Telegram Web
👏6👍1
#__ወዳጄ

ከፍ ከፍ ትል ዘንድ #ትሑት ሁን፤ ባለጸጋ ትሆን ዘንድ #ድኻ ሁን፤ ትጠግብ ዘንድ #ረኃብን ውደዳት። ጤነኛ ትሆን ዘንድ የመብል ሸክምን አቅልል፤ ትከብር ዘንድ #ተዋረድ፤ ደስ ይልህ ዘንድ #አልቅስ፤ ትኖር ዘንድ #ሙት፤ ትበራ ዘንድ ትጋ። ትድን ዘንድ በማስተዋል #ጸልይ፤ ኃጢአትህን ይቅር ይልህ ዘንድ አብዝተህ #ጹም፤ ታገኝ ዘንድ #ፈልግ፤ ታተርፍ ዘንድ ለመነገድ ተፋጠን። ባለጸጋ ትሆን ዘንድ በብርሃናውያን መንገድ ትመላለስ ዘንድ #መስቀልህን ተሸከም፤ ሥጋህን ጥላት #ነፍስህን አንጻት።

አጫጭር ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
•➢ 👇 ለማግኘት // 👇

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
17👍2👏2
🕊

† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዘካርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ! †

🕊  †  ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ  †  🕊

† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን [አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር] : መጻዕያትን [ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን] የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: [ሐዋ.፲፩፥፳፯] ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር : ወተናጸሩ ገጸ በገጽ::" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: [ቅዳሴ ማርያም]

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ:: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: [ዮሐ.፬፥፴፮]

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል:: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: [ማቴ.፲፫፥፲፮, ፩ጴጥ.፩፥፲] ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" : "አራቱ ዐበይት ነቢያት" : "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት" እና "ካልአን ነቢያት" ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

† "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" ማለት :-

፩. ቅዱስ አዳም አባታችን
፪. ሴት
፫. ሔኖስ
፬. ቃይናን
፭. መላልኤል
፮. ያሬድ
፯. ኄኖክ
፰. ማቱሳላ
፱. ላሜሕ
፲. ኖኅ
፲፩. አብርሃም
፲፪. ይስሐቅ
፲፫. ያዕቆብ
፲፬. ሙሴ እና
፲፭. ሳሙኤል ናቸው::

† " አራቱ ዐበይት ነቢያት "

፩. ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
፪. ቅዱስ ኤርምያስ
፫. ቅዱስ ሕዝቅኤል እና
፬. ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

† " አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት "

፩. ቅዱስ ሆሴዕ
፪. አሞጽ
፫. ሚክያስ
፬. ዮናስ
፭. ናሆም
፮. አብድዩ
፯. ሶፎንያስ
፰. ሐጌ
፱. ኢዩኤል
፲. ዕንባቆም
፲፩. ዘካርያስ እና
፲፪. ሚልክያስ ናቸው::

† " ካልአን ነቢያት " ደግሞ :-

- እነ ኢያሱ
- ሶምሶን
- ዮፍታሔ
- ጌዴዎን
- ዳዊት
- ሰሎሞን
- ኤልያስ እና
- ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::

- የይሁዳ [ ኢየሩሳሌም ] :
- የሰማርያ [ እሥራኤል ] እና
- የባቢሎን [ በምርኮ ጊዜ ] ተብለው ይጠራሉ::

† በዘመን አከፋፈል ደግሞ :-

- ከአዳም እስከ ዮሴፍ [ የዘመነ አበው ነቢያት ] :
- ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል [ የዘመነ መሳፍንት ነቢያት ]
- ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት [ የዘመነ ነገሥት ነቢያት ] :
- ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ [ የዘመነ ካህናት ነቢያት ] ይባላሉ::

† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

† ቅዱስ ዘካርያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ/ል/ክርስቶስ በ፬፻፶ [450] ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ ፲፬ [14] ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

† ነቢዩ ቅዱስ ዘካርያስ :-

- ከክርስቶስ ልደት ፬፻፶ [450] ዓመታት በፊት የነበረ::
- በጻድቅነቱ የተመሰከረለት::
- ፲፬ [14] ምዕራፎች ያሉት ሐረገ - ትንቢት የተናገረ::
- ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በስፋት የተነበየ ነቢይ ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትም አንዱ ነው::

† የአባታችን በረከት ይደርብን::

🕊

[   † የካቲት ፲፭ [ 15 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት   ]

፩. ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ [ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ]
፪. ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ [ከጻድቅነቱ ባሻገር በግብጽ በርሃ የሚኖሩ የብዙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት የጻፈ አባት ነው::]
፫. ቅዱሳን አርብዐ ሐራ ሰማይ [፵ [40] የሰማይ ጭፍሮች] ለ፵ [40] ቀናት ሰብስጥያ በምትባል ሃገር መከራ ተቀብለው በሰማዕትነት ያለፉ ክርስቲያን ጓደኛሞች::

[     † ወርኀዊ በዓላት     ]

፩. ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
፪. ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ [አፈ በረከት]
፫. ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
፬. ቅድስት እንባ መሪና
፭. ቅድስት ክርስጢና

". . . የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:: 'ወደ እኔ ተመለሱ . . . እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ::' " † [ዘካርያስ ፩፥፫]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]


         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
👍1
4👍2
#ኪዳነምህረት_እናቴ 16 🙏🙏

#የብርሃን_እናቱ_ሆይ ካንቺ በነሳው ስጋ እኛነታችንን አከበረ፡ መዐዛሽ ስቦት አንችን በወደደ ጊዜ ድህነታችን ተሰራ #ድንግል_ሆይ እውነተኛው የህይወት እንጀራ : ጣፋጩን የነፍስ መጠጥ አማናዊው የፅድቅ ብርሀን የፈነጠቀብሽ ነሽና ከትውልድ መሀል #ብፅዕናሽን እንናገራለን ጥማችንን የቆረጠ ጥዑም ወይን ረሀባችንን ያጠፋ እውነተኛው መብል ካንቺ ወጥቶልናልና #እንወድሻለን ምስራቃዊት በራችን ሆይ ከሴቶች አንችን የሚመስል የለም፡ ባንቺ ላይ ስለተደረገልን ታላቅ ነገር ዛሬም ለዘላለምም ስምሽን እናገናለን፡፡

#ዝምተኛይቱ_ድንግል_ሆይ አንቺ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ የአይሁድ ሴቶች አይደለሽም በትሕትና ተልመሽ በንፅሕና አጊጠሽ የባህርያችንን መመኪያ ያስገኘሽልን የፅድቅ በራችን ነሽ።

#አንችን_ማመስገን የነፍስ ምግብ የህሊና እርካታ ነው #ስናመሰግንሽ እናርፋለን ስናርፍ #እናመሰግንሻለን። ክብርሽ ከሰማይ ምስጋናሽም ከአርያም ነውና አንችን ለማመስገን ልቦናችን ይብራ አሜን🙏

@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
11🙏5❤‍🔥2🥰1
                          †                          

     [   🕊  መዝሙረ ተዋሕዶ   🕊   ]  

🍒▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬🍒               

[  ኦርቶዶክሳዊ የተቀደሰ ያሬዳዊ ዝማሬ ሰዓት  ]

[ ሳምንታዊ መርሐ-ግብር ]

🕊

በስመ አብ ፡ ወወልድ ፡ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ንጹሕና የተቀደሰ ነው ፥ ለእግዚአብሔር ምስጋናና ልመና የሚቀርብበት ፣ ይቅርታና ምሕረት የሚጠየቅበት ፣ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት የሚዘጋጅ ንጹሕ መስዋዕት ነው ፥ በአበው ጸሎት ይዘጋጃል ፥ ከስጋዊና ከደማዊ ሀሳብ የራቀ ነው ፥ ልቦናን ወደ ንስሐ ይጠራል ፥ ከኃጢአትና ከክፉ ሥራ የመለየት ኃይል አለው ፥ ክፉ መንፈስን ከሰው ልብ ያርቃል ፥ መረጋጋትን ልቦናን ዘልቆ የሚሰማ ውስጣዊ ሰላምን ይሰጣል ፥ በአሚነ ሥላሴ ያጸናል ፥ የክርስቶስን የባህርይ አምላክነትና መሐሪነት ይመሰክራል ፥ የእመቤታችንን ፍቅር በልቦና ያሳድራል ፥ በእናትነቷና በምልጃዋ እንድንታመን ያደርጋል ፥ በቅዱሳን ጸሎትና በቃል ኪዳናቸው ያጸናል ፥ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን እናውቅ ዘንድ መንገድ ይመራናል ፥ ፈሪሐ  እግዚአብሔርንና ፍቅረ እግዚአብሔርን ያጎናጽፈናል፡፡

†                       †                       †

ተወዳጆችሆይ ፦ በተቀደሰ ሰማያዊ ያሬዳዊ ዜማ ነብሳችንን እናስጊጣት፡፡ ከደጋጎቹ አባቶቻችን ጋር ከዓለም ርኩሰት በተለየ የተቀደሰ ዝማሬ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሥግን፡፡ ለስጋዊ ጆሮዎች ከሚመች ከረከሰ የተሃድሶ የኑፋቄ እርሾ ልቦናችንን እንጠብቅ፡፡ ገንዘብን ስለመውደድ ከሆነ ከሥጋዊ ሥራ ፈጽሞ እንለይ፡፡

🍒

🕊 ከጦመ በኋላ ተራበ ! 🕊  ]

[  " ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው ፥ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። "  ]

{ ማቴ.፬፥፩ }  


†                       †                       †
💖                    🕊                    💖
👍2
😢8💔5❤‍🔥2
🕊                   

[ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ]

✞ እንኩዋን ለዐቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ ✞
                   
🕊                       💖                   🕊

[ ዐቢይ ጾም  " የጌታ ጾም " ]

  🍒

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው ፯ [ 7 ] አጽዋማት አሏት:: " ጾም " ማለት "መከልከል" ነው::

የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ መባልዕት መከልከልን ይመለከታል::

ጾም ለክፉ ሥራ ከሚያነሣሱ የምግብ ዓይነቶች መከልከል ወይም ለተወሰነ ጊዜና ሰዓት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መወሰን [ መታቀብ ] ማለት ነው፡፡ ለሰውነት የሚያምረውንና የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ብሎ መተው ነው፡፡

ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ ጸዋሚ ሰው ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን የሚያለማምድበት ስንቅ ነው፡፡ "ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ ፤ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም ፤ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ፤ ከእግዚአብሔር ጸጋን የምታሰጥ ፤ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ ፤ የጽሙዳን ክብራቸው ፤ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው ፤ የንጽሕና መገለጫ ፤ የጸሎት ምክንያት እናት ፤ የዕንባ መገኛ መፍለቂያዋ ፤ አርምሞን የምታስተምር ፤ ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት፡፡" [ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬፥፮]

ጾም ተድላ ሥጋን የምታጠፋ ፥ የሥጋን ጾር የምታደክም ፥ ቁስለ ነፍስን የምታደርቅ ፥ ለጎልማሶች ጸጥታንና ዕርጋታን የምታስተምር ፥ ከግብረ እንስሳዊ የምትከለክል ፥ ሰው መላእክትን መስሎ የሚኖርባትና ኃይል መንፈሳዊን የሚጎናጸፍባት ደገኛ መሣሪያ ናት፡፡ ከኃጢአት ፆር ከፍትወት አንዱንም አንዱን ድል ለመንሳት ለማጥፋት ፥ የዲያብሎስን ረቂቅ ፍላጻ ለመመከት በጾም መድከም የሥራ ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነች የታወቀ ነው፡፡ ጾም ምህረት መለመኛ ፥ የንስሐ መገለጫ ፥ ከመከራ የሚሠወሩባት ፥ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታርቃ ርስት መንግሥተ ሰማያት የምታስገባ "ኆኅተ ጽድቅ - የጽድቅ በር" ሆና የተሰጠች ቀዳማዊት ሕግ ናት፡፡

🕊       💖      🕊

[ ዐቢይ ጾም [ ጾመ እግዚእ ] ]


ከ፯ [7] ቱ አጽዋማት አንዱ የሆነው ይህ ጾም

፩. ዐቢይ [ ታላቁ ] ጾም
፪. የጌታ ጾም
፫. ጾመ ሑዳድ
፬. የድል ጾም
፭. የካሳ ጾም
፮. አርባ ጾም
፯. የፍቅር ጾም . . .
በሚሉ መጠሪያዎችም ይታወቃል::

የጾሙ መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ =

፩. ጾመ ሕርቃል
፪. ጾመ በረከት ዘሐዋርያት
፫. ሰሙነ ዘወረደም ይባላል::

የጾሙ የመጀመሪያው ሳምንት [ዘወረደ] የሚጾመው እስከ ፲፪ [ 12 ] ሰዓት ሲሆን ከቅድስት [ ከ፪ [ 2 ] ኛው ሳምንት እስከ ተጽኢኖ [ የኒቆዲሞስ ዓርብ ] ድረስ ደግሞ እስከ ፲፩ [ 11 ] ሰዓት ይጾማል::

በሰሙነ ሕማማት ግን የምንጾመው "እስከ ይሠርቅ ኮከብ" [ እስከ ምሽት ፩ [ 1 ] ሰዓት ] ድረስ ይሆናል::

ነገር ግን ሁሉም እንደ መጠኑ ነውና ከመምሕረ ንስሃ ጋር ሊጨዋወቱት ይገባል:: በዓቢይ ጾም ለቻለ ቂጣ በጨው እየበላ : ውሃ እየተጐነጨ ሊጾም ይገባል:: በእነዚህ ፶፭ [ 55 ] ቀናትም ከዕለተ ሆሳዕና በቀር ከበሮ አይጐሰምም:: ጸናጽል አይጸነጸልም:: ተድላ ደስታም አይደረግም::

አብዝቶ መብላት : ሳቅ ማብዛትና ጌጥን ማብዛትም እንዲሁ አይገባም:: ለቻለ ደግሞ በሌሊት ሰዓታቱን ፡ በነግህ ኪዳንና ስብሐተ ነግሁን : በመዓልት ቅዳሴውን : በሰርክ [ ምሽት ] ደግሞ ምሕላውን ሊሳተፍ ይገባል::

በእነዚህ ፶፭ [ 55 ] ቀናት ፈቃደ ሥጋ ሊደክም : ፈቃደ ነፍስ ልትሰለጥን ግድ ነውና:: ከሌላው ጊዜ በተሻለ ወቅቱ ምጽዋትና ጸሎት የሚደረግበት ነው:: በዚያውም ላይ ነገሮችን እያመቻቹ በእነዚህ ዕለታት ቅዱስ ቃሉን መስማት [ማንበብ] ይገባል:: በትዳር ውስጥ ላሉም መኝታን መለየት ግድ ነው::


ጾሙን የሰላም : የፍቅር : የምሕረት : የፀጋ : የበረከት ያድርግልን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን፡፡

" አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ:: ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ:: አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ: ቁጣው የዘገየ: ምሕረቱም የበዛ: ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ:: " [ትን. ኢዩኤል.፪፥፲፪ (2:12) ]


ወስብሐት ለእግዚአብሔር : ወለወላዲቱ ድንግል : ወለመስቀሉ ክቡር !

         [       ይቆየን ! ]

†                       †                         †
💖                    🕊                     💖
❤‍🔥8🥰3
ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተመረጥሽ #እመቤታችን_ሆይ! አንቺን አናመልክም ነገር ግን ከሁሉ በበለጠ እጅግ በላቀ ምስጋና ክብርሽን እንገልጣለን።

#የተመረጥሽ_ድንግል_እመቤቴ_ማርያም ሆይ ሁልግዜ #በዓይን_ልቦናዬ አይሻለሁ . . . በሃሳቤም በየስፍራው ሁሉ አገኝሻለሁ ልጅሽም የዓለም መድሀኒት ነው ። በተኛሁም ጊዜ እኔን ለመጠበቅ የነቃሽ ነሽ ፣ከመኝታዬም ስነቃ እኔን ለማንሳት የተዘጋጀሽ ነሽ ስቀመጥም እኔን #ለመምከር ትደረሻለሽ ፣ በቆምሁም ጊዜ በቀኜ ትቆሚያለሽ ፣ በተናገርሁም ጊዜ አንደቤቴን ለማጣፈጥ ታከናውኛለሽ ፣ በዝምታዬም ጊዜ ለመጠበቄ ማሞገሻ ነሽ ፣ ሀሴትም ባደረግሁ ጊዜ ተድላ ደስታዬ ነሽ
በእውነት ምን ብዬ እንዴት ልገልጥሽ ይቻለኛል።
ዝክርሽን ዘክሬ በበረከትሽ እንድጎበኝ ፈጣሪ ይርዳኝ።
የእናታችን የኪዳነምህረት እረድኤት በረከት ፍቅር አይለየን አሜን 🙏🙏🙏

#እንኳን_ለእመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም ዓመታዊ የኪዳን በዓል በሰላም አደረሳችሁ 🙏🙏🙏


@Enatachn_mareyam
@Enatachn_mareyam
9🙏3❤‍🔥1
🕊

[ † እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የኪዳን በዓል በሰላም አደረሳችሁ †  ]

† ፯ [ 7 ] ቱ ኪዳናት †

'ተካየደ' ማለት 'ተስማማ: ተማማለ' እንደ ማለት ሲሆን 'ኪዳን' በቁሙ 'ውል: ስምምነት' እንደ ማለት ነው:: ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር: ሰዎችም ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል:: ልዩነቱ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው::

እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጉዋል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ ፯ [7] እንደ ሆኑ ታስተምራለች:: ስለዚህም ዛሬ ፈጣሪ ቢረዳን እነዚሁን ፯ [7] ኪዳናት በጥቂቱ እንመለከታለን::

"ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ"
"ከመረጥኩዋቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ" [መዝ.፹፰፥፫] [88:3]

፩. " ኪዳነ አዳም "

አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት: የፍጡራን አስተዳዳሪ: ነቢይ: ካህንና ንጉሥ ነው:: እግዚአብሔር ከአዳም ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው:: ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ:: [ዘፍ.፫፥፩] [3:1]

አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን ተስፋ: "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ኪዳንን ተቀበሉ:: [ቀሌምንጦስ: ገላ.፬፥፬]

፪. " ኪዳነ ኖኅ "

ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት ፲ [10] ትውልድ ዓለም በዓመፃ ተሞላች:: ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች:: ከመርከቡ ከወጣ በሁዋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ተጋቡ:: "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ" እንዲል:: [ዘፍ.፱፥፲፪] [9:12]

፫. " ኪዳነ መልከ ጼዴቅ "

መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ: የክርስቶስም ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው:: በ፲፭ [15] ዓመቱ መንኖ: አጽመ አዳምን ይዞ: በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት ነበር::

እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ: በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል:: በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም:: ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል:: [ዘፍ.፲፬፥፲፯ ፣ ዕብ.፯፥፩]

፬. " ኪዳነ አብርሃም "

ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት: ሥርወ ሃይማኖት: የጽድቅም አበጋዝ ነው:: ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና እግዚአብሔር "በዘርሕ አሕዛብ ይባረካሉ" አለው:: [ዘፍ.፲፪፥፩] የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን ሰጠው:: [ዘፍ.፲፯፥፩-፲፬]

፭. " ኪዳነ ሙሴ "

ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ: የእሥራኤል እረኛ: የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት [የዋህ] ሰው ነው:: በፈጣሪው ትዕዛዝ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለ፵ [40] ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል:: [ዘጸ.፳፥፩ 20:1, ፴፩፥፲፰ (31:18)]

፮. " ኪዳነ ዳዊት "

ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት: ጻድቅ: የዋህና ቡሩክ የሆነ አባት ነው:: እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ" [መዝ.፻፴፩፥፲፩] [131:11] ሲል ምሎለታል:: አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ "አልዋሰሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን:: [መዝ.፹፰፥፴፭]

፯. " ኪዳነ ምሕረት "

በብሉይ ኪዳን የነበሩ ፮ [6] ቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲዖል ማዳን ግን አልቻሉም:: ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ ነበር:: ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማሕጸን አደረ::

በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ: አድጎ: ተጠምቆ: አስተምሮ: ሙቶ: ተነስቶና ዐርጐ ሥጋ ማርያምን በዘባነ ኪሩብ አስቀመጠው:: ኪዳነ ምሕረት [የምሕረት ኪዳን] የምንለው አንዱ ታዲያ ይሔው ነው::

የጌታችን መጸነሱ: መወለዱ: መሰደዱ: መጠመቁ: ማስተማሩ: ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ: መሰቀሉ: መሞቱና መነሳቱ: ማረጉና መንፈስ ቅዱስን መላኩ በአንድ ላይ ኪዳነ ምሕረት ይባላል:: ታዲያ ይህ ሁሉ የተደረገው በሥጋ ማርያም ነውና የኪዳኑ ባለቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት::

የእርሷ ኪዳን ፮ [6] ቱን አበው ኪዳናት ፍጹም በማድረጉ የኪዳናት ማሕተም ይባላል:: የድንግል ማርያም ኪዳኗ ከሲዖልና ከገሃነም ሊታደገን አቅሙ አለውና:: መድኃኒታችን ክርስቶስ ለድንግል እናቱ ቃል ኪዳኑን ያጸናላት ደግሞ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ ጐልጐታ ላይ ነው::

እመ ብርሃን በዚያ ቁማ ስለ ኃጥአን ስታለቅስ "እናቴ ሆይ! በስምሽ ያመነውን: በቃል ኪዳንሽ የተማጸነውን እምርልሻለሁ" ብሎ ደስ አሰኝቷታልና:: ይሔው በእመ ብርሃን ምልጃና ቃል ኪዳን ምዕመናን ከመቅሰፍትና ከገሃነመ እሳት ማምለጥ ከጀመሩ ፪ [2] ሺ ዓመታት ሆኑ:: ዛሬም እኛ ኃጥአን ልጆቿ ከእሳት እንደምታድነን አምነን በጥላዋ ሥር እንኖራለን::

" ኢትዝክሪ ብነ አበሳነ: ኃጢአተነ: ወጌጋየነ:
ማርያም እሙ ለእግዚእነ:
በኪዳንኪ: ወበስደትኪ ድንግል ተማሕጸነ::"

"ድንግል ሆይ! ኃጢአታችን: አበሳችንና በደላችንን አታስቢብን ዘንድ በስደትሽና በኪዳንሽ ተማጽነናል::"

የአርያም ንግሥት: የሰማያውያንና ምድራውያን ኁሉ እመቤት: የአምላክ እናት: ቅድስት: ስብሕት: ክብርት: ልዕልት: ቡርክት: ፍስሕትና ጥዕምት የሆነች ድንግል ማርያም የድኅነታችን መሠረት: ላመኑባት አንገት የማታስደፋ እውነተኛ አማላጅ ናት::

በዚህች ዕለት የካቲት ፲፮ [16] ስለ ወገኖቿ የሰው ልጆች ፍቅር በእንባ ያቀረበችውን ልመና የባሕርይ አምላክ የሆነ ልጁዋ ተቀብሎ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላታል:: በስምሽ ያመነ በቃል ኪዳንሽ የተማመነ እሳት አያይም ብሏታል::

ቸሩ ልጇ ከበረከተ ኪዳኗ አይለየን:: በዓሉንም የሰላም: የፍቅርና የበረከት ያድርግልን::

🕊

[  † የካቲት ፲፮ [ 16 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ኪዳነ ምሕረት [የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም]
፪. ቅድስት ኤልሳቤጥ [የመጥምቁ ዮሐንስ እናት / የእመቤታችን አክስት / የሶፍያ ልጅ]
፫. ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ [የቅ/ላሊበላ ወንድም]

[   † ወርኀዊ በዓላት   ]

፩. ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
፪. አባ አቡናፍር ገዳማዊ
፫. አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
፬. አባ ዳንኤል ጻድቅ

" . . . ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ:: በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት:: በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች:- አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ: የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው:: የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጀሮየ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና:: ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈፀማልና ያመነች ብፅዕት ናት::" [ሉቃ.፩፥፴፱]

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
4👍4
2025/07/12 13:56:57
Back to Top
HTML Embed Code: