tgoop.com/EthPHI/6758
Last Update:
የኢትዮጵያን የትምቧሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎችን ለማጠናከር የተደረገው ጥናት ውጤት ይፋ ሆነ
-----------------------
ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መንስኤ የሆነውን ትምባሆን የመጠቀም ልምድን ወይም ሱስን መከላከል በኢኮኖሚና በማህበራዊ ህይወት ላይ የሚያስከትለውን ጫና በማቃለል ረገድ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ሲሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ። የፌዴራል የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ዛሬ ሲካሄድ በቆየው የኢትዮጵያን የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎችን ለማጠናከር በቀረበ ምክረ-ሃሳብ ላይ ነው ይህን ያስገነዘቡት።
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የምክክር ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዳሉት፣ የትምባሆ ሱስ ተላላፊ ላልሆኑት እንደ ስኳር በሽታ፣ የልብ ህመምና የመተንፈሻ አካላት ችግሮች መንስኤ ነው ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ትምባሆ ለኢኮኖሚና የማህበረሰብ ጤና ቀውስ ዋና መንስኤ እንደሆነ አስታውሰዋል። “ስለዚህም፣ ይህን የሃገሪቱን አምራች ዜጎች ተጠቂ እያደረገ ያለ ችግርን ለማስወገድ የጤና ሚ/ር፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣንና ሌሎች አጋር አካላት በተከታታይ በማጥናትና በመከላከሉ ረገድ እያደረጉት ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑ ሁላችንንም ያበረታታናል፣” ብለዋል።
ሚ/ር ዴኤታው እንዳሉት በተደረገው ጥናትና ተከትሎም በተወሰደው እርምጃ፣ ከ21 ዓመት በታች ያሉ ወጣት ታዳጊዎች ትምባሆ እንዳያገኙ፣ ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ሲጋራ እንዳይጨስ፣ እና በሌሎችም እርምጃዎች አጥጋቢ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። “ህ/ሰቡን ስለ ትምባሆ አደገኛነት ትምህርት በመስጠት፣ የአመጋገብ ባህላችንን እንዲሻሻል በማድረግ፣ የአካል እንቅስቃሴዎች እንዲዘወተሩና የአካባቢያችንንም ፅዳት በመጠበቅ ረገድ ያልተቋረጠ ትምህርት በመስጠትም ብዙ ስራ ተሰርቷል፣” ብለዋል፣ ሚ/ር ዴኤታው።
ዶ/ር ደረጀ በመጨረሻም የኢትዮጵያን የትምቧሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎችን ለማጠናከር የተደረገውን ጥናት ላከናወኑ አካላት፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ለዓለም የጤና ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ “የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ዳሰሳ (Global Adult Tobacco Survey-GATS) ጥናት በአስተማማኝ ምርምር ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ጤና ማሻሻያ ተግባራትን ለመደገፍ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሌላ ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የከፋ የጤና ጉዳት እንዲሁም ለሞት ከሚዳርጉ ግንባር ቀደም መንስኤዎች አንዱ የሆነው ትምባሆን የመጠቀም ልምድ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት፤ እንዲሁም በዚህ ሳቢያ በሚመጡ ተዛማጅ የጤና እክሎች ወደ 7 ሚሊዮን ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ ነው ብለዋል። ጨምረውም 1.3 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከአጫሾች በሚወጣ የትምባሆ ጭስ በመጋለጥ ሳቢያ በሚመጡ በሽታዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ አስገንዝበዋል።
ትምባሆን የመጠቀም ልምድ በሃገራችን እያስከተለ ያለውን ችግርም እንደሚከተለው አሳይተዋል። “እ.ኤ.አ. በ 2016 በኢትዮጵያ በተከናወነው የመጀመሪያው ዙር የGATS ጥናት መሰረት 5% (3.4 ሚሊዮን) አዋቂ ኢትዮጵያውያን የትምባሆ ተጠቃሚዎች እንደነበሩ ያሳያል። በሌላ በኩል የ2016 (እ.ኤ.አ.) ሪፖርት እንዳመለከተው ትምባሆ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ በሚመጡ የጤና ችግሮች ሳቢያ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ17,000 በላይ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን ያመለክታል።”
ዶ/ር መሳይ በጥናቱ የተገኘውን ውጤትም በሚከተለው ሁኔታ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የችግሩን ጉልህነት እና አጣዳፊነት በመገንዘብ የትምባሆ አጠቃቀምን ለመከላከል ጠንካራ የፖሊሲ እርምጃዎችን ወስዷል። በዚሁ መሰረት የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ (WHO FCTC) በ2004 ዓ.ም በማስፅደቅ ወደስራ ተገብቷል። በተጨማሪም በዚህ ማዕቀፍ ላይ በመመስረት በ2019 ዓ.ም ጠንካራ የትምባሆ ቁጥጥር ህጎችን ያካተተ አዋጅ በማስፅደቅ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ አዋጁም የሚከተሉትን ጠንካራ ህጎች አካቷል፤ (1) ለህዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ቦታዎች 100% ከትምባሆ ጭስ-ነጻ ፖሊሲ፣ (2) ነጠላ-ሲጋራ ሽያጭ ክልከላ፣ (3) ጣዕም ያላቸው የትምባሆ ምርቶች እና የኤሌክትሮኒክስ ሲጋራዎች እገዳ፣ (4) የትምባሆ ማሸጊያ ካርቶኖች ላይ 70% የሚሸፍኑ ሥዕላዊ የጤና ማስጠንቀቂያዎችን አስገዳጅ ማድረግ ይገኙበታል።
እንደ ዶ/ር መሳይ አባባል የሁለተኛው ዙር የGATS ጥናት የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ከተከናወነ ከስምንት አመታት በኋላ በመሆኑ፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተደረጉ ለውጦችን ለመገምገም እና ተጨማሪ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለመለየት ታሳቢ ተደርጎ ነው። “ይህ ጥናት በትምባሆ አጠቃቀም ለውጦች፣ ለህዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች ላይ ለሲጋራ ጭስ የመጋለጥ ደረጃን፣ ትምባሆ ተጠቃሚዎች ማጨስ ለማቆም የሚያደርጉት ጥረት፣ በተጨማሪም ማህበረሰቡ ትምባሆ በመጠቀም እንዲሁም ከአጫሾች በሚወጣ የትምባሆ ጭስ መጋለጥ ስለሚያመጣው የጤና ጉዳት ያለውን የግንዛቤ ደረጃ ለመዳሰስ ያስችላል” ብለዋል፣ ዋና ዳይሬክተሩ።
በመጨረሻም በጥናቱ ውጤት መሰረት ኢትዮጵያ ትምባሆን ከመቆጣጠር አንጻር ከፍተኛ እመርታ ብታሳይም፣ ብዙ መከናወን ያለባቸው ስራዎች እንዳሉ አመላካች መሆኑን አስምረውበታል።
በመሆኑም የጥናቱ ውጤት ላይ ተመስርተን ያሉብንን ክፍተቶች በመለየት፤ ለፕሮግራም እና ለፖሊሲ ግብአት በመጠቀም የዜጎቻችንን ጤና መጠበቅ፣ መጪው ትውልድ በትምባሆ ሱስ ውስጥ እንዳይወድቅ ማድረግ እንዲሁም ኢትዮጵያን በትምባሆ ቁጥጥር ውስጥ ግንባር ቀደም ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ ሄራን ገርባ፣ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን በዋናነት፣ እንዲሁም በሌሎች ድርጅቶች አጋርነት የተሰራው የምርምር ስራ ውጤታማነቱ ሁሉንም ሊያስደስት ይገባል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ ስለጥናቱ ሲገልጹም፣ የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ዳሰሳ (Global Adult Tobacco Survey-GATS) በማስረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ፖሊሲ ማውጣትን የሚደግፍና የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነትን በመተግበር ላይ ያለውን ሂደት የሚለካ አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ቤተሰብ ላይ ያተኮረ ጥናት ነው ብለዋል። “በGATS 2024፣ ኢትዮጵያ የትምባሆ ቁጥጥርን ለማጠናከር ባደረገችው ጥረት አበረታች ውጤቶችና ክፍተቶችን ለማወቅ ተችሏል ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት 4.6 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን (በጉልምስና ደረጃ ላይ ያሉ ወይም በተለምዶ አዋቂዎች)፣ ትምባሆ የሚጠቀሙ ሲሆን፣ በጾታ ረገድ ሲታዩ 8.8 በመቶዎቹ ወንዶች፣ 0.5 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች ናቸው፣ እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ።
BY Ethiopian Public Health Institute | የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
Share with your friend now:
tgoop.com/EthPHI/6758