tgoop.com/youthkiper/11746
Last Update:
ጥሮ አደር እንጂ አውርቶ አደር ምኞቱን አያሳካም!!
በከፈለኝ ዘለለው [ሐዋዝ]
ማዘናችን ለመደሰታችን ዋዜማ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ጣፍጦ አልተሰጠንም፡፡ መኖርም ያልጣፈጠውን የማጣፈጥ ረጅምና አድካሚ ጉዞ ናት፡፡ የተፈጠርነው የሚያስቸግረንን ችግር አስቸግሮ ለመኖር ነው፡፡ ለችግራችን ተንበርካኪ ሳይሆን ችግሮቻችንን አንበርካኪ እንሁን!! እንዳዘራራችን አስተጫጨዳችን ይወሰናል፡፡ በመሆኑም … ለሕልማችን ሟች እንጂ ሕልማችንን አሟች አንሁን፡፡ ‘መሸመን ጀምር እግዜር ክሩን ይሰጥሀል ነውና በጣርነው ልክም ወደ ስኬት እንጠጋለን፡፡ መልፋት ካልቻልን መገፋታችን አይቀርም፡፡ ሕይወት የጎደለብንን ለመሙላት የምንሮጣት ሩጫ ናት።
እኔ … ሲያጥቡት የማይጠራ ዕድፍ እንዳለ አላምንም፡፡ ግና አጣቢውና አስተጣጠቡ ለዕድፉ መጥራትና አለመጥራት ወሳኞች ይሆናሉ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን … ጥረት ከ … እስከ የሚባል ወሰን የለውም፡፡ ጥረታችን እስትንፋሳችን ስትቆም የሚቆም እንጂ በደከመንና በሰለቸን ቁጥር ከላያችን አውርደን የምንጥለው ወቅታዊ ሸክም አይደለም፡፡ ከሕይወት ምንጭ እስከ መኖር ጥግ ድረስ እየጣርን መኖር ይጠበቅብናል፡፡ ምንያቱም የምንደርሰው ስንራመድ ብቻ ነውና! ጣፋጭ ፍሬዎች በሙሉ መራራ መስዋዕትነትን ያስከፍላሉ፡፡ ሣር ካልሰጠናት ላም ወተትን ማግኘት ስለማይቻል ለውጣችንን ቁጭታችን ውስጥ ሳይሆን ሩጫችን ውስጥ እንፈልግ፡፡
በእርምጃችን ወቅት የሚያጋጥሙን ብዙ አስቸጋሪ ደመናዎች ይኖራሉ፡፡ ግና … መከራና ጉም እያደር እንደሚቀሉ እንመን፡፡ ተራምደን ደራሽ ለመሆን ጀምሮ ጨራሽ መሆን ያሻናል! እየለመለምን የምንረግፍ ሳይሆን እያበብን ፍሬ የምንሰጥ ዘሮች ለመሆን ራሳችንን የራሳችን አረም ከማድረግ እናቅብ፡፡ ስኬት የብዙ ውጣ ውረዶች ድምር ውጤት ናት፡፡ እናም የጣፈጠውን ለማጣጣም የመረረውን ቀምሶ ማለፍ አያስጠላን፡፡ ጠግቦ አዳሪ ለመሆን ለፍቶ ኗሪ መሆን የውድ ግዳችን ነው፡፡ ጥሮ አደር እንጂ አውርቶ አደር ምኞቱን አያሳካም፡፡ ሳይሰሩ እያፈሩ እንጂ እየኮሩ የኖሩ የሉም፡፡ በኩራት ለማምሸት በትጋት እንዋል፡፡ ያማረ ነገን ለመፍጠር የተዋበ ዛሬን መኖር እንቻል። አስቸጋሪ ችግሮች ወደ አስደሳች ነገሮች መሸጋገሪያ ድልድዮቻችን ናቸው፡፡ የምንኖረው ከችግሮች ነፃ በሆነች ምድር ላይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ችግሮቻችንን የመሸሽ ሳይሆን ችግሮቻችንን የማሸሽ ሥራ እንስራ፡፡
BY ወጣቱ ና ሙዱ
Share with your friend now:
tgoop.com/youthkiper/11746