tgoop.com/Habibacalligraphy/1928
Last Update:
የባከኑ ቀናት
" ማርፈድ ከትምርት ቤት ይልቅ ህይወት ላይ ዋጋ ያስከፍላል"
ክፍል አንድ
(ሂባ ሁዳ)
.
.
"ማሂር" ስሙን ባነሣሁት ቁጥር ፈገግታው ይታወሰኛል። ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ትምህርት ቤት የቀየርኩት፤ ሌሎች ሁለቱ ጓደኞቼ ቀድመውኝ እዛ ትምህርት ቤት ስለገቡ የቀረነው እኔና ኢክራም ስምንተኛ ክፍል እዛው እነሱ ጋር ተመዘገብን። ትምህርት በተጀመረ በሣምንቱ ሰኞ ለመማር ሄድን፤ ግን ደግሞ ሶስታችን አንድ ክፍል ሆነን ኢክራም ግን ሌላ ክፍል ደረሣት። በዚህም ከፍቶን ነበር፤ ምክንያቱም ከመዋለ ህፃናት እስከ ሰባተኛ ክፍል አብረን ነበር የተማርነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ስምንተኛ ክፍል ላይ ተለያየን።
*
የትምህርት የመጀመሪያው ቀን፤ ኢክራምን ወደ ክፍሏ አድርሠናት እኛም ገብተን መማር ጀመርን፤ ረፍት ሰዐት ላይ ኢክሩ መጣች..
<<እንዴት ነው ተመቸሽ ክላሱ? ተዋወቅሻቸው?>> የኔን ያህል የከፋት አትመስልም።
<<አይ ኢክሩ ያላንቺ ሁሉም ነገር ደባሪ ነው ባክሽ። የምን መተዋወቅ.. ከማንም ጋር አልተነጋገርኩም። ዩስራ ና ራቢ ሲቀሩ....ያው ቀስ በቀስ እንለምዳቸዋለን።>> መለስኩላት።
.
ኢክሩ አንድ ቦታ መቆም አትወድም፤ ጊቢውን ዞር ዞር እያልን ማየት ጀመርን። ከመቼው እንደተደወለ ባይገባንም እረፍቱ ሲያልቅ ወደ ክፍል ለመግባት ዞረን ለመመለስ መንገዳችንን ተያያዝን። ኢክሩን ክፍሏ ለማድረስ እየሄድን ዩሲ ና ራቢን ብንፈልጋቸው ልናገኛቸው አልቻልንም። እኔ ላደርሣት ተስማምተን ሶስተኛ ፎቅ ላይ ወደ ሚገኘው ክፍሏ ለመሄድ ደረጃ መውጣት እንደጀመርን ከፊታችን ደረጃ በመውጣት ላይ ያለ ልጅ አየን። ከኢክሩ ጋር ዞር ብለን ተያየን በዛው ቅፅበት <እንዴ ማሂር> እኩል ነበር የጠራነው። ሁለት ድምፅ በአንዴ ሲያደምጥ ወዲያው ዞረ ፤ አየን.. ግራ ተጋብቶ ባለበት ቆመ። እኛ እንደማፈር ብለን እርስ በእርስ ተያይተን ቶሎ አጎነበስን....
*
ከልጁ ጋር ሳንነጋገር ኢክሩን ሸኝቻት ለብቻዬ ወደ ክፍሌ ገባሁ። አስተማሪው ግን አልገባም፤ ተማሪዎች ክፍሉን ቅውጥ አድርገውታል። ብዙዎቹ ሰባተኛ ክፍል አንድ ላይ ስለነበሩ ለመግባባቱ ጊዜ አልፈጀባቸውም። እስካሁን ዩስራ ና ራቢያ አልተመለሱም፤ እኔም ብቻዬን ቁጭ ብያለው። በዚህ ጊዜ ከኃላዬ ያለችውን ልጅ አዲስ ስለሆነች ይመስለኛል አንድ ልጅ ይዝጋታል፤ ደግሞም ያሾፍባታል.. ሌሎች ሁለት ልጆች ደግሞ ይስቃሉ። እሷ ጋር ሲጨርስ እኔም ጋር አፉን ሊከፍት ወደኔ መጣ
<<ስሚ እናቱ ማለቴ ሰሚራ..>>ዝም አልኩት። ከሁለቱ አንዱ
<<ባቢ ዱዳም እኛ ክፍል አለ ማለት ነው?>> ተደረበለት።
<<ሃሃሃ>> ሶስቱም ሣቁ አላናደዱኝም፤ ጅል ነው የመሰሉኝ። እንደናኳቸው ሲገባቸው...
<<ቆይ ማን ነኝ ብለሽ ነው እያናገርንሽ ዝም የምትዪው?>> ባቢ ያሉት ልጅ ነው የሚያወራው። አሁን አላስቻለኝም።
<<ማን ስለሆንክ ማወራህ ይመስልሃል? ቦታህን እወቅ!>> ሣልዞር ነበር የመለስኩለት።
<<አረ ባቢ በፍሬሽ ተማሪ ልሰደብ!>> ብሎ ሲነሳ ዞር ብዬ አየሁት። ወደኔ እየቀረበ ነው.. ሊደባደብ መሆኑ አልጠፋኝም።
<<እንዴ! ባ..ቢ ና ና!>> ይህን ሲሠማ ዞረ፤ እኔም ተከትዬው ዞርኩ። አብረውት ከነበረው ልጅ እስካሁን ዝም ያለው ነበር። ልክ ሣየው ቶሎ ዞር አልኩኝ። <እንዴ ማሂርን የሚመስለው ልጅ ደግሞ ምን ይሰራል እዚህ?> ከራሴ ጋር ነበር...
<<ምንሼ ሎጋው?>> በጥያቄ አስተያየት ማሂርን የሚመስለውን ልጅ ተመልክቶት ግራ እየተጋባ መልስ ይጠብቃል፤ ባቢ። <አሃ ሎጋው ነው እንዴ ስሙ? ማሂር ስንል ምን አዞረው ታዲያ?> ለራሴ አንሸኳሸኩ...
<<በቃ ና አልኩሃ>> ብሎ ተነስቶ ወደ በሩ አመራ፤ "ሎጋው"።
<<አቤላ ምንሼ ነው የሚለው እእ?>> ባቢ አልዋጥልህ እያለው ቢሆንም "ሎጋው"ን ተከትለው ወደ በሩ አከታትለው ሄዱ። ብቻዬን ቀረሁ ባቢ ፣አቤላ ፣ሎጋው፣ አሃ የክፍሉ ጉልቤ እናንተ ናችሁ ማለት ነዋ!....
*
የመጀመሪያው አስተማሪ ሣይገባ ቀጣዩ አስተማሪ መጣ። ከፊት ካሉት ጋር ትንሽ አወራና <<እሽሽሽ ዝምታ!>> ብሎ ዴስኩን መታ መታ አደረገ። ቀጥሎም እሱ ለትምህርት ቤቱ አዲስ እንደሆነና ስማችንን እንድናስተዋውቅ ጠየቀን። ከፊት ጀምሮ እያስተዋወቁ እነ ባቢ ጋር ሲደርስ <<እኔ ባቢ እሱ..>> ብሎ ጓደኛው ጋር ሲደርስ በሩ ተንኳኳ
<<ቆየኝ..>> መምህሩ ለመክፈት ወደ በሩ ተራመደ።
<<አረ ቲቸር እኔ ባጣ ቆየኝ ነኝ እንዴ?>>
<ሃሃሃሃ...> ተማሪው በሳቅ አደመቀው፤ ግማሹ ምን እንደተባለ ሣይሰማ ከተሣቀማ እናድምቀው ይመስል ሳቁን ተቀባበሉት።
<<ኢብቲላ?>> አስተማሪው ነበር፤ በሩን ከፍቶ ወደኛ መለስ እያለ... ከውጪ ዩስራን አየሁዋት። <<የለችም?>> አለ ዝም ሲባል።
<<ኧረ አለች እዛ ጋር...>> ዩስራ ወደኔ እየጠቆመች ታሳየዋለች።
<<አንቺ ስጣራ ለምን ዝም አልሽ?>> አፈጠጠብኝ ።
<<መቼ ጠራኸኝ?>>
<<ኢብቲላ ስል አልሰማሽም?>> ቆጣ አለ።
<<ኧረ የሌላ ሰው መስሎኝ ነው...>> ተማሪው እየቀለድኩበት ስለመሰለው ክፍሉን በሳቅ አናጉት <ሃሃሃሃ..>። መምህሩ ጭራሽ ይበልጥ ተናደደ።
<<ነይ ውጪ እንዳገቢ!>>
<<ለምን?>>
<<ስርዐት የለሽማ!>>
<<ማለት?>> ተማሪው ፀጥ አለ፤ <<አትወጪም!?>> በጣም ጮኸብኝ። ተማሪው ዝም ብሎ የሚሆነውን ይከታተላል፤ ባቢ <<ኧረ እንዳትወጪ.. እንዳሠሚው>> አንሾካሸከ። አስተማሪው ፈጠን ፈጠን እያለ በሩን ብርግድ አድርጎ ከፈተው። በዛው እርምጃው ወደኔ እየመጣ ነው፤ ከመቼው እንደ ደረሠ ባላውቅም አጠገቤ ቆመ። ሲፈጥረኝ ሰውን ንቄ መተው ያስደስተኛል።
<<አንቺ ጎትቼ ሣላወጣሽ ውጪ!!>> እጁን ሲያነሣ ተማሪው በአንድ ድምፅ <ኧረረረረ....> ሊመታኝ መሠላቸው፤ ተንጫጩ።
<<እንዳትነካኝ!!>> ለካ ጮክ ብዬ ነው ያልኩት፤ በአንዴ ጫጫተው በዝምታ ተዋጠ። ከቦታዬ ተነስቼ ቆምኩኝ በዚህ መሃል አንድ አስተማሪ ወደ ክፍላችን ገባ፤ ተቆጣጣሪ ነው። ድምጽ ሰምቶ ነበር የመጣው።
<<ምንድነው?>> ሁላችንንም እያፈራረቀ አየን።
<<በጣም አስቸገረች ክፍሉን እያስረበሸች ነው።>>
<<ኧረረረረ.. እንዴዴዴ...>> አስተማሪው ወደኔ እየጠቆመ ሲያወራ ተማሪው በአንድነት ከቅድሙ በባሰ መልኩ ተጯጯኸ።
<<ዝም በሉ! ነይ አንቺ !>> ተቆጣጣሪው ነበር። እንደለመደብኝ ጅንንን ብዬ ስሄድ
<<ይኸው ንቀቷን እየው>> አስተማሪው፤ እልህ እንደያዘው ያስታውቃል። ሁሉንም አንድ በአንድ ነገረው።
<<ታዲያ ጥፋቱ ያንቺ ነዋ>> ተቆጣጣሪው ኮስተር አለ።
<<አይ አይደለም...>> ረጋ ብዬ መለስኩ።
<<እንዴት?>>
<<ስሜ ኢብቲላ አይደለማ!>>
<<እና ማን ነው?>> ተቆጣጣሪው በመገረም ይመለከተኛል። የኔ ስም ሁሉንም ስለማያውቁት ለመስማት እንደ ፈለጉ ገባኝ።
<<ኢብቲሣም ነው ስሜ>> በጣም ዝቅ ባለ ድምጽ። ተማሪው እእ ቢሉም ምላሽ ግን አላገኙም። ተቆጣጣሪው ከአስተማሪው ጋር ሲነጋገር ወደ ቦታዬ ተመልሼ ተቀመጥኩ። ግን ሁሉም እያዩኝ ነው፤ ምናልባትም <ምኗ ደረቅ ናት> እያሉም ይሆናል።
.
.
ይቀጥላል...
www.tgoop.com/Habibacalligraphy
BY Habiba Calligraphy
![](https://photo2.tgoop.com/u/cdn4.cdn-telegram.org/file/OnYn4Hrm5pf-MHe85p1XgfjdwHy_QENya-owiYC6408KpjW2IyGACbb7YOgv-O64yk3VscAG6b6wG5qhJAkrUXKLnzwkNz3tXma5zsiH2Hl9Y0GRPx03jO987KNUaZJ7d4I2mEpDBc3zUq8HRnOK2dVxpsRhcj3hm-HpNxXuqLtt3XLfMB1Jw_C1XeXPEfaSj9oiIa7H-8yMhbjiLSvBajPKXP_YWTSBanscMytCyCYOZU04brYeBp3jFU_Y7Q6WBUfBInTT_m90TNSSHRmgrDe5zZRbszx7Pmz6yCistm3FW2ibzY1MRKU_4pbsY-b3ZivAQ6S6dBH5Vwv7nbNJFg.jpg)
Share with your friend now:
tgoop.com/Habibacalligraphy/1928