tgoop.com/Geb19/1582
Last Update:
🔊ምስጢረ ሥላሴ በብሉይ ኪዳን📖
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
🙏እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር፡ እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በመልካችን እንደምሳሌአችን እንፍጠር ዘፍ 1፥26 እዚህ ላይ እግዚአብሔርም አለ ሲል አንድነቱ፣ እንፍጠር ሲል ከአንድ በላይ መሆኑን ግሱ /ቃሉ/ ያመለክታል፡፡በዚህ ንባብ እግዚአብሔር የሚለው ሥመ አምላክ ከአንድ በላይ የሆኑ አካላትን የሚመለከት መሆኑን ከተረዳን ስለ ሥላሴ ኃልወት በሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ከተጻፉት ምንባባት ጋር በማገናዘብ ይህ ጥቅስ ፍጹም አንድነቱንና ልዩ ሦስትነቱን እንደሚመሰክር በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ አንቀጽ እንፍጠር በመልካችን እንደምሳሌያችን የሚለው ንግግር የሦስት ተነጋጋሪዎች ነው እንጂ ያንድ ተናጋሪ ቃል አይደለም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር፤ ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደምሳሌያችን፤ ሲል ሦስትነቱን ማስተማሩ ነው፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
💁♂ሙሴም ይህን የእግዚአብሔርን ነገር ሲጽፍልን ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደ ምሳሌያችን ያለውን የብዙውን አነጋገር ለአንድ ሰጥቶ፤ እግዚአብሔር አለ፤ ብሎ መጻፉ በአካል ሦስት ሲሆን በባሕርይ በህልውና አንድ ስለሆነ በአንድ ቃል መናገሩን ከእግዚአብሔር ተረድቶ ለእኛ ሲያስረዳን ነው፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
🗣እግዚአብሔርም ለሰው ልጅ ቃል ኪዳን ሲሰጥ፡እግዚአብሔር አምላክ አለ፡- እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ዘፍ 3፥22 በማለት ባለቤቱን አንቀጽን አንድ፣ አሳቡን ዝርዝሩን የብዙ አድርጐ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር አለ ሲል አንድነቱን፣ «ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ» ሲል ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ በማለቱ ሦስትነቱን ያስረዳል፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
💁♂ምንአልባትም እግዚአብሔር አለ፤ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ የሚለው ቃል ሦስት ተነጋጋሪዎች በአንድ ቦታ ቢኖሩ አንዱ ሁለቱን ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ብሎ ሲነገር ከአንድ የበዙ ተናጋሪዎች ቃል መሆኑን ነው የሦስትነት ተነጋጋሪዎች መሆኑን ስለሚያስረዳ እግዚአብሔር ሦስት አካል መሆኑ በዚህ አነጋገር ግልጽ ነው፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
📖በባቢሎን ግንብ ወቅት፡ እግዚአብሔርም አለ፡- «ኑ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው፡፡» ዘፍ 11፥6-8፡፡ «እግዚአብሔር አለ» ብሎ አንድነቱን፣ «ኑ እንውረድ» ብሎ ደግሞ ከአንድ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡በዚህ አንቀጽ እግዚአብሔር ኑ እንውረድ ብሎ በመናገሩ ከሁለትነት የተለየ ሦስትነቱን ያስረዳል፡፡ መረጃውም ሦስት ተነጋጋሪዎች በአንድ ቦታ ሁነው ሲነጋገሩ ሦስተኛው ሁለቱን ኑ እንውረድ ሊላቸው ይችላል፤ ምክንያቱም ሁለት ሆነው ግን አንዱ ሁለተኛውን ና እንውረድ ቢለው እንጂ ኑ እንውረድ ሊለው ስለማይችል ነው፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
👆ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የእግዚአብሔር ቃላት ተገልጸው ሲተረጐሙ፤ አካላዊ ልባቸው አብ አካላዊ ቃሉ ወልድንና አካላዊ ሕይወቱ (እስትንፋሱ) መንፈስ ቅዱስን፤ ሰውን እንፍጠር በመልካችን እንደ ምሳሌያችን፤ እነሆ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ እንዲሁም ኑ እንውረድ፤ ብሎ እንዳነጋገራቸው ይታወቃል፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
💁♂ለአብርሃም በተገለጠለት ጊዜ የአንድነቱና የሦስትነቱ ማስረጃ ሁነው የታመኑ እነዚህ ሦስቱ ቃላት ከአንድ የበዙ የሁለት ተነጋጋሪዎች፤ ከሁለትም የበዙ ተነጋጋሪዎች ቃላት መሆናቸው ይታወቃል እንጂ ከሦስት ያልበለጡ የሦስት ብቻ ተነጋጋሪዎች ቃላት እንደ ሆኑ ቃላቶቹ በማያሻማ ሁኔታ ስለማያስረዱ፤ እግዚአብሔር በእነዚህ አነጋገሮች ከሦስት ያልበዛ ሦስት አካላት ብቻ መሆኑ አይታወቅም የሚል አሳብም ቢነሳ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህም በሌላ አንቀጽ ይመልሳል፡፡ «በቀትርም ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት አብርሃም ሦስት ሰዎችን በፊቱ ቆመው አየ» ዘፍ 18፥1-15 በማለት እግዚአብሔር አንድ መሆኑንና ሦስት አካል ያለው መሆኑን ወስኖ ያስረዳናል፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
🗣የነቢያት ምስክርነት፡ እግዚአብሔር ለሙሴ በተገለጠለት ጊዜ «እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር ነኝ» ዘፀ 3፥6 ሲል «አምላክ፣ አምላክ፣ አምላክ» ብሎ ሦስትነቱን፣ «እኔ እግዚአብሔር ነኝ» ብሎ ደግሞ አንድነቱን ገልጾ ተናግሯል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም «የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች፣ በእግዚአብሔርም ቃል ሰማዮች ጸኑ፣ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ» በማለት የሥላሴን ምስጢር ተናግሯል (መዝ 32፥6)፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
📖ነቢዩ ኢሳይያስም «ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በልዑል ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አየሁት… ሱራፌልም ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ ይጨሁ ነበር፡፡» ኢሳ 6፥1-8 በማለት ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ብሎ ሦስትነቱን፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአበሔር ብሎ ደግሞ አንድነቱን አይቶ መስክሯል፡፡ እንዲሁም “የጌታንም ድምፅ ‘ማንን እልካለሁ? ማንስ ወደዚያ ሕዝብ ይሄድልናል’ ሲል ሰማሁ” (ኢሳ 6፥8) በማለት ፍጹም አንድነቱንና ልዩ ሦስትነቱን አመልክቷል፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
🙏የእግዚአብሔር ቀራቢዎች አገልጋዮች ሱራፌል በምስጋናቸው ሦስት ጊዜ ብቻ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ማለታቸው የሦስትነቱን አካላት መጥራታቸው ነው፤ እግዚአብሔር የሠራዊት ጌታ በማለት በአንድ ስም ጠርተው ምድር ሁሉ ምስጋናህን መልታለች በማለት ያንድ ተመስጋኝ ምስጋናን መስጠታቸው ሦስቱ አካላት አንድ ሕያው እግዚአብሔር፤ አንድ ገዥ፤አንድ አምላክ፤ አንድ ተመስጋኝ አምላክ መሆኑን መመስከራቸው ነው፡፡ ሱራፌልም በዚህ ምስጋናቸው እግዚአብሔር በአካል ከሦስትነት ያልበዛ ሦስት ብቻ እንደ ሆነ በባሕርይ በህልውና ከአንድነት ያልበዛ ሦስት አካል አንድ አምላክ ብቻ መሆኑን ይመሰክሩልናል፡፡
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
ሚስጢረ ስላሴ በሐዲስ ኪዳን ይቀጥላል
┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈
✝️✨✝️✨✝️✨✝️✨✝️✨✝️✨
🔊ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ። ከምታልቀዋ ከዛሬዋ ቀን እስከማይፈጸም ዘመን ። ከደካማው ልባችን እስከ ጸናው ሰማይ።ለዘላለሙ አሜን 🙏
✝️✨✝️✨✝️✨✝️✨✝️✨✝️✨
══════◄✣••✥••✣►══════
🙏 ወስብሐት ለእግዚአብሔር🙏
══════◄✣••✥••✣►══════
💒💒💒💒💒💒⛪⛪⛪⛪⛪⛪
💒 @efr21 📖 @Geb19 ⛪
💒 @Geb19bot🔊 @Geb19 ⛪
💒 @efr21 🔔 @Geb19 ⛪
💒💒💒💒💒💒💒⛪⛪⛪⛪⛪
BY የገኃነም ደጆች አይችሏትም❗️
Share with your friend now:
tgoop.com/Geb19/1582