Telegram Web
🕊

[  † እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና አባ አርከሌድስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊  † አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ †  🕊

† ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አቡነ አረጋዊ ከዘጠኙ [ ተስዓቱ ] ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር :-

፩. የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ:
፪. ዓላማ [ የእግዚአብሔር መንግስት ] እና
፫. ገዳማዊ ሕይወት ነው::

አቡነ አረጋዊን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት ፭ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ፬፻፸ [470] ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች:: አቡነ አረጋዊና ፰ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አቡነ አረጋዊ እንደገና አቀጣጠሉት::

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አቡነ አረጋዊ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::

የነ አቡነ አረጋዊ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::

- ዸንጠሌዎን በጾማዕት :
- ገሪማ በመደራ :
- ሊቃኖስ በቆናጽል :
- አባ ይምዓታ በገርዓልታ :
- ጽሕማ በጸድያ :
- ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
- አባ አረጋዊ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ዳሞ [እዛው ትግራይ] ሆነ::

በሃገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ እኒህ ጻድቅ ናቸው:: ጻድቁ የተወለዱት በ፭ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ንጉሥ ይስሐቅና ቅድስት እድና ይባላሉ:: የተለወለዱበት አካባቢም ሮም ነው::

ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው:: ወላጆቻቸው " ዘሚካኤል" ሲሏቸው በበርሃ "ገብረ አምላክ" ተብለዋል:: በኢትዮዽያ ደግሞ "አረጋዊ" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ::

በዚያም በገዳመ ዳውናስ [ግብጽ] የታላቁ ቅዱስ ዻኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል:: ከመነኮሱ ከዓመታት በሁዋላም ወደ ሃገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ፯ ያህል የቤተ መንግስት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል::

"የት ልሒድ" ብለው ሲያስቡም ቅዱስ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮዽያን አሳያቸው:: ተመልሰውም ለ፰ ባልንጀሮቻቸው "ሃገርስ ባሳየሁዋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር" ብለው ከ፰ቱ ጋር ወደ ኢትዮዽያ መጡ::

በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ:: ወደ ሃገራችን የመጡ በ፬፻፸ [470]ዎቹ አካባቢ ሲሆን አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል:: በቤተ ቀጢን [አክሱም] ተቀምጠውም መጻሕፍትን እየተረጐሙ: ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል::

ለሥራ በተለያዩ ጊዜም አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ብዙ ደክመዋል:: በመጨረሻ ግን ደብረ ዳሞን [ደብረ ሃሌ ሉያን] አይተው ወደዷት:: የሚወጡበት ቢያጡም ጅራቱ ፷ [60] ክንድ የሚያህል ዘንዶ ተሸክሞ ከላይ አድርሷቸዋል::

እንደ ወጡም "ሃሌ ሉያ ለአብ: ሃሌ ሉያ ለወልድ: ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው ቢያመሰግኑ ከሰማይ ሕብስት ወርዶላቸው ተመግበዋል:: በዚህም ቦታዋ "ደብረ ሃሌ ሉያ" ተብላለች:: ጻድቁ ቦታውን ከገደሙ በሁዋላ ከተለያየ ቦታ መጥተው 6ሺ ያህል ሰዎች በእጃቸው መንኩሰዋል::

ምናኔን በማስፋፋታቸውና ሥርዓቱን በማስተማራቸውም "አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮዽያ - የኢትዮዽያ መነኮሳት አባት" ይባላሉ:: አቡነ አረጋዊ በሕይወታቸው ከተጋድሎ ባሻገር በወንጌል አገልግሎትና መጻሕፍትን በማዘጋጀትም ደክመዋል::

ቅዱስ ያሬድና አፄ ገብረ መስቀልም ወዳጆቻቸው ነበሩ:: በተራራው ግርጌ ያለችውን ኪዳነ ምሕረትን ለሴቶች ሲገድሟት ቀዳሚዋ መነኮስ እናታቸው ንግስት እድና ሁናለች::

ጻድቁ ንጹሕ ሕይወታቸውን ፈጽመው በተወለዱ በ99 ዓመታቸው በገዳሙ በስተ ምሥራቅ አካባቢ ተሰውረው ብሔረ ሕያዋን ገብተዋል:: ጌታም ፲፭ [15] ትውልድን የሚያስምር የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል:: ዛሬ ጻድቁ የተወለዱበት ቀን ነው::


🕊  †  አባ አርከሌድስ   †  🕊

† በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን በግብጽም በሃገራችንም አሉ:: ዋናውና በብዙ መጻሕፍት ዜናቸው የተጻፈላቸው ግን ዛሬ የምናከብራቸው ናቸው:: አባ አርከሌድስ የነበሩት በዘመነ ጻድቃን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ናት::

ወላጆቻቸው ክርስቲያን: በዚያውም ላይ ባለ ጠጐች ነበሩ:: አባታቸው ደግሞ መስፍነ ሃገር ነበር:: ቅዱሱን ወልደው: በሕግ በሥርዓት አሳድገዋል:: ለአካለ መጠን አባ አርከሌድስ ሲደርሱ ግን አባታቸው ሞተ::

መዋዕለ ሐዘናቸው ከተፈጸመ በሁዋላም እናት አባ አርከሌድስን ጠርታ:- "ልጄ! ሒድና የአባትህን ሹመት እጅ አድርግ" አለችው:: ለመንገድ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሰናድታ: አገልጋዮችንና ብዙ ወርቅ (ለሿሚው አካል የሚሰጥ) ጨምራም ልጇን ሸኘች::

ቅዱስ አርከሌድስም ከእናታቸው ተለይተው በአገልጋዮች ተከበው ወደ መርከብ ገቡ:: በባሕር መካከል ሳሉ ግን ታላቅ ማዕበል ተነስቶ መርከቡን በታተነው:: በመርከቡ የነበረው ሰው ሁሉ ሲያልቅ አባ አርከሌድስ ግን በስባሪ ላይ ተንጠልጥለው ተረፉ::
👍4
ዋኝተው ወጥተው ወደ ዳርቻ ሲደርሱም ማዕበል የተፋው አንድ በድን ወድቆ ተመልክተው ፈጸመው አለቀሱ:: ወዲያውም በልባቸው የዚህን ዓለም ኃላፊነት አሰቡ:: ሹመት ፍለጋ መሔዳቸውን ትተው ወደ ገዳም ሔዱ::ወደ ምድረ ሶርያ ደርሰው በታላቁ ደብረ ሮማኖስ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበሉ:: በእጃቸው የነበረውን ፪፻ [200] ዲናር ወርቅም ለገዳሙ አበረከቱ:: ለጥቂት ጊዜ በገዳሙ ካገለገሉ በሁዋላም ጾማዕት [በዓት] ተሰጣቸው::

በዚህ ጊዜም "እንግዲህ ወደ ዓለም አልወጣም:: የሴቶችን መልክም አልመለከትም" ሲሉ ቃል ገቡ:: በተጋድሏቸውም በጾምና በጸሎት: በትጋሃ ሌሊት ለ፲፪ [12] ዓመታት ቀጠሉ:: ጾማቸውም 7 ቀን ነበር:: አምላክ ጸጋውን ስላበዛላቸውም ብዙ ድውያንን ፈወሱ::

ዜናቸውም እስከ ምድረ ሮሜ ተሰማ:: እናታቸው [ሰንደሊቃ] የመርከቡን ዜና ከሰማች በሁዋላ የሞቱ መስሏት አልቅሳ ቤቷን የእንግዳ ቤት አድርጋ: በበጎ ምግባር ትኖር ነበርና አንድ ቀን የልጇን ዜና ሕይወት ሰማች::

ከደስታዋ የተነሳ ፈጥና ወደ ደብረ ሮማኖስ ደርሳ "ልጄን ልይ" አለች:: ግን "ሴትን አላይም" ብለው አባ አርከሌድስ ቃል ገብተዋልና ምን ይሁን! ሰንደሊቃም "አራዊት ይብሉኝ እንጂ ልጄን ሳላይ አልሔድም" አለች:: ወዲያው ግን "አባ አርከሌድስ ፈቅደዋልና ግቢ" የሚል መልእክት መጥቶላት ገባች::

ግን ያገኘችው የጻድቁን ልጇን ሥጋ ነበር:: ምክንያቱም የፈጣሪንም: የእናታቸውንም ልብ ላለማሳዘን እንዲወስዳቸው ለምነውት ዐርፈው ነበር:: እናትም በልጇ ሥጋ ላይ እያለቀሰች እዚያው ዐረፈች:: "አብራችሁ ቅበሩን" የሚል ቃል ከቅዱሱ ሥጋ ስለ ተሰማም አብረው ቀብረዋቸዋል::

† አምላከ ቅዱሳን ለእነርሱ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::

🕊

[   † ጥር ፲፬ [ 14 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. አቡነ አረጋዊ [ ዘሚካኤል ]
፪. ቅዱስ አባ መክሲሞስ
፫. ቅዱስ አባ አርከሌድስ
፬. ቅድስት እምራይስ
፭. ቅድስት ምሕራኤል
፮. "4034"ሰማዕታት [ማሕበራነ ቅዱስ ቂርቆስ]

[   † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. አባ ስምዖን
፪. አባ ዮሐንስ
፫. ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ [ ሙሽራው ]
፬. ቅዱስ ሙሴ
፭. ቅዱስ ፊልዾስ [ ከ፸፪ [72] አርድዕት ]
፮. ቅድስት ነሣሒት

" እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና:: ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና:: ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል  . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ:: በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ:: የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል:: አንደበቱም ፍርድን ይናገራል:: የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው:: በእርምጃውም አይሰናከልም::" † [መዝ.፴፮፥፳፰]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
4
10👍1
ጥር ፲፭ የቅዱስ ቂርቆስ እና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ ዓመታዊ የዕረፍት መታሰቢያ ቀን ናት

ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ቁጥራቸው ከቅዱሳን ሰማዕታት ነው።

ሰማዕት ማለት ''ሰምዐ፥ መሰከረ'' ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ስለ እውነት የመሰከረ ክህደት እዲጠፋ፥ እውነተኛው ሃይማኖት እዲሰፋ የታገለ፥ የተጋደለ፥ የሃይማኖት አርበኛ ሰማዕት ይባላል።

ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣም እንደ እግዚአብሔር ወዳጆች ቅዱሳን ሰማዕታት እግዚአብሔርን አንክድም ለጣዖት አንሰግድም ዘላለማዊ የሆነውን እግዚአብሔርን እንጂ ዘመን የወለደውን ንጉሥ የወደደውን አንከተልም በማለታቸው ከአላውያን ነገሥታት ከከሓድያን እና ከመናፍቃን ጽኑ መከራ ደርሶባቸዋል።

ለእግዚአብሔር ካላቸው ፍጹም ፍቅር የተነሣ እጅ እግራቸውን ለሰንሰለትቅ ሰውነታቸውን ለእሳት፣ ለስለት፣ ለግርፋት፣ ሰጥተዋል። ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚለያቸው የሌለ መሆኑን በግልጽ መስክረዋል። ''መኑ የኅድገነ ፍቅሮ ለክርቶስ''
ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ረሀብ፥ ወይስ መራቆት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?'' በማለት በድፍረት የመሰከረው የቅዱስ ጳውሎስ ምስክርነት እነርሱም ደግመውታል። ሮሜ ፰ ፥ ፴፭

#የሕፃኑ_የቅዱስ_ቂርቆስ እና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ ረድኤት በረከት አይለየን!

     #መልካም_ቀን 🙏

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
      •➢ 👇  ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam  
@Enatachn_mareyam
9
                          †                          

[    🕊    ገ ድ ለ   ቅ ዱ ሳ ን   🕊     ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[ ቅዱስ መቃርዮስ ካስተማረው ትምህርት ]

            [     ክፍል  ሰባ ሁለት     ]

                         🕊  

[ ለመኖር ምን እንደሚያስፈልግ አስተማረ ! ]

🕊

❝ አባ መቃርዮስ ታላቁ እንዲህ አለ ፦ “ ለአንተ መነቀፍ እንደ መከበር ፣ ድህነት እንደ ሀብት ፣ ገንዘብ መክሰርና ማጣት እንደ ትርፍ ፣ የተጣበቡና የተጨናነቁ ሁኔታዎች ልክ እንደ ሰፊ ጎዳናዎችና ነጻ ቦታዎች ፣ የሥጋ ነገሮችም እንደ እንግዳ ነገሮች ናቸውና ትኖራለህ እንጂ አትሞትም፡፡ ከባልንጀሮችህ ጋር ሕሊናህን ተከተል ፣ ዕብሪተኛ ከሆነ ከማንኛውም ሰው ራቅ፡፡ ❞


[ መዳንን ስለ መሻትና መናፈቅ አስተማረ  ]

❝ ታላቁ አባ መቃርዮስ እንዲህ አለ ፦ “ ወንድሞቼ ሆይ ፦ የምትመኟቸውና የምትናፍቋቸው ነገሮች ሁሉ ወደ መዳን የሚመሩ ፣ ነፍሳችሁንም የሚጠብቁና የሚያጸኑ ነገሮች እንዲሆኑ እማልዳችኋለሁ ፣ በዚህም ዛሬ ማድረግ የሚገባንን ነገር ለነገ እንዳንቀጥርና እንዳናሳድር ፣ በእግዚአብሔር መልካም ነገሮችም ሁለት ቀናትን እንግዶች ሆነን እንዳናሳልፍ አደራ እላችኋለሁ፡፡ ❞

🕊

የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡

ይቆየን !


💖                      🕊                      💖
👍5
1
Forwarded from @Bini photographer 📷 (ቢኒ ፲፪)
ዲያቆኔ አንተን ባየው አይኔ
🥰🥰🥰
@Bini photographer 📷

Join👇👇👇 share
         👇👇👇
https://www.tgoop.com/bini_image
https://www.tgoop.com/bini_image
6🔥1🥰1
                         †                        

 [       🕊    ፍኖተ ቅዱሳን    🕊      ]

[ የቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስናና የተጋድሎ ሕይወት ]

▬▬▬▬▬▬   †    ▬▬▬▬▬▬

[  ምሕረት ልናደርግና እርስ በርሳችን በፍቅር ልንቀባበል እንደሚገባ !  ]

🕊

❝ ከአሁን በኋላ እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ... ❞


❝ በግብጽ ውስጥ በበረሃ የሚኖር አንድ ቅዱስ ሰው  ነበር፡፡ ከርሱ ርቆ ደግሞ መነናዊ የሆነ [የማኒ እምነት ተከታይ] እነርሱ ካህን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡

አንድ ወቅት ይህ ሰው ከመሰሎቹ አንዱን ሊጠይቅ ሲሄድ ኦርቶዶክሳዊ ቅዱስ ከሚኖርበት ቦታ ላይ ሲደርስ መሸበት፡፡ ሆኖም መነናዊ መሆኑ እንደሚታወቅ ስላወቀ ወደዚህ ኦርቶዶክሳዊ አባት ብሄድ አይቀበለኝም በማለት በጣም ተጨነቀ፡፡

ሆኖም ምንም አማራጭ ስላልነበረው ሄደና አንኳኳ ፤ አረጋዊውም አባት በሩን ከፈተለት፡፡ እርሱም ማንነቱን አወቀው ፣ በፍቅር ደስ ብሎት ተቀበለው ፣ እንዲጸልይም አለው:: ምግብ ከሰጠው በኋላ አስተኛው:: መነናዊው ሰው ሌሊት ይህን ሁኔታ ሲያሰላስል አደረና "ስለ እኔ ምንም ያልጠረጠረው እንዴት ዓይነት ሰው ቢሆን ነው? በእውነት ይህ ሰው የእግዚአብሔር ሰው ነው" አለ፡፡

ሲነጋም ከእግሩ ላይ ወድቆ "ከአሁን በኋላ እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ" አለው ፣ ከእርሱ ጋርም ኖረ፡፡ ❞

🕊

የአባቶቻችን ጸሎትና በረከት ይደርብን፡፡


†                         †                         †
💖                      🕊                      💖
4👍3
9
💛
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

🕊       [   ምክረ ቅዱሳን   ]        🕊


▷ " ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ ! "


[    💖    አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ    💖     ] 

[                        🕊                        ]
-------------------------------------------------

❝ ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ ፥ አቤቱ ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች ፤ መቼ እደርሳለሁ ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ ?

ዘወትር። አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ። ❞

[  መዝ . ፵፪ ፥ ፩ - ፫  ]


🕊                       💖                     🕊
1
1
                        †                           

🕊  ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ  🕊

                         🕊                         

[  በፍርድ ቦታ የህጻኑ ልብ ቆራጥ ነው !  ]

🕊

† እንኳን ለቅዱሳኑ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †

▬▬▬▬▬▬   ♱    ▬▬▬▬▬▬

❝ ጥቡዕ ልቡ ለሕጻን እንዘ ሀሎ ውሥተ ምኩናን ይቤላ ሕጻን ለእሙ ጥብኢኬ እም ንፈጽም ገድለነ ወስምአነ ንፈጽም ገድለነ ወስምአነ ከመ ንርአይ ገጾ ለአምላክነ ❞

[   ትርጉም    ፦

[  በፍርድ ቦታ የህጻኑ ልብ ቆራጥ ነው። እምዬ [ እናቴ ] ሆይ ምሥክርነታችንን ገድላችንን እንፈጽም ዘንድ ቁረጭ የአምላካችንን ፊቱን እናይ ዘንድ ! ]

[ ዚቅ ዘማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ]

🕊

[  † እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ : ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]



🕊                        💖                      🕊
3
3
🕊

[  † እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ : ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን። †  ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊  †  ቂርቆስ ወኢየሉጣ   †  🕊

† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው:: በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው:: ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል::" [ማቴ.፯፥፲፯]

መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብጹዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል:: ቡርክተ ማሕጸንም እንላታለን:: የተባረከ ማሕጸኗ የተባረከ ልጅን ለ፱ ወር ተሸክሟልና::

በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕጻን እርሷን መስሎ: እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና:: አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብጹዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች::

በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ:: በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር::

ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት:: መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኩዋ የመጮህ እድል አልነበረውም:: ምክንያቱም የሚሰማው አልነበረም::

በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ:: የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር:: ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ: ካልሆነ ደግሞ ሃገርን ጥሎ በዱር: በገደል መሰደድ ነበረበት::

እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም:: ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና::

ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብጽዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን [የዘመነ ሰማዕታት] ፍሬ ናቸው:: በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ:: ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው::

በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት [ኢጣልያዊት] ብጽዕት ኢየሉጣም በመበለትነት [ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ] ትኖር ነበር:: ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና ፫ ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው: ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር::

እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕጻን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች:: ሃብት ንብረቷን: ወገንና ርስቷንም ትታ: ሕጻን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች:: መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም::

እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት:: ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት:: መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው" አለችው:: ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው:: ሞክሼ [ሞክሲ] ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ" አለችው::

"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የ፫ ዓመት ሕጻን ፈልገህ አምጣና ተረዳ" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው:: የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር::

ቅዱሱ ሕጻን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕጻን - ደስ የተሰኘህ ሕጻን እንዴት ነህ" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታየ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ" አለው::

በሕጻኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ" አለው:: ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ: ስሜ ክርስቲያን ነው:: እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው" ሲል መለሰለት::

ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕጻን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ:: ከዚህ በሁዋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር [እጽፍ] ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም::

በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ::

- ፯ ብረት አግለው በዐይናቸው: በጆሯቸው: በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ::
- በ፬ ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው::
- በእሳት አቃጠሏቸው::
- ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ::
- ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው::

እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ:: ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት:: ከብዙ ስቃይና መከራ በሁዋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕጻኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል:: ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል::


🕊  †  ቅዱስ አብድዩ ነቢይ  †  🕊

† "አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው:: ቁጥሩ ከ፲፪ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው:: ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ::

ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፰ መቶ ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል:: ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እሥራኤልን ስታስፈጅ ፶ውን በአንድ ዋሻ : ፶ውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል:: ፱ መቶው ግን ተጨፍጭፈዋል::

ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል:: አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በሁዋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል:: እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር: ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል::

በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይሕ ነቢይ ነው:: ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና:: ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል::

† አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን:: በይቅርታው ኃጢአታችንን ይተውልን:: ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን::

[   † ጥር ፲፭ [ 15 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
፪. ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
፫. ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
፬. ቅድስት ሶፍያ
፭. ቅድስት አድምራ
፮. "11,004" ሰማዕታት [ ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ ]

  † ወርሐዊ በዓላት    ]

፩. ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
፪. ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
፫. ቅድስት ክርስጢና
፬. ቅድስት እንባ መሪና

" በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር: ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ: በልብህም:- 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል:: እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ: ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን: 'ከዚያ አወርድሃለሁ' ይላል እግዚአብሔር::" † [ አብድዩ.፩፥፫ ]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
2025/07/13 10:50:34
Back to Top
HTML Embed Code: