tgoop.com/Hulaadiss/38569
Last Update:
እናት ፓርቲ የጣሪያ ግድግዳ/ ንብረት ግብር መመርያ እንዲቆም የመሠረተው ክስ ተቀባይነት ማግኘቱን አስታወቀ
እናት ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የጣሪያ ግድግዳ/ ንብረት ግብር መመርያ እንዲቆም የመሠረተው ክስ በፍርድ ቤት ተቀባይነት ማግኘቱን አስታወቀ። ፓርቲው ዛሬ እንዳለው ክሱ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አስተዳደር ችሎት መመሪያው "ተፈጻሚ ሊሆን አይገባም" ሲል ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ወስኗል። መመሪያው"ሕግን ባልተከተለ መንገድ እና የከተማ አስተዳደሩ ባልተሰጠው ሥልጣን የወጣ በመሆኑ" እንዲሻሻል ሲል መበየኑን ፓርቲው ገልጿል። እናት ፓርቲ የግብር መመሪያውን በዘፈቀደ የተጫነ ነው የሚለው።
የፓርቲው የሕግ እና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዋለልኝ አስፋው ፣ ቢሮው መመርያውን "በሕግ ሥልጣን ሳይሰጠው ያወጣው" ነው በሚልም ለአስተዳደር ችሎት ክስ መስርቶ መቆየቱን ዛሬ አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ክስ ላይ "ፓርቲው የክስ ምክንያት የለውም፣ ክሱ በይርጋ የታገደ ነው" በማለት ወደ ፍሬ ነገር ክርክር ሳይገባ ውድቅ ተደርጎ መዝገቡ ሊዘጋ ይገባል ብሎ ተከራክሮ እንደነበር እናት ፓርቲ ገልጿል።
ሆኖም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አስተዳደር ችሎት ያቀረባቸውን መቃወምያዎች ውድቅ በማድረግ ወደ ፍሬ ነገር ክርክር መገባቱን ፓርቲው አስታውቋል። ፍርድ ቤቱ መመርያው "የመመርያ አወጣጥ መርኾዎችን በመከተል የወጣ አለመሆኑን፣ መመርያው የወጣውም የንብረት ግብር አዋጅ ባልወጣቡት በመሆኑ" ተፈጻሚ አይሆንም ሲልም መወሰኑን ፓርቲው ገልጿል።
የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈ ሥላሴ አያሌው ፓርቲው የውሳኔውን አፈጻጸም እንደሚከታተልና ለዚህም ሲባል "የፍርድ አፈጻጸም ሥልጣን ላለው የአፈጻጸም ፍርድ ቤት ፋይል ለመክፈት" በዝግጅት ላይ ነው ማለታቸውን ከጀርመን ድምፅ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።
BY Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Share with your friend now:
tgoop.com/Hulaadiss/38569