tgoop.com/zebisrat/368
Last Update:
እረኛ ካህን
ይገርምሃል እኛ የእግዚአብሔር በጎች ነን (ፍየል አለመሆናችንን እንኳን እርግጠኛ አይደለሁም) የምንበላውን የምንበላበትን ቦታ የማናውቅ በጎች ፣ ጠላት በፈለገ ጊዜ አርዶ አወራርዶ ለክፋት ተግባር የሚያውለን በጎች ፤ ለዚያም ነው እግዚአብሔር ያለ እረኛ በዚህ አለም ላይ ሊተወን ያልፈቀደው።
የእኛ በግነት በእድለኝነት ነው። ምክንያቱም በርካታ በጎ እረኛዎች አሉንና። ነገር ግን ይህን እድለኛነታችንን አገናዝበን በአለም ውስጥ ያለ ምክንያት ከመቅበዝበዝ የዳነው ስንቶቻችን እንሆን?!
የኛን በግነት እንያዘውና ስለ እረኞቻችን እናውጋችሁ። እኒህ እረኞቻችን ስለ እኛ እጅግ ብዙ ዋጋ ይከፍላሉ። ለነገሩ ዕለት ዕለት ታላቅ እረኛ የሆነ የዳዊት መዝሙር እየደገሙ እንዴት ዋጋ የማይከፍል እረኛ መሆን ይቻላል።
እረኞቻችን እኛን ለመመገብ ዘወትር የጌታችንን ስጋና ደም ይዘው በቅዳሴ ይሰየማሉ ፣ ነፍሳችንን ንፁህ ለማድረግ ለማሰብ የከበደ ኃጢአታችንን እያራገፍንባቸው እነሱ ግን ለኛ ድህነት ይፀልያሉ ለድህነታችንን የሚጠቅመንን ነገር ይነግሩናል ፣ እኛ ለራሳችን የተወሰነች ደቂቃ በጸሎት መቆም ተስኖን ሳለ እነሱ ግን እኛ በምንተኛበት ለሊት ክርስትና ስማችንን እየጠሩ ይጸልዩልናል ፣ በህመም ውስጥ ሆነው እንኳን ከስጋ በሽታ የነፍስ በሽታ ይከፋልና የኛን የነፍስ በሽታ ለማከም ይጥራሉ ፣ . . . .
ካህናት የነፍስ እረኛ ናቸው። በግ ያለ እረኛ ሲሄድ አውሬ እንደሚበላው ሁሉ እኛም ያለ ካህናት እርዳታ ስንሄድ የአውሬ ምግብ መሆናችን አይቀርም። ለዛ ነው አውሬው ቅድሚያ ልብላችሁ ከሚለን ይልቅ ከካህናት ጋር የሚያጣላን። ከካህናት ጋር ተጣልተን ያለ እረኛ ስንቀር ያኔ እኛን መብላት ቀላል ነው።
እኛ ያለ ካህናት ስንሄድ የአውሬው ምግብ ከመሆናችንም በላይ በረሃብ እንሞታለን። ነፍሳችን ምግቧ የእግዚአብሔር ቃል ብሎም ስጋ ወደሙ ነው። ያለ ካህን ደግሞ የጌታን ስጋና ደም ማግኘት አይቻለንም። አሁን እኮ ስጋችንን ሸፍኗት ነው እንጂ ነፍሳችን ብትታይ በታሪክ በ77 ድርቅ ተብሎ እንደሚታዩ ሰዎች የሚታዘንልን በረሃብ ውስጥ ያለን ምስኪኖች ነን።
ታዲያ ወዳጄ አሁን ተነስ አትዘግይ እረኛህን ፈልጋቸው። ከስራቸው ቁጭ ብለህ ያለ እረኛ የኖርክባቸውን ቀናቶች አስታውሰህ መሳሳተህን ንገራቸው። አይዞህ እንደ ዘመናችን ፍርድ ስፍራ ጥፋትህን ብታምንም ቅጣት አይቀርልህም አይሉህም ይልቁኑ አይዞህ ልጄ ብለው ያፅናኑሃል። እርግጥ በሚያዝን ልባቸው አስታውሰው የተወሰነ ስግደት የተወሰን ምፅዋት የፆም ቀንም ይሰጡህ ይሆናል። ግን እኮ ይሄ ሁሌ ማድረግ ያለብን ነገር ነበር ያው በዚህ ምክንያት ቀስ በቀስ መንፈሳዊነቱን ይለምድ ይሆናል ብለው እንደሆነ አትዘንጋ።
ለማንኛውም የብዙዎች እረኛ የሆኑ አባቶቼ እነሆ
#መምህር #ቀሲስ ናሁሠናይ ተሾመ
ነፍሰ ሄር #ቄሰ ገበዝ ሠርገወርቅ ተሾመ እና
ክብርት ባለቤቱ ወ/ት አልጋነሽ ተሾመ
አንድ ቀን ደግሞ ስለ ካህናት ሚስቶች የመጣልኝን እፅፍ ይሆናል
ዲያቆን ዳዊት ናሁሠናይ
ጥቅምት 19 2015 ዐ.ም
ብስራተ ገብርኤል
BY ዲያቆን ዳዊት ናሁሠናይ (ዘደብረ ብሥራት)
Share with your friend now:
tgoop.com/zebisrat/368