tgoop.com/yekidst_hager777/2508
Last Update:
የካቲት ፲፪ - የአካፋው ሚካኤል
የካቲት ፲፪ በሃገራችን ታሪክ የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን በቤተክርስቲያን ደግሞ በተለምዶ የአካፋው ሚካኤል ተብሎ ይታወቃል ።
በሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ወቅት በኢትዮጵያ የፋሽስት ሹም የነበረውን ግራዚያኒን ለመግደል እነ አብርሃም ደበጭና ሞገስ አስገዶም በጣሉት አደጋ ምክንያት የተቆጣው የኢጣሊያ ጦር እንደ ግራዚያኒ ቁስለኛ የሆኑበትን የአመራሮቹንና የሞቱበትን ጥቂት ወታደሮች ደም ለመበቀል በቦታው ለምፅዋት ከተሰበሰቡት ሰዎች አንስቶ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ያሉ እስከ ፴ ሺ የሚደርሱ ዜጎችን በዘግናኝ ሁኔታ በአካፋ ሳይቀር ያገኙትን መሳሪያ ሁሉ እየተጠቀሙ ጨፈጨፏቸው።
በየአብየተ ክርስቲያኑ ደጃፍ የቅዱስ ሚካኤልን ወርኃዊ የበዓል መታሰቢያውን ለማድረግ በጠዋት የወጡ ምዕመናን ሬሳቸው እንደቅጠል ረገፈ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ በመቶዎች የሚቆሩ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት አርበኞችን ደብቃችኋል ተብለው በገዳማቸው ተረሸኑ።
ፋሺስት ጣሊያን ሕዝቡን ለመጨፍጨፍ አካፈን ተጠቅማ ስለነበርና በየሜዳው የወደቀውን አስከሬን በአካፋ እየተሰበሰበ በጅምላ ስለተቀበረ ቀኑ የአካፋው ሚካኤል ተባለ።
እነሆ ዛሬ ይህ ታሪክ ፹፯ ዓመታት ሞልቶታል።ቤተ ክርስቲያን ከነፃነት ማግስት ጀምሮ በየዓመቱ አጽማቸው ተሰብስቦ በክብር ባረፈበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ ባሉት ሁለት ሐውልቶቻቸው ዙሪያ በጸሎተ ፍትኃት ታስባቸዋለች።
BY ታሪክ ዘ ኢትዮጵያ
Share with your friend now:
tgoop.com/yekidst_hager777/2508