tgoop.com/Hulaadiss/38518
Last Update:
አሜሪካ የውጭ ዕርዳታ እንዲቆም መወሰኗን የሚያሳይ ማስታወሻ ሾልኮ መውጣቱ ተነገረ!
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ዕርዳታ እንዲቆም መወሰኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለባለስልጣናት እና ለውጭ አገራት ለሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የላከው የውስጥ ማስታወሻ ማሳየቱ ተገልጿል።ማስታወሻው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ፖሊሲያቸው ውጤታማነት እና ወጥነት እስኪገመገም ድረስ ለ90 ቀናት የውጭ የልማት ድጋፍ እንዲቆም ሰኞ ዕለት ያሳለፉትን የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝን የተከተለ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።
አሜሪካ ከዓለማችን ትልቁ ዓለም አቀፍ እርዳታ ለጋሽ ስትሆን፤ በአውሮፓውያኑ 2023፣ 68 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን ከመንግሥት የተገኘ መረጃ ያስረዳል።የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያስተላለፈው ትዕዛዝ ከልማት ዕርዳታ እስከ ወታደራዊ ድጋፍ ድረስ የሚሸፍን ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ይህ ሾልኮ የወጣው የውስጥ ማስታወሻ ለድንገተኛ የምግብ ዕርዳታ እንዲሁም፤ ለእስራኤል እና ለግብጽ ወታደራዊ ድጋፍ በስተቀር ሁሉም የውጭ ልገሳዎች እንዲቆሙ የሚያዝ መሆኑ ነው የተነገረው።በተጨማሪም በውጭ አገራት ላሉ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የተላከው ይህ የውስጥ ማስታወሻ፤ "እያንዳንዱ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ማራዘሚያ እስካልተገመገመ እና እስኪጸድቅ ድረስ አይለቀቅም" ሲል ያትታል።
አክሎም የአሜሪካ ባለስልጣናት "ከእርዳታዎች ጋር በተያያዘ በአስቸኳይ የሥራ ማቆም ትዕዛዞችን እንዲያስተላልፉ እና ይህም ግምገማውን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስኪወስንበት ጊዜ ድረስ የሚቆይ ይሆናል" እንደሚልም ዘገባው አመላክቷል።በተጨማሪም ዕርዳታዎች የፕሬዚዳንት ትራምፕን የውጭ ፖሊሲ ግቦች የተከተሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በሁሉም የውጭ ዕርዳታዎች ላይ ሰፋ ያለ ግምገማ በ85 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ያዛል።
አዲሱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ በውጭ አገራት ገንዘብ ማውጣት ያለባት አገሪቷን "ጠንካራ፣ ደኅንነቷ የተጠበቀ ወይም የምትበለጽግ" ካደረገ ብቻ ነው ሲሉ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።ይህ ውሳኔ በአሜሪካ ልገሳ በሚደረግላቸው የውጭ ዕርዳታ ፕሮግራሞች ላይ "ከበድ ያለ ተጽዕኖ" እንዳለው፤ አንድ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን መናገራቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
BY Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Share with your friend now:
tgoop.com/Hulaadiss/38518