tgoop.com/wegoch/5292
Last Update:
'ለምን' ብዬ ልጠይቅ ከማሰፍሰፌ ምክንያታቸው ተገለጠልኝና አስችለኝ ብዬ
"ታዲያ ከሳቸው ደስታ የሚበልጥ ምን አለ ሚጡዬ?በቃ የመረጡልሽን አድርጊ እናትሽ አይደሉ?" ብዬ አባበልኳትና አቅፌአት የጨጓራዬን ጭስ ወደ ባዶው አየር ለቀቅሁት።
የመሞሸሪያችን ቀን እሳቸውን የቻለ ትዕግስቴን ጎረቤቶቻቸውና ወዳጆቻቸው ሲፈታተኑት ዋሉ።እዮብም እንዲህ መፈተኑን እንጃ!ታላቅ ወንድሟ ካሳሁን ጓደኞቹን ሰብስቦ ሰርጌን የጀማሪ ክብደት አንሺ የቅርፅ ዉድድር አስመሰሉት። በሌባ ጣቱ መሬቱን እየጠቆመ
"ሎ...ሎጋው ሽቦ...ቦ" ሲል
"ኧረ የምን ሎጋው ሽቦ?እስቲ ሌላ ትከሻ እሚፈትን ዘፈን አምጡ"አሉ ጎረቤታቸው እትየ አስካል።የቀለም ትምህርቱም ሆነ ህይወት ራሷ ባስተማረችኝ ልፈታው ያልቻልኩት ትልቁ እንቆቅልሽ ሴት ስታርጥ ለምን አሽሙረኛ እንደምትሆን ነው።አዛውንቱን ቀርቶ ወጣቱን የሚያስት ጥርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ ያቀነቅኑ ገቡ።
አንች የኔ አበባ ነሽ የኔ አበባ...
አንች የኔ አበባ ነሽ የኔ አበባ(ተቀባይ)
....
መላ ነው ነይ መላ
እነው መላ መላ(ተቀባይ)(2x)
የዘውድነሽን ልጅ ነይ መላ
እነው መላ መላ(ተቀባይ)
ወዴት አገኛት " "
አለ እናቷ ጓዳ '' "
መታያም የላት " "
የኔማ ዘውድነሽ " "
እጇ ያረፈበት " "
ለአልፎ ሂያጅ ይበቃል " "
ማጠር አያውቅበት " "
እየው እየው መላ
አሉና ለ ሁለት ደቂቃ ያህል ትከሻቸው እስኪገነጠል ተንዘፍዝፈው ከከበባቸው ተቀባይ መሃል ወጡ።የሳቸውን መንዘፍዘፍ ተከትሎ አማቴ በኩርፊያ ተነፋፍተው ወደ ጓዳ እያቶሰቶሱ ሲገቡ ታዝቤ ነበር።
በነጋታው የተከራየነዉን ቬሎ መልሰን በአማቴ ሰፈር በኩል አለፍን...ሰይጣን ሹክ ብሎን ነው መቼስ!እትየ ዘውዴ ቤት ስንደርስ በርከት ያለ ሰው ተሰብስቦ ስላየን ጠጋ አልን።አማቴ እያማረሩ ለተሰበሰበው ህዝብ ስሞታ ያቀርባሉ።
"ምነው ነገር በኔ መግነኑ?አጭር አምቻ በኔ አልተጀመረ!ምነው ዘቢዳር በርጩማ እሚያህል አምቻ ስታመጣ ምን ተባለ?ደሞ ደግሸ ባበላሁ እኔ ላይ አሽሙር አስካል?እኔ ላይ?... ቁመት ቢረዝም ምን ሊረባ??በቁመት የጎዳውን በጠባይ ክሶት የለ?...እንደአንች አምቻ ነጋ ጠባ ከሚጎረጉጫት ኧረ የሽቶ ጠርሙስ አክሎ መኖር በስንት ጣዕሙ?..."እያሉ የጥያቄ ናዳ ሲያዥጎደጉዱ እትየ ዘቢዳር የተሰበሰበውን ሰው እየገፈታተሩ እትየ ዘውዴ ላይ ደረሱ
"እከከከከከከ!ይች ናት ዘቢዳር!የማን አምቻ ነው በርጩማ አንች?የኔን አምቻ ነዋ ምሽቱ ብብትና ብብቱን ይዛ አልጋ ላይ እምታሰቅለው!አልሰማንም'ኮ አሉ...አልሰማንም...አሁን ማን ይሙት ከአንች አምቻ የሚወደለው እንቅፋት ሆኖ የሰው ጥፍር አይልጥም? " እያሉ ሲውረገረጉ
ሹልክ ብዬ ወጣሁና ከጥቂት እርምጃ በኋላ ያገኘኋቸውን አንድ የኔ ቢጤ አባት ሰላም ብዬ ጥያቄዬን አስከተልኩ።
"አባቴ እንደው መዘጋጃ ቤቱ በየት በኩል ይሆን?"
"ማን ሞቶ ነዉ?" ደንገጥ ብለው ጥያቄዬን በጥያቄ መለሱት።
ቃል አጠሮኝ ጉዞየን ቀጠልኩ።ለካ ፍታትና ቀብር ለሞተ ብቻ ነዉ።
ዘማርቆስ
@wegoch
@wegoch
@paappii
BY ወግ ብቻ
Share with your friend now:
tgoop.com/wegoch/5292