tgoop.com/Hiwotegziabher/1220
Last Update:
🌼 የምወድህ ልጄ ሆይ እንደ ዘመኑ አንተም ተለወጥ🥰
ልጄ ሆይ....... ወጣትነት ፈትኖህ፤ለስጋህ አድልተህ፤ነፍስህን አቀጭጨኻት ከአለም የኖርክበትን ዓመትህን ጥለኸው በንሰሐ እንደ ዘመኑ አንተም ተለወጥ።
ልጄ ሆይ ..... በአዲስ አመት ለአምላክህ የሚገባህን ግብር ትፈፅም ዘንድ በፍቅሩ አፀድ እንድትገኝ ካለመታዘዘ ተለወጥ።
ልጄ ሆይ ....... በአፈር ከሚሸነፈው ስጋዊ ዘርህ ወጥተህ ሰማያዊነትን ከሚያለብስህ ከማይጠፋው ሰማያዊ ዘር ክብረት ታደርግ ዘንድ ሰውን ካለመውደድ ጥላቻ ተለወጥ።
ልጄ ሆይ ...... በምክንያቶች ተደልለህ አፅዋማትን ዘለህ፤ምስጋናን ነፍገህ፥አገልግሎትን ንቀህ ከአለም ጫጫታ ውስጥ የዘፈቀውን ማንነትህ እንዳያጠፋህ እንደ ዘመኑ አንተም ተለወጥ።
ልጄ ሆይ ...... ዲያቢሎስ በቃል እንዳያስትህ፤በማማለል እንዳይጠልፍህ የመንጋውን ጠባቂ ቃልን ስማ፤ የመታዘዝን በረከት ታገኝ ዘንድ ከትምህክትህ እንደ ዘመኑ አንተም ተለወጥ።
ልጄ ሆይ .....ቀናት ሳይሆን መንፈስህ ይለወጥ፤ፀሐይ ሳትሆን የህይወት ጀንበርህ ይለወጥ።
ልጄ ሆይ ......ዕለታት አይሰልጥኑብህ፤ ዘመናት እስከ ሞትህ ጥግ ድረስ እስኪገፉህ ሳትጠብቅ አንተም እንደ ዘመንህ ተለወጥ
ልጄ ሆይ .....የእግዚአብሔር ፍቅር ለተከፈተ ልብ ቸር ነው ። ርህራሄው ጥልቅ ነው ። በአምሳሉ ፈጥሮሃል እና እንዳትጠፋ አንድያ ልጁን ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት የደረስ ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል ። ስለዚህ ከዘመንህ ቀድመህ ተለወጥ።
ልጄ ሆይ ...አዛኝቷን ተለማመን፤መላአኩን ተማለደው ፤ቀደምት ቅዱሳን አባቶችህን ጥራ፤ ፃድቃንን ዘክር እንጅ ላለመለወጥ ተማምለው ቀናት ብቻ ከሚለወጥባቸው ሰልፈኞች ተርታ አትገኝ ።
በንስሐ ወደ በረቱ የምንመለስበት ዘመን ይሁንልን! አሜን
🌻 መልካም አዲስ ዓመት ይሁን ለኹላችን | ሠናይ ሐዲስ ዓመት ይኲን ለኲልነ
🙏🏾ወስብሐት ለእግዚአብሔር🙏🏾
🥰ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ!🥰
@Hiwotegziabher
BY ጥቅሰ መጽሐፍቅዱስ
Share with your friend now:
tgoop.com/Hiwotegziabher/1220