tgoop.com/Dreyob/6823
Last Update:
ኃይል (ስልጣን) እና ራስን መግዛት
“የመጨረሻው ሰው ለማግኘት ሊጣጣር የሚገባው ኃይል (ስልጣን) ራስን የመግዛት ኃይል (ስልጣን) ሊሆን ይገባዋል” - Elie Weisel
“ሌሎችን መግዛት ጥንካሬ ነው፣ ራስን መግዛት ግን እውነተኛ ኃይል ነው” ይላል የሰነበተ የሩቅ ምስራቆች አባባል፡፡
ሰው ሰፊ ቤተሰብ፣ ግዙፍ ድርጅት፣ ከዚያም አልፎ አገር እያስተዳደረ ራሱን በቅጡ ላያስተዳድር ይችላል፡፡
ቤተሰብ ለማስተዳደር ምናልባት በቂ ገንዘብን ማቅረብ ሊጠይቅ ይችላል (ሁኔታውን በዚያ ጎኑ ብቻ ለማየት ከወሰንን)፡፡ ድርጅትና ሃገርን ማስተዳደር ምናልባት እውቀትንና ሹመትን ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ራስን ለማስተዳደር ግን ይህ ነው የማይባል ራስን የመግዛት ዲሲፕሊን ይጠይቃል፡፡
ባለን ገንዘብ ሰዎችን ስናስተዳድር በእኛ ላይ የተደገፉትን ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ እናኖራቸዋለን፡፡ በጨዋነትና በዲሲፕሊን ራሳችንን ስናስተዳድር ግን ለራሳችንም ሆነ ለእነሱ ለረጅም ጊዜ እንኖራለን፡፡
ባካበትነው ገንዘብ፣ በቀሰምነው እውቀትም ሆነ በሌሎች ነገሮች አማካኝነት በእጃችን በገባው ኃይልና ስልጣን ተጠቅመን ትክክለኛውን ነገር ማድረግ የምንችለው፣ በእሱ ተጠቅመን በአካባቢያችን የሚገኙትን ሰዎች አንቀጥቅጠን ስለገዛናቸው ሳይሆን ራሳችንን በመግዛት ለእውነት ስንኖር ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ “ኃይል የሚያስፈልግህ ሰዎችን የሚጎዳ ነገር ለማድረግ ስትፈልግ ብቻ ነው፡፡ አለዚያ፣ ማንኛውንም ነገር ለማከናወን ፍቅር በቂ ነው”፣ ይለናል Charles Chaplin፡፡
በቤተሰብ ውስጥ ካላችሁ የበላይነት ተነስታችሁ እስከ ትምህርት፣ ስራና ማሕበራዊ ተቋሞች ድረስ የተሰማራችሁበትን መስክ ተመልከቱት!
በማን ላይ ምን ያህል ኃይልና ስልጣን አላችሁ? ይህንን ኃይልና ስልጣናችሁን ሰዎች ሲያስቡ ምን እንዲሰማቸው እያደረጋችሁ ይመስላችኋል?
ኃይልና ስልጣናችሁን ተጠቅችሁ የምትገዷቸው ይመስላቸዋል ወይስ የምትጠብቋቸው?
ይህንን ስሜት ከምን የተነሳ ያዳበሩት ይመስላችኋል?
በኃይልና በስልጣናችን ተፈሪነት ሳይሆን ፍሬ ማፍራት እንዲሆንልን እንስራ!
https://www.tgoop.com/Dreyob
https://m.youtube.com/user/naeleyob623
https://www.facebook.com/Dr-Eyob-Mamo-1050816404958639/
BY Dr. Eyob Mamo

Share with your friend now:
tgoop.com/Dreyob/6823