tgoop.com/whispers_of_thought/725
Last Update:
የሚገርሙኝ ዘመን ተሻጋሪ ቃላት
- ከእመጓ መፅሐፍ
- በዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ (ዶ/ር)
(ገፅ 162-163)
~በአፍላ ትጀምራላችሁ በወረት ትተዉታላችሁ፡፡ ያወቃችሁትን ትረሳላችሁ፤ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ፤ የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፤ የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ፡፡ ምኞታችሁ ልክ የለውም፤ አምሮታችሁ ብዙ ነው፡፡
~የአማራችሁን ስታገኙ ወዲያው ይሰለቻችኋል፡፡ ተዉ የተባላችሁትን ትሽራላችሁ፤ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ፤ የተፈቀደላችሁን ችላ ትሉታላችሁ፡፡ …
~ሁሉን ማወቅ ትፈልጋላችሁ፤ በአንዱም ግን አትጠቀሙበትም፡፡ ሁሉ አላችሁ፤ ግን ባዷችሁን ናችሁ፡፡ ሃይማኖት እንጅ እምነት የላችሁም! …
~መቀመሚያውን ነግሬህ ማርከሻውን ሳልገልጥልህ መጀመሪያውን ብቻ ሞጭልፈህ ትተኸኝ ትሄዳለህ፡፡ ጥበብን ‹‹ሀ ግዕዝ›› ብዬ ላስተምርህ ብሞክር፣ መንደር ውስጥ በቃረምካት ዕውቀት ተመክተህ በመሰልቸት ‹‹ሆ ሳብዕ›› ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ፡፡
~የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተልከፈከፈ የተማሪ ኮፋዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል፡፡
~ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ፣ ሰርታችሁ ሀብት ስታፈሩ፣ ከላይ የሆናችሁበትን ሃገር ለቃችሁ፣ ሰፋ ወዳለው እንሂድ ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ፡፡ ትቀጥላላችሁ፣ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ፡፡ ቸኩላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ፡፡ በጽኑ ታማችኋል!
~ከታሪክ ፍቅርንና ልማትን ሳይሆን ጥላቻንና ጥፋትን ለይታችሁ ትቆፍራላችሁ፡፡ ከዚያም ቀጥላችሁ የከበረ ማዕድን እንዳወጣችሁ ሁሉ በኩራት ደረታችሁን ነፍታችሁ ሳትመርጡ ሁሉን በአደባባይ ትዘሩታላችሁ፤ እናም ወደ ኋላ ስለታሪካችሁና ስለ ቅርሳችሁ ባሰባችሁ ቁጥር ፍርሃትና ሃፍረት ይሰማችኋል፡፡
~ስለሆነም ከኋላ ታሪካችሁና ክብራችሁ እየራቃችሁ መጣችሁ። የአሸናፊነትንና የተሸናፊነትን ትርጉም በአንድ ላይ የያዙ ሃውልቶች ታቆማላችሁ፡፡ ለግልጽነትና ለነጻነት እያላችሁ በምታደርጉት ሽኩቻ ዕርቃን ወደ መሆን ወረዳችሁ፡፡
~ቅቤ ላይወጣችሁ ትናጣላችሁ፡፡ በዚህ ዓለም ጥድፊያ ታማችኋል፡፡ ሀገራችሁን ትንቃላችሁ፤ ጥላችሁ ለመሄድ ትፈልጋላችሁ፤ ከሄዳችሁ በኋላ ደግሞ አፍታ ሳትቆዩ አገሬ ናፈቀኝ ትላላችሁ፡፡
~በቁማችሁ የናቃችሁትን የሀገራችሁን አፈር በሞታችሁ ልትለብሱት ትናፍቃላችሁ፡፡ ለሀገሬ አፈር አብቃኝ ብላችሁ በድናችሁን ልካችሁ የወገኖቻችሁን ልብ ትሰብራላችሁ፡፡
~ግብዝነታችሁ መጠን የለውም፡፡ ሁለት ሀገር እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁ፤ አንዱን በደም ሌላኛውን በመታወቂያ ታስባላችሁ፡፡ ከአንዱም ግን በአግባቡ አትኖሩም፡፡ ዘመናችሁም በምልልስና በመዋተት ያልቃል፡፡
~ምን እንደምትፈልጉ አታውቁም እናም ፍለጋችሁ አያልቅም፡፡
BY የኔ_እይታ 🧘🏽 Thoughts
Share with your friend now:
tgoop.com/whispers_of_thought/725