tgoop.com/Ethio_Betecrstian/5040
Last Update:
፫
የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን ስለ ጌታችን ጥምቀት
እነሆ በዚች ዕለት በውኃ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት እጠመቃለሁ፡፡ ውኃው የኃጢአትን እድፍ የማጠራበት ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስም መሬታውያኑን ሰማያውያን አደርግበታለሁ፡፡ በእሳቱም የኃጢአት እሾህን አቃጥልበታለሁ።
ዮሐንስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ በታላቅ ፍርሀትና መንቀጥቀጥ በብዙ ትሕትናም በጌታ ኢየሱስ ራስ ላይ እጁን ዘርግቶ አጠመቀው፡፡ ሰነፎች አይሁድ ይህን ባዩ ጊዜ ዮሐንስ ከክርስቶስ ይልቅ እጅግ ይከብራል፡፡ ክርስቶስም ከእርሱ ያንሳል፡፡ እንዲህስ ባይሆን ኑሮ ከእርሱ ባልተጠመቀም ነበር አሉ፡፡
እግዚአብሔር አብም የአይሁድን ሐሳብ ያውቃልና ይህችን ሐሳብ ከልቡናቸው ያርቅ ዘንድና እርሱ በመለኮቱ ክብር ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ የሚወደው ልጁ እንደ ሆነ ያስረዳቸው ዘንድ ወደደ፡፡
ስለዚህ ሰማይን ከፍቶ መንፈስ ቅዱስን በርግብ አምሳል ሰደደ፡፡ በራሱ ላይም ተቀመጠ፡፡ በታላቅ ቃልም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ብሎ ተናገረ። ዳግመኛም በሥጋ የተወለደው እርሱ በመለኮቱ ክብር ከእኔ ጋር አንድ ነው፡፡ ከቀደመ ግብሩ ሳይለወጥ ሰው ሆኗልና፡፡ እኔ የወለድሁት ማርያም ከወለደችው የተለየ አይደለም፡፡ በጎል የተኛው ሰብአ ሰገል ከሰገዱለት ልዩ አይደለም፡፡ እርሱ በኔ ህልው ነው፡፡ እኔም በእርሱ ህልው ነኝ፡፡
በሥጋውም ተገልጦ ይታያል፤ በመለኮቱ ተኣምራትን ያደርጋል፡፡ ከማርያም በሥጋ ለተወለደው ልደቱ አባትን አትፈልጉ፡፡ ከዓለም ሁሉ በፊት ከኔ ለተወለደው ልደቱም እናትን አትመርምሩ፡፡ መለኮቱንም ከትስብእቱ አትለዩ፡፡
በእርሱ መጨመርና መለየት የለበትምና፡፡ ክርስቶስ ብቻውን አምላክ ብቻውንም ሰው አይምሰላችሁ፡፡ ሰው የሆነ አምላክ ነው እንጂ፡፡ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ወልድ ዋሕድ በተጠመቀ ጊዜ እግዚአብሔር አብ እንዲህ በማለት ተናገረ።
ዳግመኛም የወልድ ፊቱ በደብረ ታቦር በተለወጠ፣ መልኩም እንደ ፀሐይ በደቀ መዛሙርቱ ፊት ባበራ ጊዜ እግዚአብሔር አብ እንዲህ አለው፡፡ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡፡ እርሱን ስሙት››፡፡
ይቀጥላል.....
(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 55-67)
#ይቀላቀሉን!
@Ethio_Betecrstian
BY 🇨🇬 ደጉ ሳምራዊ (ኢትዮጵና ቅድስት ቤተክርስቲያን )
Share with your friend now:
tgoop.com/Ethio_Betecrstian/5040