tgoop.com/DrYonasLakew/2582
Last Update:
የለውጥ ሂደቶች
▪️ሰዎች በህይወት ዘመናቸው በተለያዩ የለውጥ ሂደቶች ያልፋሉ:: ለውጥ በአንድ ጀምበር አይመጣም:: ሂደት ነው:: ብዙ መውደደቅና መነሳቶች: ብዙ ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያቶች ታልፈው ነው ስኬት ላይ የሚደረሰው:: ምናልባት አንዳንዶቹ እድል: ብርታት ወይንም ብልጠት በታከለበት ሁኔታ ነገሮች ቶሎ ተፈጽመውላቸው ይሆናል::
▪️እንደ Prochaska እና DiClemente እይታ ከሆነ: መለወጥ በሽክርክሪት ይመሰላል::
▪️ ለዛሬ ለዚህ ጽንሰ ሃሳብ አስረጅ እንዲሆነን: ሱስ የማቆም ሂደትን እንመለከታለን
▶️ Pre-contemplation/ቅድመ ውጥን:-
▫️ በዚህ የለውጥ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች ስለችግሮቻቸው ያላቸው ግንዛቤ እምብዛም ነው::
▫️ብዙ ሱስ አስያዥ እጾችን የሚጠቀሙ ግለሰቦች: ሱሱ በሚታይ ሁኔታ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰባቸው ቢሆን እንኳን: ችግሩን አምኖ ከመቀበል ይልቅ: ምንም ችግር እንዳልተከሰተባቸው በመካድ (denial) እና ሱሰኛ እንዳልሆኑና ማቆም ከፈለጉ በየትኛውም ጊዜ ማቆም እንደሚችሉ ሲናገሩ ይስተዋላል:: በዚህ ወቅት የባለሙያው ሚና እነዚህን ጉዳቶች እንዲያስተውሏቸው (impact assessment): እጽ ተጠቃሚ መሆናቸው የጠቀማቸውንና የጎዳቸውን ነገር (pros and cons) እንዲዘረዝሩ በማድረግ ነገሮችን እንዲያሰላስሉ መፍቀድ ይሆናል::
▶️ Contemplation/ውጥን-
▫️በዚህ የለውጥ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች ስለ ችግሩ እውቅና ይኖራቸዋል:: ንግግሮቻቸው በመለወጥና ባለመለወጥ ሃሳቦች መሃል ይዋልላሉ::
▫️ 'እጹን መጠቀሜ ከባለቤቴ ጋር እንዳጋጨኝ አውቃለሁ: ግን ደሞ ጓደኞቼን ሳገኝ መጠቀሜ አይቀርም: የክፋ ቀን ወዳጆቼን ማጣት ደሞ አልፈልግም' አይነት ንግግሮች ይስተዋላሉ::
▫️ብዙዎቹ የዕጽ ተጠቃሚዎች እዚህኛው ደረጃ ሲደርሱ ወደ ባለሙያ እርዳታን ለማግኘት የማቅናት እድላቸው ይጨምራል::
▫️በዚህ ወቅት የባለሙያው ሚና ወደ መለወጥ ሃሳቦች እንዲዘነብሉ ማበረታታት ይሆናል::
▫️ የችግሩን ግዝፈት እንዲረዱ እና ለውጥ ለማምጣት ብቁ እንደሆኑ እንዲገነዘቡ በማድረግ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ማሻገር ይቻላል::
▶️ Preparation/ የዝግጅት ምዕራፍ
▫️በዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የመለወጥ ውጥናቸው ሚዛን መድፋት ይጀምራል::
▶️ Action/ ተግባራዊ የመለወጥ ስራዎች
▫️የለውጥ ስራዎቻቸው መታየት ይጀምራሉ:: የሚጠቀሙትን ሱስ መጠን ሲቀንሱ: ከፍ ሲልም ሲያቆሙት ይስተዋላል::
▫️በዚህ ሂደት ውስጥ ያሉ ሰዎች: የለውጥ ሂደቱን የሚያሳልጡ መሰረታዊ ክህሎቶችን እንዲማሩ ይደረጋል::
▶️ Maintenance/ ለውጥን ማስቀጠል
▫️በዚህ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎች: የቀድሞ ባህርያቸው እንዳያገረሽ ስራን ይፈልጋል::
▶️ Relapse/ ወደ ቀደመ ባህርይ መመለስ
▫️ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደቀደመ ባህርያቸው ሊመለሱ ይችላሉ:: እነዚህ ምክንያቶችን መለየትና መስራት መቋቋምያ መንገዶችን መፈለግ ያሻል::
▪️የሱስ ማቆም ህክምናዎች እነዚህ የለውጥ ሂደቶቾን መሰረት አድርገው ይካሄዳሉ::
▪️በግል ወይንም በቡድን ሊሰጡ ይችላሉ::
▪️የሱስ ማቆም ህክምናን ለማግኘት የተለያዩ የህክምና ተቋም አማራጮች በመዲናችን ይገኛሉ::
▪️በቀጣይ ስለ ህክምና አማራጮቹ እንቃኛለን::
Reference
- Curriculum based motivational group by Ann Fields and Internet
ቸር ይግጠመን!
ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው: የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት
Hakim
BY Mental wellness የአእምሮ ጤና
Share with your friend now:
tgoop.com/DrYonasLakew/2582