tgoop.com/Hulaadiss/38571
Last Update:
ዩኤስኤይድ (USAID) መፍረስ ያለበት ተቋም ነው” ሲል ኤለን መስክ ተናገረ፡፡ ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ድርጅት የሆነውን ዩኤስኤይድን በተመለከተ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቋል፡፡ ከውይይታቸውም በኋላ ይህ ተቋም መፍረስና መዘጋት እንዳለበት ስምምነት መድረሳቸውን አስረድቷል፡፡
የአሜሪካ የመንግስት ብቃት አስተዳደር መስሪያ ቤት ሀላፊ የሆነው መስክ ዩኤስኤይድን ‹‹የወንጀል ድርጅት›› ሲልም ወቀሳ አቅርቦበታል፡፡ የቴስላ ባለቤት የሆነው መስክ ጨምሮም ‹‹የዩኤስ ኤይድ ሰራተኞችን በተመለከተ ከፕሬዝደንቱ ጋር በዝርዝር ተነጋግረንበታል፡፡ ይህ ትልቅ ኳስ በትሎች ተወሯል፡፡ በመሆኑም ሁሉንም ነገር ከስር መሰረቱ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ የዩኤስኤይድ ችግር ከጥገናም በላይ ነው፡፡ ድርጅቱ በመፍረሱ ላይ እሳቸው ማለትም ፕሬዝደንቱም ተስማምተዋል›› ብሏል፡፡
ኤለን መስክ በኤክስ ስፔስ ላይ ይህንን አስተያየት የሰጠው የሚመራው የመንግስት ብቃት አስተዳደር መስሪያ ቤት ተወካዮች በዋሽንግተን የሚገኘውን የዩኤስኤይድ ዋና ፅህፈት ቤት መረጃዎች መመልከታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ከቀናት በፊት በዋና ፅህፈት ቤቱ የሚገኙ ሚስጢራዊ መረጃዎችን የዩኤስ ኤይድ ከፍተኛ አመራሮች ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀው ነበር፡፡ ይሁንና በዚህ የተነሳ ሁለት ከፍተኛ የዩኤስ ኤይድ አመራሮች ከስራ እንዲባረሩ ከተደረጉ በኋላ መረጃዎቹን ለማግኘትና ለመመልከት እንደተቻለ ዘገባዎች አስረድተዋል፡፡
ዩኤስ ኤይድ በመላው አለም ከሴቶች ጤና ጀምሮ እስከ መጠጥ ውሀ፣ ኤችኤቪ ኤድስ፣ የሀይል አቅርቦትና ፀረ ሙስና ትግሎች ድረስ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ሲያቀርብ የቆየ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ትራምፕ አገራቸው የምትሰጠውን ማናቸውንም እርዳታዎች ለዘጠና ቀናት እንድታቆም ያስተላለፉትን ትእዛዝ ተከትሎ ይህ ተቋምም እንቅስቃሴዎቹን ማቋረጡን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚህ የተነሳም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት በዩኤስ ኤይድ ድጋፍ የሚከናወኑ በርካታ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ ተደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል የዩኤስ ኤይድ ድረ ገፅና የኤክስ አካውንት ከቅዳሜ ጀምሮ መዘጋቱን ማስታወቃችን አይዘነጋም፡፡
BY Hule Addis Media ( ሁሌ አዲስ ሚዲያ)
Share with your friend now:
tgoop.com/Hulaadiss/38571