tgoop.com/DrYonasLakew/2579
Last Update:
የጤና ባለሞያ መንደድ (Health Care Burnout)
================================
አንዳንድ ጊዜ ትሰራ ትሰራና ድክም ይልሀል። አሁንም መስራት ከቀጠልክ ትዝላለህ። አካልህም ስሜትህም ሲዝል መንደድ (Burn out) ይከተላል። የጤና ባለሞያዎች መንደድ በአለማችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እየተሰጠው ነው።
የጤና ባለሞያው ከመዛል አልፎ መንደድ ላይ ሲደርስ ከፍተኛ ሀዘን ይሰማዋል፣ እንቅልፍ አይኖረውም፣ ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት ይሻክራል፣ የተለያዩ መድሀኒቶች መጠቀም ሊጀምር ወይም ራሱን ሊያጠፋ ይችላል። (በሚያሳዝን ሁኔታ በሀገራችንም ራሳቸውን ያጠፉ የጤና ባለሞያዎች አሉ።) ተፅእኖው ባለሞያው ላይ ብቻ ተወስኖ አይቀርም። ታካሚዎች በሙሉ ልብ የሚያዳምጣቸው አይኖርም፣ የሚያገኙት ህክምና ጥራቱ ይቀንሳል። የጤና ተቋሙም ቢሆን ውጤታማነቱ ይወርዳል። ዝውውር የሚጠይቁ፣ ስራ የሚቀሩ እና የሚለቁ ሰዎች ስለሚበዙ ወጥነት ያለው አገልግሎት መስጠት አይችልም።
መንስኤው ምንድነው?
መንደድ እንዳይከሰት የሚከላከሉት ሁለት ነገሮች ናቸው። የግለሰቡ ጥንካሬና (Individual resilience) የተቋም ቅልጥፍና (Organizational efficiency)። የግለሰብ ጥንካሬ ለማዳበር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ...ወዘተ አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም የእነዚህ ሚና ከ20 ከመቶ አይበልጥም። ዋናው የተቋም ቅልጥፍና ነው።
ለምሳሌ አንድ ሀኪም በጥራት በአንድ ቀን ውስጥ ማየት ያለበት አስር ታካሚ ቢሆንና ለስራው ደግሞ የኩላሊትና የጉበት ምርመራ የሚያስፈልገው ቢሆን የሚሰራበትን ሆስፒታል አስተዳደር የተበላሸውን የኩላሊትና የጉበት ላብራቶሪ እንዲያሰራ ነግሯል እንበል። ዛሬ ነገ እየተባለ ለወራት አልተሰራም። ለሊት ተረኛ ሆኖ እንቅልፍ ሳይተኛ አድሮ የቀን ስራው ላይ ተገኝቷል። "የግዴታ ሰላሳ ታካሚ ነው ማየት ያለብህ!" ተብሎ ሰላሳ ካርድ ሲመጣለት አስቡት። "ብዙ የተመረቁ ሀኪሞች አሉ፤ እኔ ሰላሳ ታካሚ ላጥላጥ እያደረግሁ ከማክም ሁለት ተጨማሪ ሀኪም ተቀጥሮ ታካሚዎቹ በደንብ ቢታዩ ጥሩ ነበር።" ብሎ ማሰቡ አይቀርም። ለታካሚዎቹ ብቻ ሳይሆን ለራሱም በማሰብ። ቀጥሎ የኩላሊት ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችን እየደበረው "ውጭ አሰሩ" እያለ ይልካል። ታካሚዎቹም "እሺ" እያሉ ለማሰራት ይሄዳሉ። አንድ በእድሜ አባቱ የሚሆኑ ታካሚ ግን "ምንም ብር የለኝም ልጄ። እዚሁ እናንተ ጋ አሰራልኝ ተባበረኝ" ይሉታል። "እኛ ጋ የለም" ብሎ ሲያያቸው ያሳዝኑትና "በቃ በዚች አሰሩ" ብሎ ከሚያገኛት እጅግ አነስተኛ ደሞዝ ለታካሚው የላብራቶሪ ማሰሪያ የተወሰነ ብር ይሰጣቸዋል። ይህ እሽክርክሪት በተለያየ ቀን በተለያየ መልክ ሲደጋገም አስቡት።
በጣም የደከማቸው የጤና ባለሞያዎች አሉ። ለእነሱም ለሚያክሙትም ሰው ስንል ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
Physician, first heal thyself. መፅሀፍ ቅዱስ ሉቃስ 4:23 ላይም "...ባለ መድሀኒት ሆይ፥ ራስህን ፈውስ..." ይላል።
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!!!
በዩቲዩብ ተቀላቀሉ https://www.youtube.com/@dryonaslakew3386
ዶ/ር ዮናስ ላቀው
BY Mental wellness የአእምሮ ጤና
Share with your friend now:
tgoop.com/DrYonasLakew/2579