tgoop.com/KALTUBE/11380
Last Update:
በክርስቶስ IN CHRIST
ክፍል 40
የወንጌል ኃይል
የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ።ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ። ርኵሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን፦ “እኔ ታላቅ ነኝ፡” ብሎ፡ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ። ከታናናሾችም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ፦ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው፡” እያሉ ሁሉ ያደምጡት ነበር። ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላ ስላስገረማቸው ያደምጡት ነበር። ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ። ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ። ሐዋር 8:4-13
➢በሐዋርያት ዘመን ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ ቤተክርስቲያን በታላቅ ስደት ላይ ነበረች። ምንም እንኳን ሰደት ላይ ቢሆኑም ተሰደው በሄዱበት ሰማርያ ወንጌልን ይሰብኩ ነበር።
➢ከላይ በመግቢያ ጥቅሳችን ላይ እንዳነበብነው እውነተኛ ወንጌል በሚሰበክበት በየትኛውም ጊዜና ቦታ የእግዚአብሔር ኃይል ይገለጣል። ወንጌል ኃይል የታጠቀ የእግዚአብሔር መልእክት ነው።
➢ወንጌል ወደ ሰማርያ እስከደረሰበት ጊዜ ድረስ ሕዝቡ የእግዚአብሔር ኃይል እያለ አምኖ የተቀበለው የጥንቆላን ኃይል ነበር።ሲሞን የተባለው ጠንቋይ የሰማርያን ነዋሪዎች ከማስደነቅ አልፎ ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ተብሎ ታምኖ ነበር።
ነገር ግን ፊልጶስ ወንጌል እየሰበከ ሲመጣ የእግዚአብሔር እውነተኛ ኃይል መገለጥ ጀመረ፣ የጥንቋላ አሰራር መፍረስ ጀመረ፣
ህዝቡን በተአምራት ሲያስደንቅ የነበረው ጠንቋይ ሲሞን እራሱ በእግዚአብሔር ኃይልና በፊልጶስ በሚደረገው ተአምራት መደመም ጀመረ። ይህ ብቻ አይደለም ደስታ ያጣችው ሰማርያ ታላቅ ደስታ ሆነላት።
➢ወንጌል የትኛውንም ኃይል የሚሽር ፣የትኛውም ኃይል የማይቋቋመው የመለኮት ኃይል ነው።
➢የኛ የአማኞች ድርሻ ወንጌል መስበክ ነው።
ወንጌል መስበክ የሰይጣንን ስራ ያፈራርሳል የእግዚአብሔርን መንግስት ደግሞ ያስፋፋል።
➢ቤተክርስቲያን ምስባክ ላይ ሆነ በየትኛውም አጋጣሚ የቆጥ የባጡን ሳይሆን ወንጌል መስበክ አለባት።ወንጌል ኃይል አለው። ወንጌል ሲሰበክ ተአምራት በራሱ ጊዜ መከሰት ይጀምራል። ወንጌል ጠንካራና ድንጋይ ልቦችን ያቀልጣል። ወንጌል በየትኛውም አመክንዮ የተወጠሩ ጭንቅላቶችን አሳምኖ ማሸነፍ ይችላል። ወንጌል ከተማን ይፈውሳል፣ወንጌል ማህበረሰብን ይለውጣል፣ ወንጌል ትውልድን ይባርካል።
ወንጌልን በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት፣በስራ ቦታ፣በየመንገዱ፣ በከተማ ፣በገጠር ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንስበክ። በዚህ አጋጣሚ ወንጌል በመስበክ ላይ የተጠመዳችሁ ውድ የጌታ ልጆች ፀጋ ይብዛላችሁ።ተባረኩ!!
✍ መሳይ አለማየሁ (ነቢይ)
ክፍል 41 ይቀጥላል
👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
@KALTUBE
@KALTUBE
@KALTUBE
BY #KALTUBE
Share with your friend now:
tgoop.com/KALTUBE/11380