tgoop.com/zikirekdusn/24434
Last Update:
+ቅዱስ አግናጥዮስ የተወለደው በክርስቶስ አምላካችን መዋዕለ ስብከት (በ30 ዓ/ም አካባቢ) እንደ ሆነ ይታመናል:: በትውፊትም በማቴ. 18:1 ላይ ያለው ሕጻን እርሱ ነው ይባላል::+ሐዋርያት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ሲጠይቁት አንድ ሕጻንን (አግናጥዮስን) ከመሃል አቁሞ "ካልተመለሳችሁ: እንደዚህም ሕጻንካልሆናችሁ ከቶውንም ወደ እግዚአብሔር መንግስት አትገቡም" ብሏቸዋል::
+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ሐዋርያት ለወንጌል ሲፋጠኑ ሕጻኑ ቅዱስ አግናጥዮስ እየተከተለ አገልግሏል: ተምሯል:: ኢየሩሳሌም በጥጦስ አስባስያኖስ ቄሣር በጠፋችበት ዓመት (በ70 ዓ/ም) ቅዱሱ የአንጾኪያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሟል::
+ከዚህ በሁዋላም ለ2 እና 3 አሠርት ዓመታት ከወንጌላዊ ዮሐንስ ጋር አብሮ ወንጌልን ሰብኩዋል:: የዚህ ቅዱስ ተጋድሎ ጫፍ የደረሰው ከ100 ዓ/ም በሁዋላ ሁሉም ሐዋርያት ሰማዕት በመሆናቸውና ትልቁን ኃላፊነት እርሱ በመሸከሙ ነው:: የወቅቷን ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳኑ ቀሌምንጦስ ዘሮምና ፖሊካርፐስ ዘሰርምኔስ ጋር ሆኖ እስከ ደም ጠብታ ጠብቁዋል::
+ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ አግናጥዮስ ለዘመናት ወንጌልን እየሰበከ በሕይወቱና በትምሕርቱ አስተማረ:: ብዙ መልእክቶችን (ድርሳናትንም) ጻፈ:: በመጨረሻው ግን በጠራብሎስ ቄሣር ተይዞ: በብረት ሰንሰለት ታስሮ: ከአንጾኪያ (ሶርያ) ወደ ሮም (ጣልያን) ተወሰደ::
+ደሙ እስኪፈስም ገረፉት:: ዛሬ በሮም ከተማ ግማሽ አካሉ ፈርሶ በሚታየው ስታዲየም (በአባቶቻችን አጠራር ተያጥሮን) እንዲገደል ተወሰነበት:: በወቅቱ ባደረገው ንግግርም ቄሣሩና ሕዝቡ ድፍረቱን አደነቁ:: በመጨረሻም ለአንበሳ እንዲሰጥ ተደርጐ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነ::
+" ቅድስት አስቴር "+
=>ይህቺ ቅድስት እናት:-
*እሥራኤል በባቢሎን ምርኮ ሳሉ የነበረች
*አባቷ አሚናዳብ ባለ መኖሩ በአጐቷ መርዶክዮስ እጅ ያደገች
*እጅግ ውብ በመሆኗ የአርጤክስስ ሚስት (ንግሥት) ለመሆን የበቃች
*ራሷን መስዋዕት አድርጋ ወገኖቿን አይሁድን ከሞት ያተረፈች
*ለመርዶክዮስ ክብርን: ለአማሌቃዊው ሐማ ደግሞ ስቅላትን ያስፈረደች እና
*እግዚአብሔር ሞገስ የሆናት እናት ናት::
*ዛሬ ዕረፍቷ ነው::
=>አምላከ ቅዱሳን ወዳጆቹን ባጸናበት ቅዱስ መንፈሱ እኛንም ያጽናን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱሳን ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኃረያ
3.ቅዱስ አግናጥዮስ ሐዋርያ
4.ቅድስት አስቴር
5.አባ ፊሎንጐስ ሊቀ ዻዻሳት
6.አባ ዻውሊ ጻድቅ
7.ጻድቃን ቅዱሳን ዘከዲህ
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
2.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
3.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
4.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
5."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
6.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
=>+"+ ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ:- 'ንጉሥ ሆይ! በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ: ንጉሡንም ደስ ቢያሰኘው: ሕይወቴ በልመናዬ: ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ:: እኔና ሕዝቤ ለመጥፋትና ለመገደል: ለመደምሰስም ተሸጠናልና:: +"+ (አስቴር. 7:3)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
BY ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)
Share with your friend now:
tgoop.com/zikirekdusn/24434