tgoop.com/Ortodoxe19/5019
Last Update:
"ኑ ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ"
(ብፁእ አቡነ ሺኖዳ)
ኑ ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ ፤ ኑ በፀሎት ወደአምላክ ቅረቡ ፤ በፀሎት ማለት እንዴት ነው? ይህስ የልባችሁን ምስጢር ሁሉ ሳትደብቁ እርሱ እግዚአብሄር እንደሚያስፈልጋችሁ መናገር ማለት ነው ፤ እንዲህም በሉ ፦ “ጌታ ሆይ ወደ አንተ መምጣት እፈልጋለሁ ፡ ጌታ ሆይ ካንተ ተለይቼ እኔ ምንም ነኝ ፡ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ህይወቴን አጣሁ ፤ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ደስታየን ሁሉ አጣሁ ፤ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ህይወቴ ትርጉም አልባ ሆነ ፤ ጌታ ሆይ እኔ አንተን ያጣሁ እለት ህይወቴ ጣእም አልባ ሆነ” በሉ ፤ ዳግምም ከእግዚአብሄር እግር ስር ተደፍታችሁ እንዲህ በሉት፦ “ አምላኬ ሆይ ፦ ወደ አንተ መመለስ እፈልጋለሁ ፤ ነገር ግን ጠላቶቼ ከእኔ በእጅጉ የሚበልጡ ናቸው ፤ ነፍሴንም አምላክሽ አያድኑሽም የሚሏት ብዙ ናቸው” ፡፡
ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ ፤ “ ጌታ ሆይ ታደገኝ ወደ አንተ የምመለስበትን መንገድ ምራኝ” በሉት ፤ ለአምላካችሁ ንገሩት ፦ “ካንተ ከተለየሁ ወዲህ አቅሜ ሁሉ ተዳክሟልና ጌታ ሆይ ልዩ ሃይልህን ላክልኝ ፡ ወዳንተ የምመለስበትን ልዩ ርዳታህን ስጠኝ ፤” በማለት፡፡ ብዙ ሰወች በመደጋገም “ወደ እግዚአብሄር የምመለሰው እንዴት ነው ?” ይላሉ፡፡ ከእግዚአብሄር እግር በታች ራሳችሁን ጣሉ ፡ እንዲህም በሉት ፦ “ ጌታ ሆይ ሳትባርከኝ አልለቅህም ፡ ወዳንተ አቅርበኝ ፡ ከልጆችህ እንደአንዱ አድርገኝ ፡ ሃጢአቴን ብቻ ይቅር እንድትልልኝ አልሻም ፡ ይልቁንም ከሃጢአት ፍቅር ትለየኝ ዘንድ ጭምር እንጂ ፡”በሉት ፦ ዳግምም “ ጌታ ሆይ የሃጢአት ፍቅር ልቤን ተቆጣጥሮታልና ይህን ካላስወገድኩ ወዳንተ መቅረብ አይቻለኝም ፡ ጌታ ሆይ የሃጢአትን ፍቅር ከልቤ ላይ ንቀል ፡” በሉት ዳግምም እንዲህ በሉት ፦ ”ጌታ ሆይ ከሃጢአቴ ነፅቼ ወዳንተ መምጣት እንደምን ይቻለኛል? ይልቁንስ መጀመሪያ አንተ ናልኝ ሃጢአቴንም ደምስስ እንጂ “ እንዲህም በሉት ፦ “ በራሴማ ሃጢአትን ማስወገድ ብችል ወዳንተ መቼ መመለስ ያቅተኝ ነበር? እኔ ግን አንተ ከሃጢአቴ እንድታርቀኝ እወዳለሁ ፡ ጌታ ሆይ ፦ ሃይልህን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” በሉት፡፡
እመኑኝ የምወዳችሁ ልጆቼ ፦ ትክክለኛዋን ፀሎት ያወቃት እርሱ ትክክለኛዋንም ንስሃን የሚያውቅ እርሱ ነው ፤ ማር ይስሃቅ እንደተናገረው ፦ “ንስሃ ከፀሎት ውጭ እንደሚገኝ የሚያስብ ሰው እርሱ በዲያቢሎስ የተታለለ ነው” ምክንያቱም በፀሎት ወደ እግዚአብሄር የምትመለሱበትን ሃይልን ታገኛላችሁና፡፡ ስለሆነም ከየትኛውም ስራ ይልቅ ራሳችሁን ለፀሎት አስገድዱ ፤ ምክንያቱም በፀሎት አማካኝነት በእናንተና በእግዚአብሄር መካከል ያለውን ግድግዳ አስወግዳችሁ እንደገና ወደእርሱ ትመለሱ ዘንድ ይቻላችኅልና ፤ በጣም ብዙ ሰወች ከፀሎት ይልቅ ለአገልግሎት መትጋታቸው የሚገርም ነው ወይንም ከፀሎት ይልቅ በንባብ የሚተጉትም እንደዚያው ወይንም ከፀሎት ይልቅ በተመስጦ የሚተጉትም እንደዚያው ወይንም ከፀሎት ይልቅ በመንፈሳዊ ስብሰባወች ለመታደም የሚተጉትም እንደዚያው ፤ ለዚህ እኮ ነው ከእግዚአብሄር ጋር ባላቸው ግንኙነት የማይሳካላቸው ፤ ይፀልያሉ ያነባሉ ደግሞም ስብሰባወችን ይታደማሉ በዚህ ሁሉ ሰአት ከእግዚአብሄር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም ፤ ምንም አይነት ግንኙነት ፡፡
ወደ እግዚአብሄር ተመለሱ ፤ ወደእግዚአብሄር ተመለሱና ከእርሱ ውሰዱ ፤ አንዳንድ ሰወች በመፀለይ ለእግዚአብሄር የሚሰጡት እንዳለ ያስባሉ ፡ ለእግዚአብሄር ቃላትን ይሰጡታል ፡ ጊዜን ፡ ምናልባትም ስሜታቸውን ፤ ነገር ግን ጥልቅ የሆነ ፀሎት ከእግዚአብሄር የመውሰድ ጉዳይ ነው ፤ እርሱ ሰጭ እንጂ ተቀባይ አይደለምና ፤ በፀሎቱ ስኬታማ ውጤትን የሚያመጣ ሰው እርሱ ከእግዚአብሄር ስለሚወስደው የፀለየና እንደዚያም የሚያምን ነው ፤ እርሱ ነው በፀሎቱ የተሳካለት፡፡ በምትፀልዩበት ጊዜ ከእግዚአብሄር ሃይልን እንደተቀበላችሁ ከተሰማችሁ ፡ ያን ጊዜ ውጤታማ ፀሎት ፀለያችሁ ፤ አንድ ሰው ፀልዮ ከእግዚአብሄር በረከት ከተቀበለ፡ እንግዲህ ይህ ሰው ነው ውጤታማ ፀሎት ያቀረበው ፤ ማንም በፀሎት በፀፀትና በንስሃ ወደእግዚአብሄር ቢቀርብ እርሱ ውጤታማ ፀሎትን አቀረበ ፤ አንድ ሰው ቢፀልይና ለቅድስና ቢታገል ፡ ይህ ሰው ፀሎቱ ውጤታማ ሆነ ፤ አንድ ሰው ቢፀልይና ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን ግንኙነት ቢያጠናክር ይሄኔ ውጤታማ ፀሎትን አቀረበ፡፡
እግዚአብሄር እንድትመጡ ይናገራችኅል ፡ በፀሎት ኑ ና የሚያስፈልጋችሁን ልስጣችሁ እያለ ፤ ነገር ግን እናንተ ለሁለት ደቂቃ ብቻ ትፅልዩና ወዲያው ትሰለቻላችሁ ፡ ከእግዚአብሄርም አንዳች ሳትቀበሉ ትሄዳላችሁ ፤ እግዚአብሄር ወደእናንተ ያይና እንዲህ ይላል ፦ “ስለምን ከእኔ ሳትቀበሉ ተመለሳችሁ? የሚያስፈልጋችሁን ልሰጣችሁ ወድጄ ነበርና ፤ ስለምን ቶሎ ተመለሳችሁ ያዘጋጀሁላችሁን ሳትወስዱ?” እያለ ፤ ነገር ግን እናንተ ቶሎ ሰለቻችሁና ለመሄድ ወሰናችሁ ፤ እሺ ሂዱ ፡ ከዚያ ግን እግዚአብሄርን መፈለግ ትጀምራላችሁ አታገኙትም ፤ ጥላችሁ ስትሄዱ ያጣችሁት ምንም ሳትይዙ መሄዳችሁን ብቻ እንዳይመስላችሁ በልባችሁ ለእግዚአብሄር ጊዜ እንደሰጣችሁት ማሰባችሁም ጭምር እንጂ ፤ ወዲያውም ከመንፈሳዊ የስኬት ድርጊቶች ውስጥ መፀለያችሁን ትፅፋላችሁ፡፡
ይህ ግን ፀሎት አይደለም!!! ከእግዚአብሄር ከቶ ምን አገኛችሁ? እግዚአብሄርን አጥብቃችሁ ልትይዙት ይገባል አጥብቃችሁ መቼም ቢሆን ካንተ አልለይም መለየትም አልፈልግም ማለት አለባችሁ፡፡ ስለዚህ እኮ ነው ለፀሎት ትእግስት የሚያስፈልገው፤ ያለትእግስት ከእግዚአብሄር አንዳች እንኳን ልትቀበሉ አትችሉም፤ በፀሎታችሁ ትእግስተኞች ልትሆኑ ይገባችኅል፤ እግዚአብሄርን ንገሩት፦ ከእግርህ በታች እንደሆንኩ እቆያለሁ በረከትህንም ሳትሰጠኝ አልነቃነቅም ከእግዚአብሄር በረከትን ካልተቀበልኩ እርሱን መያዜን አልለቅም ካልባረከኝ አልለቅህም እይዘዋለሁ ወዴትም ይሄድ ዘንድ አልተወውም፤ እንግዲህ ይህ ነው በፀሎት ውስጥ ያለው ትግል፤ ሰወች ፀሎት እንዴት እንደሚፀለይ አልተማሩም እነርሱ የሚያስቡት ፀሎት ማለት ጥቂት ቃላትን መናገር ይመስላቸዋል አይደለም፡፡
ፀሎትን አዘውትሩ፡- ከእግዚአብሄርም አንዳች እስክትቀበሉ ድረስ ታገሉ ፤ አንዳች እንኳን ካልወሰዳችሁ ሳትቀበሉ የትም እንደማትሄዱ ንገሩት ፀሎቴን አልገታም በሉት እንደተፃፈ አንተ ሩህሩህ መሃሪ አምላክ ነህ የለመነውን ሁሉ የምትሰጥ ነህና እንግዲህ እኔም ለምኜሃለሁ እስከምትሰጠኝ ድረስ ወዴትም አልሄድም በሉት፤ በፀሎታችሁ ከእግዚአብሄር ጋር ታገሉ ያን ጊዜ ታርፋላችሁ በፍቅር ትሞላላችሁ በፀሎታችሁም ብርቱ ትሆናላችሁ ከንቱ ነገርንም መደጋገም ትተዋላችሁ እንዲያውም ልባችሁን በእግዚአብሄር ፊት ትዘረጋላችሁ፤ የሳሙኤል እናት ሃና በፀሎቷ ጊዜ ታለቅስ ነበር በልቧም ልጅ እንደምታገኝ ቃል ሳይገባላት ከቤተመቅደሱ ላለመውጣት ወስና ነበር ፤ ንጉስ ዳዊት ከእግዚአብሄር በረከትን እስኪቀበል ድረስ ፀሎቱን አላቋረጠም በመጀመሪያ “ጌታ ሆይ ፦ አስጨናቂወቼ ምንኛ በዙ” በማለት ፀለየ፤ ቀጥሎም እንዲህ አለ ፦ “ እናንተ ክፉ አድራጊወች ከእኔ ራቁ እግዚአብሄር ፀሎቴን ሰምቶልኛልና ፡ ጌታየ የልመናየን ድምፅ አድምጧልና ጌታየ ፀሎቴን ሰምቷልና“፡፡ ኑ ወደእግዚአብሄር ተመለሱ፡፡
@Ortodoxe19
@Ortodoxe19
@Ortodoxe19
BY ✟ የተዋህዶ ልጆች ✟
Share with your friend now:
tgoop.com/Ortodoxe19/5019