tgoop.com/yismakeworku/806
Last Update:
ወዳጄ በእውቀቱ እንደፃፈው... #ሼር አድርጉት!
የሚያሳስበኝ
(በእውቀቱ ስዩም)
ዶስተየቨስኪይ የተባለ የሩስያ ደራሲ ልቦለድ ውስጥ የሚገኝ ኢቫን የተባለ ገጸባህርይ ” ሰውን አውሬ ብሎ መጥራት አራዊትን እንደ መስደብ ይቆጠራል ይላል ፤” ሰው የበጎነት አቅም ያለውን ያህል ፥ በጭካኔ የሚወዳደረው የእንስሳ ዝርያ የለም፤ አንበሳ ሚዳቆን የሚገድለው በልቶ ማደር ስላለበት ነው፤ ሳይቸግረው ያለ አላማ መሰሉን፥ የሚገድል፥ ብጤውን በማሰቀየት የሚደሰት ፍጡር ሰው ብቻ ነው፤
ልጅ ሆኜ በጎችን አሰማራ ነበር፤ ግልገል በግ የሚደፍር ትልቅ በግ አይቼ አላውቅም ፤ ወንዱ በግ ፥ደረሰች በግ ላይ ለመውጣት ራሱ ወቅት ይጠብቃል፤ ለርቢ መድረሷን አሽትቶ ካላረጋገጠ በቀር አይደርስባትም፤
የሰባት አመትዋን ሄቨንን ለመስማት በሚገዘገንን ጭካኔ ደፍሮ የገደላትን ሰውየ “ እንስሳ ፥ወይም አውሬ” ብሎ መጥራት ፍትሀዊ የማይሆነው ለዚህ ነው፤ እንዲህ አይነቱ ቀፋፊ ፍጡር የሚገልጽ ሌላ ቅጽል ተፈጥሮ መዝገበቃላት ውስጥ መካተት አለበት፤
ህግ ካለ ይህ ወንጀለኛ እንደ ምግባሩ ፍዳውን መቀበል ይገባዋል፤ እሱ ብቻ ሳይሆን ወንጀሉን ለመሸፋፈን የሞከሩ እና የዶለቱ ሁሉ ከቅጣቱ ድርሻቸውን ማንሳት አለባቸው፤
አስገድዶ ደፈራ በዋናነት የወሲብ ጉዳይ አይደለም፤ የፈሪዎች እና የግፈኞች “ሀይል “ መግለጫ ነው፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰባ ምናምን አመት ሴት የደፈረ ጎረምሳ በአስራት መቀጣቱን የሚገልጽ ዜና ማንበቤ ትዝ ይለኛል ፤ የሰባ አመት ባልቴት እና የሰባት አመት ሴት ሁለቱም ለሩካቤ የሚያሳስብ ነገር የላቸውም፤ ግን ሁለቱም አንድ የሚያደርጋቸው አቅም አልባ መሆናቸው ነው፤ ራሳቸውን ከደፋሪው መከላከል አይችሉም፤ ደፋሪዎች ብዙ ጊዜ ፈሪዎች ናቸው፤ ከሚበልጣቸው ጋራ ወይም ከእኩያቸው ጋራ ጉልበት እንደማይፈታተሹ ያውቁታል፤ በጉልበት የሚያንሳቸውን፤ ሀብት ስልጣን ወይም ወገን የለውም ብለው የሚያስቡትን ከማጥቃት ግን አይመለሱም፤ ብዙ ጊዜ የጥቃት ሰለባዎችን ስናይ ህጻናት፥ የቤት ሰራተኞች፥ እንግዶች፥ የመንገድ ዳር ተዳዳሪዎች ወይም በጦርሜዳ ላይ ያለ ታዳጊ የቀሩ ሴቶች ናቸው፤
ለወላጆች አንድ የጭንቅ ቀን ምክር አለኝ፤ ጨካኝ ፤ጭቦኛና ቀፋፊ ባህርይ ያላቸው ሰዎች
የትም እና መቼም ይኖራሉ፤ሰርሲ ላንስተር እንደተናገረችው Everywhere in the world they hurt little girls ."
ፈታኝ አለም ውስጥ እንደምንኖር አንርሳ፤ ሁሌም በህግ በፈሪሀ እግዚአብሄር እና በባህል በጭምት ፊት ተማምነህ መዘናጋት የለብህም፤የልጆችህ ወታደር መሆን አለብህ ፤ ልጆችሽን እንደ አይንሽ ብሌን ጠብቂ ! ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ግን ሌላ ምን አማራጭ አለ?
#ሼር አድርጉት
BY Yismake Worku
Share with your friend now:
tgoop.com/yismakeworku/806