tgoop.com/waaldaa/1250
Last Update:
#የኢየሱስ_እናት !!! (ዮሐ.2:1-2)
"#ከማርያም ያልተቀበልከውን ኢየሱስ እንዴት ተቀበሉ ማለት ትችላለህ ??"
+++
#የኢየሱስ እናት" ማለት ድንግል ማርያም የምትጠራበት መጠርያ ሲሆን ፣ "የፈጣሪ እናት ፣ የእግዚአብሔር እናት ፣ የጌታ እናት ፣ የመድኃኔ ዓለም እናት ናት !!" ማለት ነው ። የጌታ የኢየሱስ እናት ማለትም በወንጌል ስለ ድንግል ማርያም የተጻፈልን ምስክርነት ነው ። ።#ዮሐንስ በወንጌሉ በመጀመርያ ቃል ነበር ብሎ የዚያ እግዚአብሔር ቃል እናት ድንግል ማርያም ፣ ወላዲተ ቃል መሆኗን ለመግለጽ የጌታ ኢየሱስ እናት ይላታል ። (ዮሐ.1:1፤ ዮሐ.2:1-2)#እውነት ነው !!
#የእግዚአብሔር ልጅ ፣ የማርያም ልጅ ሆኗል ። የማርያም ልጅም የእግዚአብሔር ልጅ ነው ። እርሱ ጌታ ነው ፣ እርሷም የጌታ እናት ትባላለች ፣ እርሱ አምላክ ነው፣ እርሷም የአምላክ ትባላለች ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው ፤ እርሷም የእግዚአብሔር እናት ትባላለች ። ስሙም ኢየሱስ ነው ፤ እርሷም የኢየሱስ እናት ትባላለች ። #የእግዚአብሔር ልጅ በተዋሕዶ የማርያም ልጅ ከሆነ በኋላ "ይህ የማርያም ልጅ ነው ፣ ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ።" እየተባለ ኢየሱስ አይከፈልም ። ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ሥጋን መዋሐዱን ለመግለጽና አካላዊ ቃል ከሥጋ ጋር ያደረገውን ተዋሕዶን ለማሳየት ኢየሱስ "መካከለኛ' ተብሏል ፣ መካከለኛ ማለትም ሥግው ቃል ማለት ነው ፣ ሥጋን የተዋሐደው አካላዊ ቃል ማለት ነው ፣ መካከለኛ ማለት ድንግል ማርያም የወለደችው ኢየሱስ ማለት ነው ፣ መካከለኛ ማለት በቀበሌ ቋንቋ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ ፈራጅ ፣ ዳኛ ማለት ነው ። የአብ አንድያ ልጅ ፣ የድንግል ማርያምም አንድያ ልጅ ነው ። እርሱም አዳኝና ፈራጅ ነው ፣ ስሙም ኢየሱስ ነው ፤ እናቱም ድንግል ማርያምም የኢየሱስ እናት ትባላለች ፣ የእግዚአብሔር እናት ማለታችን ነው ። እንዲህ ማለት ግን "እርሷ ፈጣሪ ናት !" ማለት አይደለም ፣ "እግዚአብሔር ናት!' ማለትም አይደለም ። ወንጌላዊው ዮሐንስ ፣ ቃል ሥጋ ሆነ ባለበት የተዋሕዶ ምሥጢር ፣ እርሷንም ወላዲተ ቃል ለማለት የኢየሱስ እናት ብሏታል ። (ዮሐንስ .2:1-2)
+++
ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ከተናገራቸው ሰባት ቃላት መካከል አንዱ "እነሆ ልጅሽ!!" ብሎ ዮሐንስ ወንጌላዊውን የድንግል ማርያም የቃል ኪዳን ልጅ አድርጎ ለእናቱ የሰጠበት የቃል ኪዳን ቃል ይገኛል ። ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ እናቱን ለወንጌላዊ ዮሐንስ እናት አድርጎ ሲሰጠው እኮ ድንግል ማርያም ከራሱ ከብቸኛ ልጇ ከኢየሱስ በቀር ሌላ ልጅ እንደሌላት ሲያስተምረን ነው (ዮሐ.19:26) ፣ ይህ የራሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ነው ። ከእርሱ ሌላ ልጅማ ቢኖራት ኖሮ ከእነዚያ ልጆች መሀከል በዮሐንስ ፈንታ ስሙን በጠቀሰው ነበር ፣ ወይም ወደ ልጇ ወደ እገሌ ወይም እገሊት ውሰዳት ብሎ ለወንጌላዊው ዮሐንስ በነገረው ነበር። ነገር ግን ድንግል ማርያም ከኢየሱስ በቀር ሌላ ልጅ ስለሌላት የኢየሱስን ቃል ሰምቶ ወንጌላዊው ዮሐንስ ወደ ቤቱ ወሰዳት ። እውነታው ይህ ነው !!!
#ጸረ ኦርቶዶክስ የሆኑት ቡድኖች ግን ይህንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ባለመቀበል ክርስቲያን ነኝ ማለታቸው ያሳፍራል ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ከተናገራቸው ሰባቱ ቃላት መካከል ሌላኛው "ዛሬ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ " የሚል በቀኝ ለተሰቀለው ሽፍታ የተነገረ ነው ። ጸረ ኦርቶዶክስ የሆኑት ቡድኖች ስለዚህ ሽፍታ ሲሰብኩ በኩራት ነው ። ነገር ግን "እነሆ እናትህ !! እነሆ ልጅሽ !! የሚለውን የኢየሱስን ቃል ሰምተው ስለ ድንግል ማርያም ለመስበክ ይዘገንናቸዋል ። ሽፍቶች ናቸውና የሽፍታ መንገድ ይስባቸዋል ፣ ንጽሕናና ቅድስና የሌላቸው ትውልዶች ስለሆኑ የማርያም መንገድ አይመቻቸውም ፣
ጎበዝ !!!
አብ በሰማይ ሆኖ እኮ "ልጄን ስሙ !!" ብሏል ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ 'እነሆ እናትህ !!!" ብሎ ለክርስትናህ ምልክት አድርጎ ድንግል ማርያምን በመስቀሉ ስር ሰጥቶሃል ። ድንግል ማርያምን እናት አድርጎ ሲሰጥህ አልቀበልም ማለት እንዴት ይቻልሃል?? እርሷ እኮ ናት! ኢየሱስን የምትሰጥህ !! ከማርያም ያልተቀበልከውን ኢየሱስ እንዴት "#ተቀበሉ !!"ማለት ትችላለህ ?? እርሱ ልጇስ ኢየሱስ ክርስቶስ "እናተን የተቀበለ እኔን ተቀበለ።" አለ እንጅ መች በቀጥታ ተቀበሉኝ አለ?? (ማቴ.10:40) ለማንኛውም ወዮታ አለብህ !! ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር "የአባቴን ቃል የሚሰማ መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳል አለ እንጅ ኢየሱስ !!! ኢየሱስ !! ጌታ ሆይ !! ጌታ ሆይ !!! የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ስማያት አይገባም ብሎሃል ። (ማቴ.7:21)
#ድንግል ማርያም ለኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ለመወለዱ ምልክቱ እንደሆነች ለእኛም በመስቀሉ ስር ለተወለድነው ድንግል ማርያም ምልክታችን እንድትሆን ተሰጥታናለችና ። እናት አድርገህ ተቀበላት ፣ ከልጇ ታማልድሃለች ፣ ታስታርቅሃለችም ። ሰብአ ሰገል እናቱን ድንግል ማርያምን ሲያዩ የማርያም ልጅ ብለው ለኢየሱስ መስገዳቸውን አስብ !! (ማቴ.2:11)። አንተ የማን ልጅ ብለህ ነው ?? ለኢየሱስ የምትሰግደው ?? ሐዋርያት እኮ ፣ ድንግል ማርያም በመካከላቸው ሆና ሳለ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል ፣ በስብከታቸው ስሟንም ጠርተዋል ።(ሐዋ.1:14): አንተ ግን ድንግል ማርያም በሌለችበትና ስሟ ባልተጠራበት አዳራሽ መንፈስ ቅዱስ ወረደልኝ ስትል ትንሽ አታፍርምን ???
#እኛ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለድንግል ማርያም እንደነገረን ድንግል ማርያምን የኢየሱስ እናት፣ የጌታ እናት ፣ የእግዚአብሔር እናት እንደሆነች እናስተምራለን !! አማላጃችን እንደሆነች እናምናለን፣ እንመሰክራለን ። ድንግል ማርያም የአዳኙ የእግዚአብሔር እናት እንደሆነች ሁሉ በመስቀሉ ስር በተሰጠን የልጅነት ቃል ኪዳን ለዳኑት ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ፣ እናታችን መሆኗን እንመሰክራለን ።
✧━━━━━━━━━━━━━━━━━✧
❍ㅤ ⎙ㅤ ⌲ ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ ˢᵃᵛᵉ ˢʰᵃʳᵉ
BY ማህበር ሐዋርያት ቢሊዳ ማርያም
Share with your friend now:
tgoop.com/waaldaa/1250