tgoop.com/DIYAKONAE/3756
Last Update:
🔴 #ማክሰኞ_የትምህርት_እና_የጥያቄ_ቀን
ይህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ በተናገረው ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡
ሰኞ ቀን ጌታችን በረገማትን በለስ መድረቅ ሐዋርያት ሲደነቁ እምነት ያለው ሰው ሁሉን ማድረግ እንደሚችል ያስረዳበት ዕለት ነው፡፡
‹‹ ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት ጴጥሮስም ትዝ ብሎት መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ በእግዚአብሔር እመኑ እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም። ››ማር 11፥20-26 እያለ ያስተማረበት ዕለት ስለሆነ የትምህርት ቀን ይባላል
ሌላው ይህ ዕለት ጌታችን ሰኞ ዕለት ካደረጋቸው ነገሮች ተነስተው አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት ዕለት ነው
‹‹ ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው? አላቸው። . . . ›› /ማቴ 21 ፥23- 27/
ይህ ጥያቄ ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀረቡት ጥያቄ ነበር ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበረውን ገብያ ስለበተነው የነጋዴዎቹን መደባቸውን ስለገለበጠ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነውና በማን ሥልጣን አደረከው ብለው ጠየቁት ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን›› ቢላቸው ጸረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው
ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?›› ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት ‹‹ለምን አላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው›› ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው ከዚህ ታሪክ የተነሳ ይሄ ቀን የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡
https://www.tgoop.com/DIYAKONAE
BY ትምህርተ ኦርቶዶክስ
Share with your friend now:
tgoop.com/DIYAKONAE/3756