tgoop.com/yisakgizaw/6897
Last Update:
😳ጠላፊዎቹ
፡
#ክፍል_ዘጠኝ
፡
#በኬንፎሌት
፡
#ትርጉም_በወንዳየሁ_ንጉሴ
የጀርመንን ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች ለማሳሳት በርካታ ትላልቅ ብርማ
ቀለም ፊኛዎች ሰማዩ ላይ ያንዣብባሉ፡ ሱቆችና የመንግስት ህንፃዎች
ከቦምብ ናዳ ለመጠበቅ በአሸዋ በተሞሉ ጆንያዎች ዙሪያቸውን ተከበዋል፡
በየመናፈሻው የቦምብ
መከላከያ የተዘጋጀ ሲሆን ሁሉም ሰው በእጁ የጋዝ
ጭስ መከላከያ ጭምብል አንጠልጥሏል ሰዎች በማንኛውም ደቂቃ በቦምብ
ናዳ እንደሚያልቁ ያስባሉ፡፡
ሄሪ ስለ አንደኛው የአለም ጦርነት ምንም ትዝታ የለውም፡ ጦርነቱ
ሲያልቅ የሁለት አመት እምቦቃቅላ ነበር፡፡ ነፍስ እያወቀ ሲመጣ ጦርነት
ምን ያህል አሰቃቂ እንደሆነ አወቀ፡፡ በኋላም ፋሺስቶች በለንደን መንገዶች
ያደረጉትን ወታደራዊ ሰልፍ አዛውንት ይሁዳውያን በፍርሃት ሲመለከቱ
ሲያይ የጦርነትን አስፈላጊነት ተረዳ፡ሆኖም ሂትለር ሶቭየት ህብረትን
ይደመስስልኛል ብሎ የአንግሊዝ መንግስት የሆነውን ሁሉ እንዳላየ ሲያልፍ ጥላቻው ነገሰ፡፡
ሄሪ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ቤቱ መሄድ እንደሌለበት ወስኗል።
ፖሊሶች በዋስ በመለቀቁ ስለተበሳጩ በማንኛውም አጋጣሚ ሊያስሩት
አቆብቁበዋል፡፡ ለትንሽ ጊዜ መደበቅ ያዋጣዋል፡፡ ተመልሶ እስር ቤት መግባት
አይፈልግም፡፡ ታዲያ ስንት ጊዜ ፖሊስ መጣ እያለ ሲበረግግ ሊኖር ነው?
ሁልጊዜስ ፖሊስን መሽወድ ይቻላል? ካልሆነስ ምን ማድረግ ይኖርበታል?
እናቱ በሃዘን ፊታቸው ጠቁሯል፡ ገንዘብ እንዴት እንደሚያገኝ ቢያውቁም አንስተውበት አያውቁም፡፡ ‹‹በእናትነቴ ምንም አድርጌልህ አላውቅም›› አሉት ‹‹እማማ ያለሽን አድርገሽልኛል›› ሲል መለሰላቸው፡፡
‹ሃሰት፤ ምንም አላደረኩልህም፤ ለዚህ አይደለም መስረቅህ››
ሄሪ ለዚህ መልስ አጣ፡፡
ከአውቶብስ እንደወረዱ ጋዜጣ ሻጩ በርኒን እናቱን በስልክ ስለጠራለት
እንደውለታ ቆጥሮት ጋዜጣ ገዛው፡፡ የጋዜጣው የፊት ሽፋን ጀርመን ፖላንድን በቦምብ ደበደበች ይላል፡ ወዲያውም አንድ ፖሊስ በብስክሌት ሲመጣ ተመልክቶ በደመነፍስ ተርበተበተ፡፡ እግሬ አውጪኝ ሊል ሲያስብ ሰው ለማሰር ሁለት ሆነው የሚመጡ መሆኑን ሲያውቅ አደብ ገዛ፡፡
እንደዚህ እየሰጋሁማ እንዴት እኖራለሁ› ሲል አስበ፡፡
እቤት ሲገባ እናቱ ሻይ ጥደው ‹‹ሰማያዊ ሱፍ ልብስህን ተኩሼልሃለሁ፤ መለወጥ ትችላለህ›› አሉት
እስካሁንም ልብሱን የሚያጥቡለትና የሚያዘገጃጁለት ካልሲውንም የሚሰፉለት እናቱ ናቸው፡፡ ሄሪ መኝታ ቤት ገባና ከአልጋው ስር ሻንጣውንዐአውጥቶ ገንዘቡን ቆጠረ፡፡ ሁለት ዓመት በስርቆት ተሰማርቶ ሁለት መቶ አርባ ሰባት ፓውንድ አጠራቅሟል፡፡ የአሜሪካ ፓስፖርት እጁ ገብቷል በሃሳብ ተውጦ ፓስፖርቱን እያገላበጠ ተመለከተው፡፡ ከአንድ አሜሪካዊ ላይ እንደመነተፈው አስታወሰ፡ የሰውየው ስም ሃሮልድ መሆኑን ሰውየውም
እሱን እንደሚመስል ተገነዘበና ኪሱ ከተተው፡
የአሜሪካውያንን የአነጋገር
ቅላጼ ይችላል፡፡ በአሜሪካ ውስጥ የእንግሊዛውያን የአነጋገር ቅላጼ ካለህ የከበርቴ መደብ አባል እንደሆንክ ተደርጎ ይቆጠራል፡ አሜሪካ ውስጥ በርካታ በፍቅር ልታሳብዳቸው የምትችላቸው ኮረዶች አሉ፡፡
እንግሊዝ ውስጥ የሚቀርበት እስር ቤትና ውትድርና ብቻ ነው፡፡
አሁን ፓስፖርትና ኪሱ ሙሉ ገንዘብ አለው፡ እናቱ ቁም ሳጥን ውስጥ ንፁህ ሱፍ ልብስ ያለው ሲሆን አንድ ሁለት ሸሚዝ መግዛት ይችላል።
ከሳውዝ ሃምፕተን 75 ማይል ነው የሚርቀው
ዛሬውኑ መሄድ ይችላል።
ሁሉም ነገር እንደ ህልም መሰስ ይላል።
እናቱ ‹‹ሄሪ ሳንድዊች ትፈልጋለህ?›› ሲሉ ጠየቁት
‹‹እሺ እማ››
ኩሽና ሄዶ ተቀመጠ፤ እናቱ ሳንድዊቹን ፊቱ ቢያደርጉለትም ንክች
አላደረገውም፡፡‹‹እማ አሜሪካ እንሂድ›› አላቸው
እናቱ በሳቅ ፈነዱ ‹‹እኔ አሜሪካ?!››
‹‹እውነቴን ነው፡ እኔ ልሄድ ነው፡››
አሁን ፈገግታቸው ጠፋ ‹‹ለኔ አይሆንም ልጄ፡፡ በዚህ እድሜዬ ስደት
ለኔ አይሆንም››
‹‹እዚህ እኮ ጦርነት ሊጀመር ነው፡፡››
‹‹አንድ ጦርነት፣ የስራ ማቆም አድማና የኢኮኖሚ መዳሸቅ አሳልፌያለሁ፡››
ጠባብዋን ማድቤት አማተሩና ‹‹የኔ ዓለም ይሄ ነው›› አሉ።
ሄሪ እናቱ በዚህ እንደማይስማሙ ቢያውቅም ቁርጡን ሲነግሩት ተስፋው ተሟጠጠ፡፡
በዚህ አለም ላይ ያሉት እናቱ ብቻ ናቸው፡፡
‹‹እዚያስ ምን ልትሰራ አስበሃል?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡
‹‹የሌብነት ስራዬ ያሳስብሻል?››
‹‹ሌብነት የትም አያደርስም፡ በሌብነት ያለፈለት ሰው አላውቅም›› አሉት፡፡
‹‹እዚያ አየር ኃይል ገብቼ አብራሪ መሆን እፈልጋለሁ፡ አሜሪካ ውስጥ ጭንቅላት ካለሽ የሰራተኛው መደብ ብትሆኝም ግድ የላቸውም።››
እናቱ በመጠኑ ፈገግ አሉ፡ እሳቸው ሻይ ሲጠጡ እሱ ሳንድዊቹን ይገምጣል።
በልቶ እንደጨረሰ ገንዘቡን ከኪሱ አወጣና ሃምሳ ፓውንድ ቆጥሮ ለየ
‹‹ይሄ ለምንድን ነው?›› ሲሉ ጠየቁ፡፡ ይህ ገንዘብ ሁለት አመት ልብስ አጥበው የሚከፈላቸውን ገንዘብ ያክላል
‹‹ይጠቅምሻል እማ ውሰጂው›› አለ፡፡
እናቱ ገንዘቡን ተቀበሉና
‹‹እውነት ልትሄድ ነው?›› ሲሉ ጠየቁት።
‹‹ወደ ሳውዝ ሃምፕተን በሞተር ሳይክል እሄድና መርከብ ላይ እሳፈራለሁ»
እጃቸውን ሰደዱና የልጃቸውን እጅ ለቀም አደረጉ፡፡ ‹‹ልጄ መልካም
ዕድል ይግጠምህ፡››
እሱም የእናቱን እጅ ጨበጥ አደረገና ‹‹ከአሜሪካ ገንዘብ እልክልሻለሁ አለ።
‹‹አያስፈልግም፡፡ ከዚያ ደብዳቤ ቶሎ ቶሎ ስደድልኝና ጤንነትህን
ልወቅ፡፡››
‹‹እሺ እፅፍልሻለሁ፡››
አይናቸው በእንባ ተቆረዘዘ ‹‹አንድ ቀን ናና አሮጊት እናትህን እያት››
እጃቸውን ጨበጥ አደረገ፡፡ ‹‹እመጣለሁ እንጂ እማ፡፡ እመለሳለሁ፡››
ሄሪ በመስታወት ከላይ እስከ ታች ራሱን አየ፡፡
ሰማያዊው ሱፍ ልብስ ያማረበት ሲሆን ከሰማያዊው የአይኑ ቀለም ጋ ሄዷል፡፡
ሸሚዙ የአሜሪካ ሽሚዝ ይመስላል፡ ፁጉር አስተካካዩ የባለ ሁለት
ደረት ኪስ ኮቱን ትከሻ በቡሩሽ ሲጠርግለት ሄሪ ጉርሻ ሰጠውና ወጣ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የሳውዝ ሃምፕተን ወደብ በሰው ተጥለቅልቋል። ከዚህ ቦታ ነው የአትላንቲክ አቋራጭ ጉዞ የሚነሳው፡፡ በመሆኑም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች
ከእንግሊዝ ለመውጣት ይተራመሳሉ፡፡
ሄሪ መርከብ ለማግኘት ሲጠያይቅ የሁሉም መርከቦች ቦታ ለመጪዎቹ
ሳምንታት ጉዞ አስቀድመው እንደተያዙ አወቀ፡ አንዳንዶቹ የመርከብ ትራንስፖርት ድርጅቶች ባዶ ቢሮ ታቅፈው ለሰራተኛ ደመወዝ ከመክፈል በራቸውን ዘግተዋል፡ ለተወሰነ ጊዜ ምንም ቦታ የማይገኝ መሰለው።
በመርከብ መሄዱን ትቶ ሌላ አማራጭ መጓጓዣ ሲያፈላልግ አንድ የጉዞ ወኪል ባህር ላይ የሚያርፍና ከባህር ላይ የሚነሳ የፓን አሜሪካን
አውሮፕላንን እንዳለ
አበሰረው፡፡ ስለዚህ አይሮፕላን በየጋዜጣው ላይ
አንብቧል፡ መርከብ ወደ ኒውዮርክ ከተማ ለመሄድ አራትና አምስት ቀን
የሚፈጅበት ሲሆን አይሮፕላኑ ከ30 ሰዓት ባነሰ ይደርሳል፡ ታዲያ የአንድ
ጊዜ ጉዞ ትኬት ዋጋ 90 ፓውንድ አዲስ መኪና ይገዛል።
ሄሪ በርካታ ገንዘብ አባክኗል፡፡ እብደት ነው፡፡ ታዲያ ከአገር ለመውጣት
ሲል የፈለገውን ያህል ዋጋም ቢሆን ለመክፈል ወስኗል፡፡ አይሮፕላኑ ምቾቱ
ያጓጓል፡ ኒውዮርክ እስክትደርስ ድረስ ሻምፓኝ መጨለጥ ነው፡፡ እንዲህ
አይነት ቅንጦት ደግሞ ለሄሪ ነፍሱ ነው፡፡
ፖሊስ ባየ ቁጥር መደንበሩ ሊቀር ነው፡፡ ሳውዝ ሃምፕተን ውስጥ
ደግሞ ስለ እሱ ሌብነት የሚያውቅ ፖሊስ የለም፡፡ ከዚህ ቀደም በአይሮፕላን
በርሮ ስለማያውቅ ግን አዕምሮው ተረብሿል፡፡
BY 📚 Book center የመፅሐፍት ማዕከል 📚
Share with your friend now:
tgoop.com/yisakgizaw/6897