መጠበቅን የሚመለከት ነው። ለምሳሌ ያህል ያዕቆብ ከዔሳው ብኩርናውን የወሰደበትን ሒደት ስንመለከተው በምንም ዓይነት ተፈጥሮአዊ አመክንዮ ይሠራል ይሆናል ለማለት የሚቻል አይደለም። የአብርሃምና ሣራ እንዲሁም የዘካርያስ እና የኤልሳቤጥ በዕርጅና ልጅ መውለድ የሚያስተምረንም ይህንኑ ነው። ዋናው ጉዳይ ግን እግዚአብሔር እርሱ ባወቀ ኤሳው ቀድሞ እንዳይወለድ እና ያዕቆብ ቀድሞ እንዲወለድ ማድረግ እየቻለ ከተወለደ በኋላ በኩርናውን እንዲወስድ ለምን አደረገ? ለእነ አብርሃም እና ለእነ ዘካርያስ ልጆችን ቀድሞ ለምን አልሰጣቸውም ብለን ብንጠይቅ ዋናው መልስ እግዚአብሔር ሊያስተምረን የፈለገው ከተፈጥሮ ሕግ እና ከየትኛውም አመክንዮ ወይም የሰው የሕሊና መረዳት የሚያልፉ ነገሮችን የሚያደርግ መሆኑን ለማሳየት ነው። በመጽሐፍም “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤” /ምሳ 3 ፡ 5/ ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ነው።

በርግጥ ሃይማኖት የሚባለውም ይህ ነው። ከመረዳታችን እና ከሎጂካችን ባሻገር እግዚአብሔር የሠራውንና የሚሠራውን ማመን። ጌታችን ከእመቤታችን ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም የተጸነሰበት፣ የተወለደበት፣ የሞተበት፣ ድኅነታችን የፈጸመበት፣ የእመቤትችን በሁለንተና ንጽሕት መሆን እና የመሳሰሉትን ነገሮች መረዳት የሚቻለው ያዕቆብ ከዔሳው ብኩርናውን በወሰደበት መንገድ ብቻ ነው። ይህም ማለት ከሎጂክና ከአመክንዮ ተላልቅቆ እግዚአብሔር አምላክነቱን በየዘመኑ ትውልድ እግዚአብሔርነቱን የገለጸባቸውንና በአእምሮ ከመታሰብ፣ በሎጂክ ከመረዳት በላይ የሆኑትን በመቀበል ነው። ያዕቆብ ብኩርናን የወሰደበት መንገድ በእምነት የምንቀበለው ብቻ ነውና። እነዚህ ነገሮች የተፈጸሙት፣ እና በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡበት ዋና ዓላማም የአካላዊ ቃል ሰው መሆን ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች በሙሉ አስቀድመው የተዘጋጁ መልሶች እንዲሆኑ ነው።

በራስ ማስተዋል ወይም በራስ የመረዳት ችሎታ ላይ መደገፍ ቢያንስ ሁለት ታላላቅ ፈተናዎችን ወደ እኛ ያመጣል። የመጀመሪያው ከእምነት መጉደል ነው። ይህ ደግሞ እንኳን በእኔ ቢጤዎች ይቅርና ጻድቁ ዘካርያስንም ፈትኖታል። ዘካርያስ ቅዱስ ገብርኤልን የተከራከረው ዕውቀት ወይም የተፈጥሮ ሕግ ገድቦት ነውና። ሰው ካረጀ ካፈጀ በኋላ አይወልድም የሚለው ዕውቀቱ ወይም የተፈጥሮ ሕጉ ስሕተት ሆኖ አልነበረም። የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ግን ከእነዚህ የሚያልፍ ነበረ። ስለዚህ በመረዳት ወይንም በማስተዋላችን ላይ መደገፍ መጀመሪያ የሚያመጣው ፈተና እንኳን ሰዎች መላእክትም ቢናገሩን እንድንከራከር ሊያደርገን ይችላል ማለት ነው። ሌላው ቀርቶ ትናንት ያከበርነው የልደተ ስምዖን ታሪክ የሚያስታውሰንም ይህንኑ ገጠመኝ ነው። ሴት እንጂ ድንግል አትወልድም የሚል ሀሳብ ይዞ ድንግል ትጸንሳለች የሚለውን የነቢዩን የኢሳይያስን ቃል ሴት ወደሚል ለመቀየር ሞክሮ ከእግዚአብሔር ይህን ሳያይ እንዳይሞት የተረዳው የእግዚአብሔር አሠራር ከሰው ማስተዋል እና መረዳት ባሻገር ስለሆነ ነው። በዚህች መንገድ መጓዝ የጀመረ ሰው አይሁድ ከመስቀል ውረድና እንመንብህ እንዳሉት በራስ መረዳት ቅድመ ሁኔታ አስቀመጦ እግዚአብሔርን መፈተኑ የማይቀር ነው።

ሁለተኛው እና ከባዱ ፈተና ደግሞ ሌሎች ይህን መረዳት እንደማይችሉ በማሰብ የዲያብሎስ ረቂቅ ወጥመድ በሆነው የትዕቢት ወጥመድ ውስጥ መውደቅን ሊያስከትል ይችላል። ይህ ደግሞ ብዙ ጥፋቶችን አከታትሎ ያመጣብናል። ሰሎሞን “በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው፥ እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም” /ምሳ 16 ፡ 5/ ሲል እንደገለጸው ቅጣቱም ቀጥታ ከእግዚአብሔር ይሆናል። ለሰውየው ግን እያወቀ ወይንም እውቀቱ ትክክል ስለሆነ እንጂ እየታበየ እና እየተጎዳ እንደሆነ አይሰማውም። ለዚህም ነው “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” /ምሳ 16 ፡ 25/ ተብሎ የተጻፈው ። ስለዚህ ከሁለቱም ለመጠበቅ በራስ መረዳት ላይ አለመደገፍ ትልቁ መፍትሔ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እና ምክሮች ያረጋገጡልንም ይህንኑ ነው።

2) ከትዕቢት / ካለመሸነፍ መንፈስ መራቅ

የትዕቢት ነገር ከላይም የተጠቆመ ቢሆንም በዓለም ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ መሠረቱ ትዕቢት ነው። በተለይ በሰው ፊት ተሸናፊ መባልን፣ አያውቅም መባልን መፍራት፣ ተሳስቷል መባልን መሸሽ ወደ ማስረዳት እና ራስን ነጻ ለማውጣት ሲባል ወደ ተለጠጠ ክርክር ይስባል፣ ከዚያም ወደ ባሰው ችግር ወይም ፈተና ሊያደርስ ይችላል። ስለዚህ ጥያቄዎች ሲፈጠሩ ቆም ብሎ ማድመጥ ፣ መጸለይ እና ቅዱሳት መጻሕፍትን እያጠኑ ሊቃውንትን ደጋግሞ መጠየቅ ብዙ ችግሮችን ያስወግዳል። ይልቁንም ልሳሳት እችላለሁ በሚል ትሑት ሰብእና ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔርን የሚለምን ሰው እግዚአብሔር በፍጥነት ከዚህ ችግር እንደሚያወጣው የታመነ ነው።

3) የምንጮችን ዐውድ በአግባቡ ለመራዳት መጣር

ብዙ ጊዜ ወደ ክርክር ተይዘው የሚወጡት ምንጮች ወይም ማስረጃዎች በራሳቸው ምንም ችግር የለባቸውም። ሆኖም ከተነገሩበት ወይም ከተጻፉበት ዐውድ አውጥተን ከተመለከትናቸው ችግር ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ጥንተ አብሶን በተመለከተ የሚነሣው ክርክር ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። የጥንት ሊቃውንት ጌታ ሥጋውን ከሰማይ ይዞ ወርዷል፣ በእመቤታችን አደረባት እንጂ ሥጋን ከእርሷ አልነሣም ለሚሉ የዚያ ዘመን መና/ፍቃን የተሰጡ መልሶች ያንኑ የበደለውን ሰው የአዳምን ሥጋ ነው የተዋሐደ ሲሉ ያንን የሳተውን፣ የወደቀውን፣ የጎሰቆለውን የእዳም ሥጋ እንደተዋሐደ ተከራክረው አስረድተዋል። ሆኖም እነዚህ አገላለጾች እመቤታችንን ጥንተ አብሶ አለባት ሊያስብሉ አይችሉም። (ይህን ጉዳይ
👍2
እንደ ሁኔታው ለብቻው ልመለስበት እችላለሁ) በጣም የተለያዩ ሀሳቦች ናቸው። እንዲህ ያለው ችግር ቀደም ብሎም የነበረ ችግር ነው። ስለዚህ አሁንም ለመርታት በሚፈልግ ልቡና ውስጥ ሆኖ ጥቅሶችን ከዐውዳቸው ነጥሎ አውጥቶ መጠቀም ችግርን ያባብስ እንደሆን እንጂ መፍትሔ ሊሆን አይችልምና ከዚህም መጠበቅ ተገቢ ነው።

4) ከመጠራጠር አለመጀመር

መና/ፍቃን ሀሳብ እና ጥያቄ ሲያነሱ የእነርሱን አመክንዮ እና ፍረጃ ሰምቶ ነባር ትምህርቶችን ወይም ምንጮቻችን ከመጠራጠር መጀመር በጣም አደገኛ ነገር ነው። ለምሳሌ ሳጥናኤል እኔ ፈጠርኳችሁ ባለ ጊዜ በጥርጥር የጀመሩት እውነት በተገለጠ ጊዜ ከእርሱ ጋር አብረው ወድቀው የሚያስቱ መናፍስት ሆኑ እንጂ ሲመለሱ አላየናቸውም። እውነቱን ባያውቁም በያለንበት እንቁም ባለው በቅዱስ ገብር ኤል ቃል ጥርጥሩን ሳያስገቡ የጸኑት ግ ን በኋላ እግዚአብሔር እውነቱን ገልጾላቸዋል። ይህ የመጀመሪያው የፍጥረት ፈተና የሚያስረዳን ከመጠራጠር መጀመር ምን ያህል አደገኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን መንገዱ ዲያብሎሳዊ መሆኑን ነው። በሳይንስ ከመጠራጠር መጀመር ወደ ዕውቀት ይወስዳል ከሚባለው በተቃራኒ በሃይማኖት በመጠራጠር አለመጀመር መሠረታዊ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን ማለት ነው።

በዚሁ መንገድ ካየን አንዳንድ የግእዝ ምንጮቻችን ከሌላ ሀገር ምንጮች ስናነጻጽር በቀጥታ ላይገጥሙልን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ገድለ ጊዮርጊስን ስንመለከት ሰማዕቱን ያሰቃየውን ንጉሥ ዱድያኖስ ይለዋል። በሌላው ሀገር ግን ያሉት ምንጮች በሙሉ ደግሞ ንጉሡን ዲዮቅልጥያኖስ ይሉታል። ይህ በመሆኑ የእኛ ምንጭ ስሐተት ነው ልንል አንችልም። እኔ እንኳ በአቅሜ በአደረግሁት ፍለጋ አንድ ጥናት ላይ የጥንት ምንጮች ዱድያኖስ ይሉ እንደነበር አግኝቻለሁ። ስለዚህ ይህ ስም ምንጫችን ስሐተት መሆኑን ሳይሆን ምንጫችንን ወይም አቀባይ ቋንቋችንን እንድንመረምር እና የእኛ ቅጂ ከቀዳማውያን ምንጮች መሆኑን ይጠቁማል እንጂ ልዩ መሆኑ ስሕተት መሆኑን ሊያሳይ አይችልም ማለት ነው።

በገድለ ተክለ ሃይማኖት ላይ ያለው የሞቱበትን በሽታ እንደመስቀሌ እቆጥርልሃለሁ የሚለውን ሀሳብ ስሑታኑ ባነሡበት መንገድ ተመልክቶ ከመጠራጠር ከመጀመር ወደ ገድሉ ጠልቆ ገብቶ ምክንያቱን ከማጥናት መጀመር ከብዙ በሽታ ይፈውሳል። በዚሁ ጉዳይ ላይ ገድሉን ስንመለከት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ትልቁ ፍላጎታቸው የደም ሰማዕትነትን ማግኘት ነበር። ዘመኑ ደግሞ ያንን አልፈቀደላቸውም። ስለዚህ ጌታ በበሽታ የገጠማቸውን ተጋድሎ እንደ ሰማዕትነት ወይም መስቀል እንደሚቆጥርላቸው ቃልኪዳን ገባላቸው ይላል እንጂ መና/ፍቃኑ የሚሉትን ወይም ሊሉ የሚፈልጉትን ገድሉ በፍጹም አይልም።

በገድለ ቅዱሳንና በገድለ ቅዱሳን መጽሐፍ መካከል ልዩነት እንኳ ቢኖር ወደ ቀዳማይ ምንጭ በሚደረግ ጥናት ይስተካከላል እንጂ ገድለ ቅዱሳንን ወደ መጠራጠር ሊወስድ አይችልም። በርግጥ የሰው አእምሮ ውሱን ስለሆነ ለእንዲህ ያለ ፈተና ተደጋግሞ ሊወድቅ ይችላል። እንዲህ ያሉትን ነገሮች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስም ያስረዳል። ለምሳሌ ያህል በሰማርያ እጅ ከባድ ረሀብ ተነሥቶ ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን ቀቅለው ለመብላት ከተስማሙና የአንዲቱን ከበሉ በኋላ ሁለተኛ ልጇን ስትደብቅ በተፈጠረው ክርክር ንጉሡ ስሞቶ በኤልሣዕ ላይ ተቆጥቶ ነበር። በኋላ ላይ ግን “የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸመታል አለ። ንጉሡም በእጁ ተደግፎ የነበረ አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ፦ እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን? አለው። እርሱም፦ እነሆ፥ በዓይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም አለ” /2ኛ ነገ 7/ ተብሎ እንደተጻፈ ንጉሡ በመጠራጠሩ ምክንያት በሕይወቱ እንዲቀጣ ሆኗል። ስለዚህ ከመጠራጠር መጀመር ውጤቱ አደገኛ መሆኑን መረዳት እና በእምነት ጸንቶ የማያውቁትን ለማውቅ መጣር ተገቢነት ይኖረዋል ማለት ነው። ለዛሬው በእነዚሁ ልፈጸም። ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።

✍️መምህር ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ እንደጻፉት
4👍1
በሰሞኑ ጉዳይ
--
#የተደነቅሁባቸው
ከ‹‹ታማልዳለች አታማልድም›› የፌርማታ ነዋሪ ነባሪ ንትርክ ሻገር ያለ ሐሳብ ያነሣ አዲስ ትውልድ በማየቴ ደስ ብሎኛል፡፡ ምሥጢራት ላይ በመሠረታዊነት ደክመዋል፡፡ ‹‹አምስቱ ብቻዎች››ን የሚሞግቱበት መንገድ ደንቆኛል፡፡ የተዋሥኦ ባሕል አነቃቅተዋል፡፡ ያ ሜዳ የዝነኞችና የአርቲስቶች የብቻ ርስት እንዳይሆን እጃቸው አለበት፡፡ ስለ ቅዳሴ ስለ ጸሎት ሕይወት ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ መልካም ነው፡፡
--
#ቅሬታዬ
አቀራረብ ላይ አብዝተው ቀሊልና ዋዘኛ አቀራረብን ይከተላሉ፡፡ ለኦርቶዶክሳዊው አድማጭ የሌላ ቤት ዘዬ ተደርገው የሚወሰዱ ቋንቋዎችንና ዘይቤዎችን ይጠቀማሉ፡፡ መጽሐፍ ላይ ስለሌሉ አይደለም፡፡ ግን በቃ … ቃላቱ በአሉታ ተዛምደዋል፡፡ የሆነ ዓይነት sensitivity ያስፈልጋል፡፡ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ውሳኔውን ወደ መምህራን ማሳለፍ፣ ከዚያም የእነሱን ምላሽ ይዞ መቅረብ የተሻለ ነው፡፡ ቤቱ ‹‹ምስክር መምህራን›› የሚባሉ ሊቃውንት አሉበት፡፡ ገርበብ አድርጎ ማለፍም አንድ ነገር ነው፡፡ እንዲህ የሚል አለ፣ እንዲህም የሚል አለና በጋራ እንጠይቅ፣ አንብበን ጠይቀን እንገናኝ ብሎ ረዘም ያለ ቀጠሮ መውሰድም ፈሊጥ ነው፡፡ ግብግብ ይጎዳል፣ ልጅ ሲሆኑ ደግሞ መቀጨትም ያመጣል፡፡ እዚህ ላይ በማልጠብቀው መልኩ አንድን አከራካሪ ርእስ በራስ ሐሳብ ዙሪያ ብቻ በማሽከርከር ‹‹ግግም!›› ማለትን አያለሁ፡፡ ያደክማል! ጊዜ ይፍታው ብሎ ማሰለፍምኮ አለ፡፡ ኃፊረ ገጽ የተለየው ድርቅ ያለ የአደባባይ ድግግሞሽ አያንጽም፡፡ የኢኦተቤክ በትምህርተ ሃይማኖት ምንጭ ረገድ ያላት አብነትነት የአኃትን ማረጋገጫ የሚፈልግ የሚያስመስል ጥንቃቄ የጎደለው አቀራረብም ያስቆጣል፡፡ በዚህ ቅር ይለኛል፡፡
--
#ሌላው_ቅሬታዬ
በቀጥታም በተዘዋዋሪም የዕቅበተ እምነት ሥራ የቲዎሎጂና የአብነት መምህራን ሥራ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ መቅረቡ ትክክል ሆኖ አይታየኝም፡፡ ያለፉት ዓመታት ተጋድሎም ያንን አያሳይም፡፡ ካህናትም. ሰንበት ት/ቤቶችም፣ ማኅበራትም፣ ሰንበቴዎችም፣ ምዕመናን/ትም ድርሻ አላቸው፡፡ ባይሆን እንደ ሰሞኑ ዓይነት አካራካሪ የሆነ፣ ማብራሪያ የሚፈልግ፣ ትርጓሜ የሚያሻው ንባብ ሲገጥም የወንበር መምህራንን ማናገር ይገባል ቢባል የቀና ነው፡፡ እንደ እውነቱ አልፎ አልፎ ብቅ የሚለው ልጆቹ በጉባኤ አልዋሉም በሚል የሚሰነዝር ምሁራዊ ትምክሕት (Clericalism) የተጫነው አነጋገር የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፡፡ አሁንም በፍቅርና በርኅራኄ አቅርቦ መያዝንና ማረቅን ሳይሆን በ‹‹ብለን ነበር›› የታጀበ የኃይለ ቃል ውርወራችን ያስጨንቃል፡፡
--
#መውጫ
አሁንም ጊዜና ዕድል አለ፡፡ ንግግሮች በውስጥ ይቀጥሉ፡፡ የአሸናፊ ተሸናፊና የነጥብ ማስቆጠሪያ ቅኝቶች ይርገቡ፡፡ ሰብእና ተኮር ነቀፋዎች ይወገዱ፡፡ የተነሡት ርእሶች ወደ ጉባኤ መምህራን ይሄዱ፣ የእነሱ ቃል እስኪሰማ ያጨቃጨቁት አርእስት ከዲጂታል ሚዲያ ተዋሥኦ ዕረፍት ያግኙ፡፡ ሰሚዎች የሰማንበት መንገድና እነርሱ የሚያብራሩበት መንገድ መካከል ክፍተት ካለ ይፈተሽ፣ ያሉበትን ነጥብ ያብራሩ፡፡ ነጥቡ ይንጠር፡፡ በጉባኤ ቤት ሰዎች እልባት ይሰጥ፣ በዚያውም በፕላትፎርሙ ላይ በምን ርእስና እንዴት እንወያይ የሚለው ይታይ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አንዳችን ለሌላችን ጸሎት እናድርግ!

✍️በአማን ነጸረ እንደጻፈው
2
በቅዱሳት ገድላትና ድርሳናት ዙሪያ እንዲሁም በጥንተ አብሶ ዙሪያ

፩፦ እስካሁን በተመለከትኩት ገድላት አያስፈልጉም መወገድ አለባቸው የሚል ንግግርም ጽሑፍም ከኦርቶዶክሳውያን አልሰማሁም። ምክንያቱም ገድላትና ድርሳናት የወንጌል ትርጉሞች ናቸው። የቅዱሳን ሕይወት የሚታይ የሚዳሰስ የወንጌልን ቃል በተግባር የሚያሳይ ነውና።

፪፦ ነገር ግን በአንዳንድ ገድላትና ድርሳናት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ ስሕተቶች ሊገኝባቸው ይችላል። ይህ እንዳይፈጠር የሊቃውንት ጉባኤያችን ጠንክሮ ማዕከላዊ የቅዱሳት መጻሕፍት ኅትመት ቢኖረውና በዚያ ቢታተሙ መልካም ነው። ብሔርን ከብሔር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን የሚያስተላልፉ ሐሳቦች በግል በሚታተሙት ገድላት ይስተዋላል።

፫፦ ለምሳሌ ቡና ይጠጣል ወይስ አይጠጣም የሚለው ክርክር ምንጩ ገድልና ድርሳን ነው። ለምሳሌ እኔ ከአምስት የገድላትና የድርሳናት መጻሕፍት ቡና እንደማይጠጣ የሚገልጽ አግኝቻለሁ። በተማርኩባቸው ጉባኤ ቤቶችና በየትኛውም የመጻሕፍት ትርጓሜ ጉባኤ ቤት ቡና አይጠጣም የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት የለውም። ታዲያ ጉባኤ ቤቶች ይህንን ሐሳብ ቀጥታ የመቀበል ግዴታ አለባቸውን?

፬፦ ባለፈው መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚእ አሰፋ (የጠቅላይ ቤተክህነት የትምህርትና ሥልጠና ክፍል ኃላፊ) ማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በነበረው ሥልጠና እንደማሳያ ብለው ብዙ የተአምረ ማርያም ቅጅዎችን እንዳዩ ገልጸውልን ነበር። እና በአንዱ የብራና ተአምረ ማርያም ቅጂ አጼ ቴዎድሮስን እጅግ በጣም አክፋፍቶ የሚገልጽ እንዳገኙ ገልጸውልን ነበር። አስተውሉ በአንዱ ቅጂ ነው የተገኘ እንጂ በሁሉ አይደለም። ትክክልነቱ ምን ያህል ነው? የሚለው ጥናት ይጠይቃል።

፭፦ ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ ላይ ዮሐንስ አሥር ጊዜ ከተለያዩ እናቶችና አባቶች እንደተወለደ የሚገልጽ አግኝቻለሁ። ዮሐንስ መጀመሪያ የተወለደ ከአዳምና ከሔዋን ሲሆን ስሙም ያን ጊዜ "ሔና" ነበረ ይላል። ከዚያ በየዘመናቱ እየተወለደና መጨረሻ ላይ ከዘካርያስና ከኤልሳቤጥ ተወለደ ይላል። ይህ በአንድ ወቅት ደብረ ሊባኖስ ገዳም ግጭት ፈጥሮ ነበር። በወቅቱ በገዳሙ የነበሩት የንታ ብሩክ ይህ መስተካከል አለበት ሲሉ አንዳንድ ከመጻሕፍት ሩቅ የነበሩ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ስለሌለ እንዳለ እንቀበላለን አሉ። ነገሩ ግን ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር መመርመር አለበት። ይህ በአንዳንድ የገድለ ዮሐንስ መጥምቅ ቅጂዎች አይገኝም።

፮፦ ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ላይ እስከ ዕለተ ምጽአት የጎጃም ሕዝብ ይቅር እንደማይባል ይገልጻል። በሌሎች ገድሎችና ድርሳኖች ለምሳሌ በገድለ አቡነ ሰላማ፣ በድርሳነ ኡራኤል፣ በገድለ ተከሥተ ብርሃን፣ በገድለ አቡነ ዜና ማርቆስ ደግሞ እስከ ዕለተ ምጽአት ወልድ ዋሕድ በተዋሕዶ ከበረ ብለው እግዚአብሔርን የሚያመልኩና እግዚአብሔርም የሚወዳቸው በሃይማኖታቸውና በምግባራቸው የተመሰከረላቸው የጎጃም ሰዎች ናቸው ይላል። እና የትኛውን እንቀበለው? መመርመር አለበት። ራእየ ማርያም ላይ ሻን*ቅላ ለዘለዓለም እንደማይጸድቅ የሚናገር አለ። በእውነት ይህን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት የተናገረችው? ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር አይጋጭም?

፯፦ እንደዚህ እርስ በእርሱ የሚጋጩ ጉዳዮች ገድላት ላይና ድርሳናት ላይ ይስተዋላሉ። ይህ በተለያየ ምክንያት ነው። አንዳንድ መምህራን ሚሲዮናውያን ኢትዮጵያውያንን ለማለያየት ያስገቧቸው ናቸው ይላሉ። ይህ ሁሉ ቢሆንም ገድላትና ድርሳናት የሚታረሙት እየታረሙ በማዕከላዊነት በጠቅላይ ቤተክህነት ቢታተሙ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ይቻላል።

፰፦ በጥንተ አብሶ ዙሪያ ለምሳሌ ማኅበረ ቅዱሳን ባሳተመው ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በጻፉት መጽሐፍ የሰው ልጅ ከጥንተ አብሶ የሚላቀቅ ሲጠመቅ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ጥንተ አብሶ በክርስቶስ መሰቀል ተወግዷል። ከዚህ በኋላ ሰው ቢኮነን እንኳ ራሱ በሠራው ኃጢአት እንጂ በጥንተ አብሶ አይደለም ይላሉ። (በጉባኤ ቤቶች ያለው አስተምህሮ ይህኛው ነው። በክርስቶስ መስቀል የውርስ ኃጢአት ጠፍቷል የሚል ነው። የእኔም አቋም ይህ ነው)። ጥንተ አብሶ የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን የበደል መጀመሪያ ማለት ነው። ይኸውም አዳምና ሔዋን የሠሩት በደል ነው። ይህ በደል ለአዳምና ለሔዋን ብቻ ይነገራል። የእነርሱ የበደል ውጤት (መርገም) ከእነርሱ ወደሚወለዱት ልጆች ተላልፏል። ይህን ውጤቱን የውርስ ኃጢአት እንለዋለን። ቅድስት ድንግል ማርያም የውርስ ኃጢአት የለባትም። ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል እንዲል ከማኅፀን ጀምሮ ራሱ እግዚአብሔር ጠብቋታልና።

፱፦ በሚዲያ ዞር ዞር ስል ሕዝቤ ለሁለት ተቧድኖ ይቧቀሳል። በሁለቱም ወገን ያለው በእመቤታችን ንጽሕናና ቅድስና ይስማማል። ጠቡ በቃላት ያለመግባባት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሁሉም ጽንፍ ይዞ የአንዱ ደጋፊና የአንዱ ነቃፊ ሆኖ በየራሱ ትርጉም ክፉ ስም ይሰጣጣል እንጂ ቆም ብሎ አንዱ አንዱን ለማዳመጥ ጊዜ ቢሰጣጡ ተመሳሳይ አረዳድ ላይ ይደርሱ ነበር። አንዳንዱ ደግሞ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር የለም። ነገር ግን በደጋፊነትና በነቃፊነት ጎራ ይተራመሳል። የዚህ መፍትሔው ከፍ ያሉ ጉዳዮች ላይ ዝም ብሎ ማዳመጥ የተሻለ ነው።

፲፦ ወቅት እየጠበቁ የሚያከራክሩ ጉዳዮች አሁንም ብዙ አሉ። ለምሳሌ የልደት ጾም በዘመነ ዮሐንስ ህዳር 15 ይጀመራል ወይስ 14? ጥምቀት ሰኞ ሲውል ቅዳሜና እሑድ ይጾማል ወይስ እሑድ ብቻ የመሳሰሉ ጉዳዮች ይነሳሉ። (እነዚህን የጠቀስኳቸው ታዋቂ ስለሆኑ እንጂ ሌላም ቀኖናዊ ያልሆኑ ከፍ ያሉ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ለጊዜው ከዚህ አልጠቅሳቸውም)። አሁን ዘመኑ የሚዲያ ስለሆነ ሁሉም የየራሱን አብነት እየያዘ ከሚወጋገዝ በማዕከላዊነት ሊቃውንት ተሰብስበው ወጥ የሆነ እይታ እንዲኖር ማድረግ ግድ ይላል። የሊቃውንት ጉባኤ ከዘመኑ መቅደም አለበት። EOTC Tv ከአሉባልታና ከጳጳሳት ውዳሴ ወጥቶ ዘመኑን የሚመጥንና ጥያቄዎችን ቀድሞ የመመለስ ሥራ ሊሠራ ይገባል።

ኦርቶዶክሳዊው መንገድ ጉዳይ ተኮር ነው። ክርስቶስ ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን አልጠላም ብሏል። ይህ ጉዳይን በጉዳይነቱ መሞገት እንደሚገባ ያስረዳናል። ሁሉም ሰው የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ከውስጥም ከውጭም ጠላቶች መጠበቅ አለበት። ሲጠብቅ ግን እውነትን መሠረት አድርጎ እንጂ በተሳሳተ ፍረጃ፣ ስምን በማጥፋት፣ በስድብ ሊሆን አይገባም።

© በትረ ማርያም አበባው
👍10😁1
✍️ .................ትዝብት ..........✍️.።

።...ዓለም እንደዚህ ናት...።

ጎል ባስቆጠርክ ጊዜ ቁማ ታጨበጭብልሃለች።ሪከርድ በሰበርክ ጊዜ በስምህ ቲሸርት ታሳትምልሃለች።በስምህ ድርጅት ትከፍትልሃለች። ለክርስቶስ ያልገለጠችውን ፍቅሯን ላንተ ትገልጥልሃለች። ነገር ግን ይህንን ያህል የወደደችህ ዓለም! ለጎል የተቃረበ ኳስን ተሳስተህ ብታበላሽ በስምህ ያሳተመችውን ቲሸርት ወዲያው ትቀደዋለች። የድርጅቷን ስምም በሌላ ትለውጣለች። ሰው ነው እና ይሳሳታል ማለቷን ትታ ለምን ተሳሳተ እያለች ታማታሃለች። የተሳሳተ ቢሠራ ነው። ያልተራመደ እንቅፋት አይመታውም።
ምክንያቱም ተኝቷል" በማለት አትረዳልህምም።
በዚህ ውስጥ ዓለም የዘነጋችው ቢኖር ? ለስሂት መኑ ይሌብዋ ያለውን የመዝሙር ጥቅስ ነው።

✍️ በዚህ ሰሞን የታዘብኳቸው ጉዳዮች ብዙዎች ናቸው ።በዋናነት ሶስት መሠራታዊ ነጥቦችን
በአክሊል ዙሪያ በኋላ አነሳለሁ። በሶሻል ምድያው ላይ በርካታ ትምህርቶች እየተሰጡ ነው።ሰውም ከዐውደ ምሕረቱ ይልቅ ሶሻል ምድያው ላይ ሰፍሯል። የምድያው አላማ አማኙን ምድያው ላይ ማስቀረት ሳይሆን ምድያው ላይ የሰፈረውን ምእመን ወደ ዐውደ ምሕረቱ መሳብ ነው። ንቦችን ዛፍ ላይ ፤ አጥር ላይ ልናሰፍራቸው እንችላለን። ኋላ ግን አውራቸውን ይዘን መዓር ወደ ሚሠሩበት ቀፎ እናስገባቸዋለን ።ምክንያቱም አሳ የሚጠመደው ባሕር ላይ ነው። ቆቅም የምታያዘው ዱር ላይ ነው ። የሚከሸኑት ግን ከቤት ውስጥ ነው።

✍️ ምእመናንንም ከሀገር ከሀገሪት ፤ ከሀቃል ከሮቢት፤ ከዱር ከገደሉ ከሶሻል ምድያው የወንጌል መረብን በመጣል ልናጠምዳቸው እንችላለን።የክርስቶስ አካል ብልት የሚሆኑት ግን የጸጋ ግምጃ ቤት በሆነችው በቤተ ክርስቲያኗ ነው።ይህንን ሥራ ደግሞ አሁን በምድያው ውስጥ ያሉ ወጣቶቻችን እየሠሩት ነው ። ይህንን ማበረታታት ግድ ነው ።

✍️ከጥቂት ዓመታት በፊት ምድያው ላይ ሙስሊሞች ንጽጽር ሠራን እያሉ መጽሐፍ ቅዱስን እያጋጩ የእኛ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጣላ እንደሚጋጭ አስመስለው ያሠራጩ ነበር። እኛ ደግሞ እንደ ከዋክብት የበዙ ሊቃውንት ቢኖሩንም ምድያው ላይ እንደ አሁኑ የሚሞግቱ የሚከራከሩ ወጣቶች ግን ብዙም አልነበሩንም ። ምድያው ላይ ማለቴ ነው ።

...........✍️ ፕሮቴስታንቶችም ".......

ኦርቶዶክስ ? ሥዕል ታመልካለች፥
☝️ታቦት ታመልካለች ፤
☝️ድንግል ማርያምን ታመልካለች፤
☝️ቅዱሳንን ታመልካለች እያሉ አንድ አምላክ ማምላኳን ክደው በሀሰት ሲኮንኗት ፤ ሲጽፉባት ፦በየምድያው ሲያቀረሹባት እንደ ኮከብ ተወርውረው እንደ አድማሱ ጀምበሬ፤ እንደ ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ የመሳሰሉት ውሃ በእሳት ላይ እንደሚነሳሳ ሁሉ እነርሱም በቅናት ተነስተው የመናፍቃንን ምንፍቅና እልም ድርግም የሚያደርጉ ጽሑፎችን ሲጽፉ አይተናል ።ይሁን እንጅ ምድያው ላይ ግን ብዙም አልተራመድንም ነበር ።ታላላቁ ምድያዎች እንኳን እስከ አሁን ሁለት ናቸው ። ይህ ስንፍናችን አሳዛኝ ቢሆንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በርካታ ወጣቶች በምድያው ላይ ተሠራጭተዋል ።

እኔ እንኳን በመጠኑ የማያቸው ወጣቶች ብዙዎቹ ዲ/ን እንኳን አይደሉም።ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሱን እንደ ውሃ ይጠጡታል ። ከላይ የጠቀስኳቸው የሙስሊም ኡስታዞች እና የፕሮቼስታንት ፓስተሮች ሊከራከሩ ቀርበው ላብ በላብ ሲሆኑ መልስ አጥተው ሲያቃትቱ አይቼ ተደንቄያለሁ ።የሳቁባቸው እና የተሳለቁባቸው የገድላትን፥ የቅዱሣት ሥዕላትን፤ የታቦትን ፤የቅዱሳን ምልጃን በተመለከተም ብዙዎች እንዲህ ነው እንዴ ? ብለው ሲመለሱ ታይተዋል።ብዙዎች ደግሞ ደንግጠው ከመንቀፍ አፋቸውን ሲቆጥቡ ተመላክቷል። ሌሎች ደግሞ በዚህ ተበሳጭተው በወጣቶቹ ላይ ፖለቲካ ሠርተዋል። በዋናነት ወጣቶቹን እኔ በግሌ የቤ/ክርስቲያኗ የደስታ ፍሬዎች ናቸው ብየ አምናለሁ ።በጣም ይቅር በሉኝ እና? እኔ በትርጓሜ ጉባኤ ቤት ብዙ ዓመታትን ደክሜያለሁ።ሰባኬ ወንጌል ሁኜም በማገልገል 10 ዓመት ሞላኝ። አሁንም የመጨረሻው ትምህርቴ መጽሐፈ ሊቃውንትን እየጨረስኩ ነው ። ግን ስንት መናፍቃን አሳመንክ ብትሉኝ ከነአኬ ጋራ ሲነጻጸር መልስ የለኝም ። ቀጥታ ሲከራከሩ ሲወያዩ ባይገጥመኝም። የተወያዩትን በፌስቡክም በሌላም ተለቆ ሳያው ግን በእጅጉ ደስተኛ ነው የሆንኩት። ሂደት ላይ ሊሳሳቱ ይችላሉ። በየቀኑ ማስተማርና በየ ቀኑ መከራከር ይለያያሉ። ወጣቶቹ ብዙ ጊዜ ከኢአማንያን ጋራ ከመከራከራቸው የተነሳ ዳኅጸ ልሳንም ዳኅጸ ልቡናም ሊገጥማቸው ይችላል። ዳጥ ደግሞ አንገዳግዶ ይጥላል። ወጣቶቹ እንዳይወድቁባት ቤ/ክርስቲያኗ ልትደግፋቸው ይገባል። ምድያ ደግሞ የዳጥ መንገድ ነው።ብዙ ሰዎች በርሱ እየተራመዱ ወድቀዋል። ምናልባትም ለመውደቅ ሲንገዳገዱ በመደገፍ ፈንታ ከገፋናቸው መውደቅ ብቻ ሳይሆን አወዳደቃቸው የከፋ ይሆናል ። ይህ እንዳይሆን ቤ/ክርስቲያኗ፤ ሊቃውንቱ ከጎናቸው ቁመው በምሥጢር በምክር እና በሀሳብ በሞራልም ጭምር መርዳት አለባቸው ፥

✍️አኬ ስለ ተባለው ወንድማችንም ባለፈው አንድ ነገር ጽፌ ነበር። አሁንም ልጁ ብዙ ጊዜ ከካቶሊኮች ጋራ፤ ከፕሮቴስታንቶች ጋራ፤ ከተሀድሶዎች ጋራ ሁልጊዜ የሚከራከር ከሆነ የቋንቋ የሀሳብ የምልከታ የእይታ ግጭት ሊፈጠር ይችላል ። በእስክንድርያ ከተነሱ ሊቃውንት እንደ ኦሪገን (አርጌንስ) ለመናፍቃን መልስ የሰጠ ፦ከመናፍቃን ጋራ የጨበጣ ውጊያ ያደረገ የለም። ለሌሎች መልስ እየሰጠ ሲሰቃይ ኑሮ እርሱ ግን የአስተምህሮ ግጭት ተገኘበት። ብዙ ሊቃውንት ለመናፍቃን መልስ ለመስጠት ሲታገሉ ከጥረታቸው ብዛት የተነሳ በትምህርታቸው ላይ እንከን ሊመጣ ይችላል ።
ይሄ ደግሞ በሁሉም ቤተ እምነት ባሉ መምህራን ዘንድ ያለ ነው ። ልጁ በርካታ አድማጮች ስለነበሩት የልጁ እንዲህ መባል ለብዙ ምእመናን በተለይ ለወጣኒዎች ጭንቀት ይሆናል። አንድ ነገር ግን እንመን። ልጁ ላይ ያሉት ሀሳቦች" እይታዎች ፤ ምልከታዎች ናቸው እንጅ በፍጹም ምንፍቅናዎች አይደሉም። እነዚህን የመሰሉ ሀሳቦች ደግሞ በጉባኤ ቤት ሁልጊዜ ይነሳሉ።ሁልጊዜ ግን መልስ ይሰጣል።ሀሳቡ ምድያ ላይ ስለተነሳ ክርክሩም ምድያ ላይ ሆነ እንጅ በጉባኤ ቤት አኬ ካነሳቸው የበለጡ የሚያስደነግጡ ሀሳቦች ሁልጊዜ ይነሳሉ።ሁልጊዜ ያከራክራሉ።ወዲያው ምላሽ ያገኛሉ። የአኬ ሀሳብም እንደዚሁ ነው ብየ ተስፋ አደርጋለሁ ።ስለሆነም .....።

✍️መምህር ጽጌ አስተራየ የቅኔ፣ የመጻሕፍተ ብሉያት፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳት፣ የመጻሕፍተ መነኮሳት፣ የአቋቋም መምህር ሲሆኑ መጻሕፍተ ሊቃውንትን ደግሞ ወደማጠናቀቅ ያሉ ወጣት ሊቅ ናቸው።
6👍6
2025/08/31 20:53:18
Back to Top
HTML Embed Code: