tgoop.com/EthPHI/6773
Last Update:
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ ጉብኝት አካሄዱ
በጉብኝቱም የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ዶክተር ታደለ ቡራቃ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ፣ ዶ/ር መልካሙ አብቴ፣ ዶ/ር ሳሮ አብደላ እና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያን የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር፣ የበሽታ ክትትልና የወረርሽኝ ምላሽ ሥርዓቶችን ለማዘመን እያከናወነ ያለው ስራ የሚበረታታ እንደሆነ ጠቁመው ወባን ጨምሮ ወቅትን ጠብቀው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰቱ ወረርሽኖችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰራ ያለው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናከሮ መቀጠል እንደሚገባ እንዲሁም በሕብረተሰብ ጤና ምርመር እና ላቦራቶሪ አቅም ግንባታ በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም አበረታች መሆናቸዉን ገለጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴርም ሆነ ከሌሎች ተቋማት ጋር እደረገ ያለውን ቅንጅታዊ ስራ በማጠናከር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በኢንስቲትዩቱ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ምሁራንና ባለሙያዎችም ተገቢው ጥቅማ ጥቅም እና ማበረታቻ እንዲያገኙ የተጀመረው ጥረት ለውጤት እንዲበቃ ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግ የተከበሩ ዶ/ር ታደለ ተናግረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ለተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶች እና ወረርሽኞች ምላሽ በመስጠትና የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተፅእኖዎችን በመቀነስ ረገድ ዉጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጠንካራ የሕብረተሰብ ጤና እና የድንገተኛ አደጋ ቁጥጥር ሥርዓት ለመገንባት እና ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የተለያዩ ጤና ሥጋቶችን እና የወባን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው ካሉ ጤና መዋቅሮች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የህብረተሰብ ጤና ምላሽ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግጁነት ቅኝትና ምላሽ፣ በሪፌራልና ማጣቀሻ ላብራቶሪ አገልግሎቶች አቅም ግንባታ ከፌዴራል እስከ ክልሎች እያጎለበተ ያለዉ አቅም፣ እያከናወናቸው ያሉ ችግር ፈቺ የህብረተሰብ ጤና ምርምር እና የጤና መረጃ ቅመራና ትንተና ስራዎች በጉብኝቱ በሰፊው ታይተዋል። ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ የማይከናወኑ ተላላፊ በሽታዎችን ለመለየትና እና በስርዓተ ምግብ ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች የሚረዱ የላቁ ላብራቶሪ ምርመራዎች በኢንስቲትዩቱ መጀመራቸው የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና ችግሮችን በመለየት ተገቢውን ምላሽ መስጠት ማስቻሉን፣ እንዲሁም ኢንስቲትዩቱ የወባ በሽታን ለመቆጣጠር ከጤና ሚኒስቴር ክክልል ጤና ቢሮ እና ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ የምላሽ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን በመስክ ምልከታው ለመረዳት ተችሏል፡፡
በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው የተገኙ ጥንካሬዎች እና ስኬቶች አበረታች መሆናቸውን እና አጠናክሮ በመቀጠል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የበለጠ ማረጋገጥ እንደሚገባም የስራ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
www.ephi.gov.et/news
BY Ethiopian Public Health Institute | የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
Share with your friend now:
tgoop.com/EthPHI/6773