tgoop.com/zebisrat/366
Last Update:
ስንት ሰው ገደልክ?
ባላወቁት ጉዳይ ባልተሳተፉበት ተግባር ምክንያት የሞቱትን ነፍስ ፈጣሪ በክብር ይኑረው።
በቁም ሞተው ፥ "የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም" በሚሉት ብሂል የነፍስን ሞት ያልፈሩ ገድሎአደሮች ፤ እጃቸውን በሰው ደም ታጥበው ከስብዕና ከነጹ በኋላ ለሚኖሩለት ስጋ መደንደን ሲሉ በላቡ ደረቅ መሬትን አርሶ አለምልሞ ጥሬ ለገበያ የሚያበቃውን ገበሬ ፣ እሳት ጋር ታግላ እንጀራ የምትጋግረውን እናት ገድለው የእጃቸውን ፍሬ እየበሉ ነው።
በዚህ መሃል አንዱ ገድሎአደር "ስንት ሰው ገደልክ?" የሚል ጥያቄውን ወደ ሌላኛው ገድሎአደር ወረወረ። ጥያቄውን የሰማው ገድሎአደር መመገቡን አቁሞ መሳርያውን እየወለ የገደለውን ሰው ቁጥር ተናገረ። ጠያቂው ገድሎአደር በንቀት አይኑ እየተመለከተው "የገደልከው ሰው ትንሽ ነው" ብሎ ወቀሰው። ገድሎ አደሩ እንዲያማ ካልከኝ አለና የገደለው ሰው ቁጥር እንዲበዛለት ወደ ተለመደ ገድሎአደርነቱ ሄደ።
ለነገሩ ልክ ነው ገድሎአደር አይደል! ለወሬውም በመቶ የሚቆጠር ሰው ሲገድል ይሻለዋል። ሲናገርም አፉ ላይ ሞላ ያለ ይሆናል። ጀማሪ ገዳይ ይመስል የምን ትንሽ ሰው መግደል ነው ከገደሉ አይቀር ገድሎአደርነትን በሚያሳይ መልኩ በዛ አደርጎ ነው እንጂ...
ብዙ ሰው የመግደል ጉዳይ በአንድ ወቅት አንድ ታላቅ ንጉስና አንድ ታናሽ ብላቴናን አጣልቶ ለመጋደል አድርሷቸው ነበር። ንጉሱ ሳውል እና ታናሹ ብላቴና ዳዊት "ሳውል መቶ ገደለ ዳዊት እልፍ ገደለ" በሚል ሙገሳ ተነሳስተው "እንዴት እሱ ከኔ በላይ ይገድላል?" ቅንዓት እርስ በርስ ሰይፍ ተማዘዋል።
የእነርሱን እንተወውና የዘመናችንን ገድሎአደሮች እናስባቸው እስቲ! እንዴት ነው ግን ሰው እንደዚህ የተጨካከነው? ምንም እንኳን ገድሎአደር ቢሆንም ስራንም በአግባቡ መወጣት እኮ መልካም ነው። እንስሳ እንኳን ሲገደል ላለማሰቃየት ይሞከራል እኮ! ይሄ ሁሉ ክፋት ምን ያደርጋል?!
ግን እኛንስ ማን እነርሱ ላይ ፈራጅ አደረገን! እነሱስ አንደኛውን ገድሎ አደር ሆነው ከአምላካቸው የሚሰጣቸውን ፍርድ ይቀበላሉ። እኛ ስንቱን ሰው ነው በነፍስ የገደልነው?
ወዳጄ አትደናገጥ መልሼ ልጠይቅህ
እኔና አንተስ ስንት ሰው ገደልን?
ለስንቱ ሰው ሞት ጥይት የሆነ መግደያ መሳርያን በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌላ አማራጭ ላይ አቀረብን?
ስንቱ ሰው በኛ ድርጊት ተሰናክሎ ሞተ?
መቼም "አትግደል" የሚለው የፈጣሪ ትዕዛዝ ትርጉሙ ስጋን መግደል ብቻ እንዳልሆነ "ስጋን የሚገድሉትን አትፍሩ ነፍስን የሚገድሉት ፍሩ" ሲል ፈጣሪ በተናገረው ቃል በግልጽ አስረድቶናል።
በስጋ መግደሉ እኮ ቀስ በቀስ እያደገ የሚመጣ የገድሎአደርነት ብቃት ነው። እኔ እና እናንተ ዛሬ ላይ ገድሎአደር ለመሆን እንችል ዘንድ ራሳችንን ከጸልዮአደርነት ፣ ከአመስግኖ አደርነት ፣ ከአስቀድሶ አደርነት ፣ ከአንብቦ አደርነት. .... አውጥተን ወደ ገድሎ አደርነት ለማደግ እየሞከርን ነው። ለዚህም ነው መሰል እውነታውን የገድሎአደርነት ጉብዝና ከመረጃ እና ከፊልም (የውሸት ነው እያልን) ስናጠናው የምንውለው!
አዎን ገድሎ አደርነት ብቃት ነው ነገ "ይህን ያህል ሰው ገደልኩ" ብለን በኩራት እንድንነጋገር ዛሬ ላይ ብዙ ጥሩአደርነቶችን ትተን ገድሎአደርነትን መለማመድ አለብን። እኛ ግን ይበልጥ ልንፈራ የሚገባን ስጋን ሳይሆን ነፍስን የምንገድል ገድሎ አደሮች ነን። ዛሬ ላይ ሞት የማይቀርላት ስጋን የገደሉትን ሰዎች እየኮነንን ነፍስን የምንገድል ራሳችንን ማመጻደቃችን "በአይንህ ያለውን ግንድ ሳታወጣ በወንድምህ አይን ላይ ያለው ጉድፍ እንዴት ሊታይህ ይችላል" ያስብላል።
ጠላት ዲያቢሎስም ራሳችን የገደልናቸውን ሰዎች ደም ከእጃችን በንስሃ እንዳናስለቅቅ በማሰብ ዘወትር ሰው የገደለው ላይ እንድናተኩር አድርጎናል። በሌሎች ገድሎ አደሮች ላይ መፍረዳችንን ትተን እያንዳንዷን ቀን ውለን ከማደራችን በፊት ምን እንደምናደርግ እናስተውል! ውሏችንን በአግባቡ እንፈትሽ። በስተመጨረሻ ከገድሎ አደሮች ጋር ከመሰለፍ እንድን ዘንድ ዛሬ ላይ አዋዋላችንን አኗኗራችንን ከጽድቅ ሰርቶ አደሮች ጋር ፣ ከእውነትን መስክሮ አደሮች ጋር.... እናድርግ። ሰው ነንና ደግሞ ለስጋችንም ለነፍሳችንም መብል የሆነ የጌታችንን ክቡር ስጋና ቅዱስ ደም ከመቀበል ወደ ኋላ አንበል። እንዴት ሳይበላ ይኖራል! ያውም በኛ ስንፍና!
ለማንኛውም እስካሁን "ስንት ሰው ገደልክ?" "ስንት ሰው ገደልሽ?" "ስንት ሰው ገደልኩ?" በሉ ተነሱ ቶሎ ንስሃ እንግባ።
ዲያቆን ዳዊት ናሁሠናይ (ዘብሥራት)
ሐምሌ 2014 ዓ.ም
ወለቴ
👇👇👇👇
👉 @zebisrat👈
👆👆👆👆
BY ዲያቆን ዳዊት ናሁሠናይ (ዘደብረ ብሥራት)
Share with your friend now:
tgoop.com/zebisrat/366