tgoop.com/zebisrat/371
Last Update:
የቤት ስራ ሲበዛ
በተለያዩ የክፍል ደረጃዎች በተማርንበት ዘመን እኒያ "ለኛ የቤት ስራ ከመስጠት ውጪ ስራ የሌላቸው" የሚመስለን መምህራን home work ብለው በነጩ ቾክ ጥቁሩ ሰሌዳ ላይ የሚሞነጭሩት የቤት ስራ አሰልቺ ነበር።
ታዲያ ከትምህርት ቤት ውሎ ተመልሰን ጨዋታ እንደጀመርን ሰአቱ እንዴት እንደሄደ ሳናቅ ጨለምለም ሲል በወላጆቻችን ጥሪ ወደቤት እንገባና ተጣጥበን ቦርሳችንን አውጥተን የቤት ስራ ጋር እንፋጠጣለን።
አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ መምህራን የቤት ስራ ሰጥተውን የቤት ስራውን መስራት ከመጀመራችን በፊት ያለንን የቤት ስራ ብዛት ስናረጋግጥ የቤት ስራው ይበዛና ተስፋ በመቁረጥ አንድ አማራጭ እንጠቀማለን። ኹሉንም የቤት ስራ አለመስራት
ወይ ልጅነት! ለማይቀር የቤት ስራ ኹሉንም አለመስራት መፍትሔ ሆኖ ለብዙ ጊዜ አገልግሎናል። ከዚያም ደግሞ አንግ የተለመደች ጸሎታችንን እናደርሳለን። የጸሎታችን ጽንሰ ሃሳብ መምህሩ ወይ ቀርቶ ወይ በሌላ መንገድ ብቻ የቤት ስራ መስራት አለመስራታችንን እንዳያረጋግጥ የሚቀርብ ልመና ነበር።
ልጅነት የዋህ ነውና ስንፍናችንን በመምህራችን ክፍተት ለመሸፈን የምናቀርበው ጸሎት አለመሳመቱም ያናደደን ጊዜ በርከት ያለ ነው።
የሚገርመው ነገር አመታት አልፈው ጊዜያት ተቆጥረው ይሄንን ነገር ለመተው አለመቻላችን ነው። ይህ ባህሪ የጋራ ሆኖ እንደ ሃገር ያሉብን የቤት ስራዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ኹሉንም እየሰራን አይደለም! እንደ ግለሰብ ለመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በምድር ለሚኖረን ቆይታ መስራት ያለብንን ብዙ የቤት ስራ እየሰራን አይደለም! እንደ አንድ ክርስቲያን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መስራት ያለብንን በርካታ የቤት ስራ ላለመስራት ኹሉንም አጣጥፈን አስቀምጠን ባተሌ ሆነናል!
የበዛ የቤት ስራ ቢኖርም የሚሰራ የቤት ስራ ግን የለም። ትልቅ ተቃርኖ! የቤት ስራውን ባለመስራታችን ለሚመጣው ችግር ደግሞ ተጠያቂ ልናደርግ የምንችለውን ሰው እንፈልጋለን።....
እስቲ ያሉንን የቤት ስራ እናስታውሳቸው እንደ ሃገር እንደ ቤተ ክርስቲያን እንደ ግል... ብዙ ናቸው።
እንደው መስራቱ እንኳን ቢቀር አንዳንድ ቅዱሳንን ጀግኖችን ስናከብር የቤት ስራቸውን ከሚገባው በላይ ሰርተው ያለፉ እንደሆኑ አንዘንጋ። ክፍሉ ውስጥ የቤት ስራውን በአግባቡ የሰራ ሰው እንደሚጨበጨብለት በሕይወት ጎዳና የቤት ስራቸውን ለሰሩ ሰዎች ጭብጨባ ከማቅረብ አንድከም።
ምናልባት አንድ ቀን ለጭብጨባ የሚጣደፉ እጆቻችን የራሳችንን የቤት ስራ ለመስራት ተግተው ሌሎችን ማስጨብጨብ ይቻላቸዋል።
ዲያቆን ዳዊት ናሁሠናይ (ዘብስራት)
ሐምሌ 7 2015 ዓ.ም
4 ኪሎ
@zebisrat
BY ዲያቆን ዳዊት ናሁሠናይ (ዘደብረ ብሥራት)
Share with your friend now:
tgoop.com/zebisrat/371