tgoop.com/yisakgizaw/6901
Last Update:
😎ጠላፊዎቹ
፡
#ክፍል_አስር
፡
#በኬንፎሌት
፡
#ትርጉም_ወንዳየሁ_ንጉሴ
ማርክ አልደር በመጀመሪያ ዳያና ላቭሴይንን ያያት ጊዜ ‹‹የአምላክ ያለህ! እንዳንቺ የምታምር ሴት አይቼ አላውቅም›› አላት፡፡
ያገኛት ሁሉ እንዲህ ይላታል፡፡ ዲያና ያለጥርጥር ውብ ሴት ስትሆን ጥሩ ጥሩ ልብስ መልበስም ትወዳለች፡፡ የዚያን ቀን እጀ ጉርድ ቅልጥሟ ጋ የሚደርስ ቀሚስ ለብሳ ነበር፡፡ እንዳማረባትም አውቃለች።
ማንቼስተር ከተማ ሚድላንድ ሆቴል ውስጥ ራት ግብዣ ተጠርታለች
በግብዣው ላይ ከነበሩት ከባሏ የንግድ ሸሪኮች ጋር በሙሉ ስትደንስ አመሸች ታዲያ ሁሉም አብረዋት የደነሱት ወንዶች ደረታቸው ላይ ይለጥፏታል ወይም እግሯ ላይ ይቆማሉ ሚስቶቻቸው ደግሞ በጥላቻ ዐይን አፈር ድሜ ያስግጧታል፡ ወንዶች ቆንጆ ሴት አይተው ሲቅበጠበጡ
ሚስቶች ለምን ባሎቻቸውን ትተው ሴቷ ላይ በቁጣ እንደሚያፈጡ ሁልጊዜ
ይገርማታል፡፡ እሷ እንደሆነ እነዚህን ጉረኛና በዊስኪ የደነበዙ ባሎቻቸውን
አትፈልግም፡፡
አንድ ጊዜማ የከተማውን ምክትል ከንቲባ በሰው ፊት በማዋረዷ ባሏን አሳፍራው ነበር፡ በኋላም ትንሽ እረፍት አገኝ ብላ ሲጋራ የምትገዛ መስላ ከሆቴሉ ወጥታ ሄደች፡
ኮኛኩን እየተጎነጨ ብቻውን ተቀምጧል። ልክ በክፍሉ ውስጥ የፀሃይ ብርሃን የፈነጠቀች ይመስል ስትገባ ዓይኑን ተከለባት፡ ሰውዬው አጠር ያለና እንደ ህፃን ፍልቅልቅ ያለ ፈገግታ የተላበሰ ሲሆን አሜሪካዊ መሆኑ ሁኔታው ያሳብቅበታል፡፡ ገና እንዳያት አድናቆቱን የገለፀላት ሲሆን ሰውዬው የደስ ደስ ያለው በመሆኑ ፈገግ ብትልለትም አላናገረችውም፡፡ ሲጋራዋን
ገዝታ ቀዝቃዛ ውሃ በጉሮሮዋ ለቀቀችና ወደ ዳንሱ አዳራሽ ተመለሰች፡
ሰውዬው ማን እንደሆነች ከቡና ቤቱ አስተናጋጅ ጠየቀና አድራሻዋን
እንደምንም አግኝቶ የፍቅር ግጥም ፅፎ ላከላት፡፡ ግጥሙን ስታነብ አነባች፡፡
ያስለቀሳት ብዙ ነገር ተመኝታ ሁሉንም ነገር ባለማግኘቷ ነው፡፡ ያለቀሰችው በዚች ደስታ በራቃት ከተማ የዓመት እረፍት መውጣት ከሚጠላ ባሏ ጋር ተጣብቃ በመቅረቷ ነው፡፡ ያለቀሰችው ከአምስት ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ
ጊዜ የፍቅር ግጥም በመስማቷ ነው: ያለቀሰችው ለመርቪን ያላት ፍቅር የተሟጠጠ በመሆኑ ነው፡፡
በነጋታው እሁድ ስለነበር ዳያና ቤቷ ውስጥ መሸገች፡፡ ሰኞ ዕለት ወደ
ከተማው መጽሐፍ ቤት ሄዳ ከዚህ ቀደም የተዋሰችውን መጽሐፍ መለሰችና ፊልም ቤት ገባች፡፡ ከዚያም ለእህቷ ልጆች ስጦታ ስትገዛ ዋለች፡፡ በኋላም
እራት መስሪያ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ገዛችና ከከተማ ወጣ ወዳለው መኖሪያዋ
በጊዜ ለመድረስ ባቡር ላይ ተሳፈረች፡፡ ከተማ ውስጥ ስትዟዟርና ቡና ስትጠጣ የአሜሪካዊ አነጋገር ቅላፄ ያለውን ሰው ሳታገኘው በመመለሷ ተከፋች፡፡
ነገር ግን ነገሩን ስታስበው ጅልነት ሆነባት፡፡ ሰውዬውን ያየችው ለአፍታ ጊዜ ሲሆን በወቅቱም አላነጋገረችውም፡፡ ሆኖም ይህ ሰው ለዓመታት ያጣችውን ፍቅር የሚቀሰቅስባት ሆነባት፡ ታዲያ ይህ ሰውዬ ደግማ ብታገኘው ወይ ባለጌ ይሆናል፣ ወይ ወፈፌ ይሆናል፣ ወይ በሽተኛ
ይሆናል፣ ወይ ደግሞ ገላው የሚቀረና ይሆናል ብላ አሰበች
ከባቡሩ ወርዳ የቤቷን መንገድ ይዛ ስትሄድ ባልጠበቀችው ሁኔታ
ሰውዬው ወደ እሷ ሲመጣ በማየቷ ክው ከማለቷም በላይ ተርበተበተች፡፡
ፊቷ ቲማቲም መሰለ፧ልቧም መቶ ሜትር ሸመጠጠ፡፡ እሱም ሲያያት መደንገጡ ባይቀርም ሊያናግራት ቆም አለ፡፡ እሷ ግን እርምጃዋን ቀጠለች።
አልፋው ስትሄድ ‹‹ነገ ጠዋት ማዕከላዊ መጻሕፍት ቤት ጠብቀኝ›› አለችው
መልስ ይሰጠኛል ብላ ባትጠብቅም ሰውዬው ፈጣን አዕምሮ ያለው መሆኑን በኋላ ተረድታለች፡፡ ወዲያው ‹‹የትኛው ክፍል?›› አላት።
አፏ እንዳመጣላት ‹‹ባዮሎጂ ክፍል›› በማለቷ ሳቅ አለ፡፡
ቤቷ የደረሰችው በደስታ ተሞልታ ነው፡
ቤቱ ውስጥ ሰው የለም፡፡ የፅዳት ሰራተኛዋ ስራዋን ጨራርሳ የሄደች ስትሆን
መርቪን ገና አልገባም፡፡
በማግስቱ ቀጠሯቸው ቦታ መጻሕፍት ቤት ከላይ ‹‹ፀጥታ›› የሚል
ፅሁፍ የተንጠለጠለበት ቦታ ተቀምጦ አገኘችውና ‹‹ሰላም›› ስትለው ሌባ ጣቱን ከንፈሩ ላይ አድርጎ ዝም እንድትልና እንድትቀመጥ አመለከታት
ከዚያ ብጣሽ ወረቀት ላይ አንድ ነገር ፅፎ አቀበላት፡፡ ‹‹ኮፍያሽ ያምራል» የሚል ነበር፡፡ ኮፍያዋን በአንድ በኩል ገደድ አድርጋ ራሷ ላይ የደፋች በመሆኗ የግራ አይኗን ከልሎታል፡፡ ይህ ኮፍያ አደራረግ ፋሽን ሲሆን ይህን ፋሽን ለመከተል የሚደፍሩት ወኔ ያላቸው ጥቂት ሴቶች ብቻ ናቸው።
እስክርቢቶ ከቦርሳዋ አወጣችና ‹‹ኮፍያው ላንተ አይሆንም› ብላ ፅፋ
አሳየችው:፡ እሱም ‹‹የግቢዬን አበባ አስቀምጥበታለሁ›› ብሎ ሲፅፍላት በሳቅ ተንከተከተች፡፡ ‹‹ሽሽሽሽ›› አላት ዝም እንድትል፡
ዳያና ይሄ ሰውዬ ወፈፌ ነው አስቂኝ አለች በሆዷ፡፡ ከዚያ
‹‹ግጥሞችህን ወድጃቸዋለሁ›› ብላ ፃፈችለት፡፡
‹‹እኔም አንቺን ወድጄሻለሁ› ብሎ መለሰላት በፅሁፍ፡፡
‹እብድ› ስትል አሰበች፡፡ ሆኖም እምባዋ በዓይኗ ተንቆረዘዘ፡፡
‹‹ስምህን እንኳን አላውቀውም› ብላ ፃፈችለት።
ቢዝነስ ካርድ አወጣና ሰጣት፡፡ ስሙ ማርክ አልደር ሲሆን የሚኖረው ሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ነው፡፡
የምሳ ሰዓት ሲደርስ ምሳ ለመብላት ወደ ምግብ ቤት ሄዱ፡ ይህን ሰዓት የመረጠችው ባሏ እንዳያገኛት ነው መቼም በዚህ ሰዓት ባሏ
አይመጣም ብላ፡፡
ከምሳ በኋላ የሙዚቃ ድግስ ለማየት ቴያትር ቤት ገቡ፡፡
ያን ቀን ማርክ የሬዲዮ ኮሜዲ ደራሲ መሆኑን፣ ለታዋቂ ኮሜዲያኖች
እንደሚደርስ፣ እንዲሁም የሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት መሆኑን አጫወታት
እንግሊዝ አገር የመጣው ትውልዳቸው ከሊቨርፑል
ውስጥ የሚሳብ የትውልድ ዘር ሐረጎችን ለማፈላለግ መሆኑን ነገራት፡፡
ማርክ አልደር ቁመቱ አጠር ያለ ሲሆን ከዳያና አይበልጥም፧ በእሜም እኩያዋ ነው፡፡ ፊቱ ሁል ጊዜ ፈገግታ አይለየውም፡፡ በአእምሮ የበሰለ አስቂኝና ተጫዋች ሲሆን ባህሪው ልስልስ ያለ በአለባበሱ ሸጋና ፅዱ ነው የሞዛርትን ሙዚቃ የሚወድ ሲሆን ከሁሉም በላይ ግን ዳያናን ወዷታል።
እስካሁን የምታውቃቸው ወንዶች ገላዋን መተሻሸት የሚወዱ፣ ባሏ መርቪን ጀርባውን ማዞሩን አይተው እንተኛ የሚሏት፣ በመጠጥ የደነበዙና ካንቺ ፍቅር ይዞናል እያሉ የሚቀባጥሩ ዓይነት ናቸው፡:
መቼም እሷን ሳይሆን ገላዋን እንደሚፈልጉ ታውቃለች፡፡ ንግግራቸው
የማይጥም ፍሬፈርስኪ ሲሆን እሷ የምትለውን ለመስማት አይፈልጉም፡፡
ስለእሷም ማወቅ ችግራቸው አይደለም:: ማርክ ግን ከነሱ ለየት ያለ ሰው መሆኑን ከቀን ወደ ቀን ማወቅ ችላለች፡፡
መጻሕፍት ቤት በተገናኙ ማግስት መኪና ተከራየና ባህሩ ዳርቻ ወስዶ
አዝናናት፤ ሳንድዊች ጋበዛትና ከለል ያለ ቦታ ፈልገው ተሳሳሙ፡፡
ማርክ ሚድላንድ ሆቴል አልጋ የያዘ ቢሆንም ዳያና እዚያ በጣም ታዋቂ በመሆኗ ከሱ ጋር መግባት አትችልም፡፡ ከምሳ በኋላ እዚያ ከወንድ ጋር ስትገባ ብትታይ በመክሰስ ሰዓት ወሬው በከተማው በሙሉ ይዳረሳል፡በመሆኑም የማርክ ፈጣን አዕምሮ አንድ ነገር ዘየደ፡፡ ሌላ የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኝ ከተማ በመኪና ሄደው ሻንጣ አንጠልጥለው ሆቴል ደረሱና አቶ እና ወይዘሮ አልደር ብለው ተመዝግበው አልጋ ያዙ፡፡ ከዚያም ምሳ በሉና አልጋ ላይ ወጡ፡፡
ማርክ በፀጥታ ልብሱን ማወላለቅ ጀመረ፡፡ እሷ ደግሞ እፍረት ስለያዛት
ልብሷን ያወላለቀችው በሳቅ እየተንከተከተች ነው፡፡
BY 📚 Book center የመፅሐፍት ማዕከል 📚
Share with your friend now:
tgoop.com/yisakgizaw/6901