tgoop.com/yekidst_hager777/2478
Last Update:
ጥር 22 ቀን በግብፅ አገር ከአቅማን ከተማ የከበረና የገነነ የመነኰሳት ሁሉ አባት በገዳም ለሚኖር እንደ ኮከብ የሚያበራላቸው አባት እንጦንስ የእረፍቱ መታሰቢያ ነው።
#የአባ_እንጦንስ_ምክሮች
✞ ከዕለታት በአንድ ቀን አባ ፓምቦ አባ እንጦስን "ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?" ብሎ ይጠይቃል።አባ እንጦስም እንዲህ ሲል መለሰለት "በራስህ ጽድቅ አትታመን፤ላለፈው አትጨነቅ፤ይልቁኑ አንደበትህንና ሆድህን ግዛ።"
✞ አባ እንጦስ በአንድ ወቅት እንዲህ አለ፦ "በዚች ምድር ላይ ስንኖር ህይወታችንንም ሆነ ሞታችን ከባልጀራችን ጋር ነው። ወንድማችንን ገንዘብ ካደረግነው እግዚአብሔርን ገንዘብ እናደርጋለን፤ ወንድማችንን ካስቀየምነው ግን በክርስቶስ ላይ ኃጢአትን እናመጣለን።"
✞ በአንድ ወቅት አንድ ወንድም አባ እንጦስን "ጸልይልኝ" በማለት ይጠይቃል። እንጦስም "አንተ ራስህ ጥረት የማታደርግና ወደ እግዚአብሔር የማትጸልይ ከሆነ እኔም ሆንሁ እግዚአብሔር ምህረት ልናደርግልህ አንችም" አለው።
✞ እግዚአብሔር ሆይ አፈርና ትቢያ ሆኜ ሳለ ጻድቅ አድርገው ከሚቆጥሩኝ ሰዎች አድነኝ።
✞ ኃጢአታችንን እኛ እያሰብን የምንፀፀት ከሆነ እግዚአብሔር ይረሳልናል፤ ኃጥያታችንን እኛ እረስትን የምንፅናና ከሆነ እግዚአብሔር ያስብብናል።
✞ ብዙ ጊዜ ሰዎች ብልህ ነን እያሉ ይሳሳታሉ። ነገር ግን ብልህ የሚባሉት ብዙ የተማሩና ብዙ ያነበቡ ብዙ የሚናገሩ ብቻ አይደሉም። ይልቁንም ጠቢባን የሚባሉት ጥብብት መጥበቢት ብልህ ነፍስ ያላቸው፤ የእግዚአብሔርንና የሰይጣንን ለይተው ለእግዚአብሔር ሆነው የሚኖሩ ናቸው። ፍጹም ምልዓተ ኃጢአትንና ከጦር ይልቅ የሚወጉ የኃጢአት እሾሀቸውን የነቀሉ ናቸው ጠቢባን።
✞ ጠቢባንስ እግዚአብሔርን ያለጥርጥር በሙሉ ልብ የሚያምኑት፤ አምነውም እንደ ፈቃዱ የተከተሉት፤ በክንፈ ጸጋ ተመስጠው ከልብ በሚወጣ ውዳሴ ከእርሱ ጋር ተዋሕደው የሚኖሩ ናቸው። የነፍሳቸውን ረብሕ ጥቅም አውቀው ዕለት ዕለት ያንን የሚለማመዱ በእውነት ጠቢባን እነዚህ ናቸው።
✞ የጋለ ብረትን ለመቀጥቀጥ የሚነሣ ሰው አስቀድሞ በብረቱ ምን ለመሥራት እንዳሰበ መወሰን አለበት፤ መጥረቢያ፥ ሰይፍ፥ ወይስ ማጭድ? እኛም በምን ዓይነት የሕይወት መስመር ፍሬ ለማፍራት እንዳሰብን አስቀድመን ልቡናችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡
✞ ዘወትር በዐይንህ ፊት ፈሪሃ እግዚአብሔር ይኑር፤ ሕይወትና ሞት የሚሰጠውን አዘክረው፡፡ ዓለምንና በዓለም ያለውን ሁሉ ጥላው፤ ከሥጋ የሚመጣውን ደስታና ሰላም አትሻ፤ ለዚህኛው ኑሮ ሙትና ለእግዚአብሔር ሕያው ሁን፤ ለእግዚአብሔር ቃል የገባኸውን አትርሳ፤ ያም በፍርድ ቀን ካንተ ይፈለግብሃል፡፡ ረኀብን በጸጋ ተቀበለው፤ ተጠማ፥ ተራቆት፥ ንቁና በሐዘን የምትኖር ሁን፡፡ በልቡናህ አልቅስና ጩኽ፤ ለእግዚአብሔር የምትመች መሆን አለመሆንህን ፈትን፤ ሥጋህን ቀጥተህ ነፍስህን ታድናት ዘንድ፡፡
✞ የቱንም ያህል በመከራ ቢወድቅብህ የቱንም ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብታልፍ ይህንን ለጌታዬ ለመድኃኒቴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስል እቀበላለሁ በል። ቀላል ይሆንልሀል። የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ኃይል ነውና። በእርሱ ማእበሉ ፀጥ ይላል ሰይጣንም ይሸሻል።
✞ ለተወሰን ጊዜ ለሀይማኖት መከራከር፤ ጠበቃ መሆን፤ መዋጋት ብሎም መሞት አይከፋም ሁልጊዜ ለሀይማኖት መኖር ግን ከሁሉ የበለጠ መስዋእትና ክብር ያለው ህይወት ነው፡፡
(#ከተለያዩ_ጽሑፎች_የተሰበሰቡ)
BY ታሪክ ዘ ኢትዮጵያ
Share with your friend now:
tgoop.com/yekidst_hager777/2478