tgoop.com/Wahidcom/3950
Last Update:
ሡጁዱ አት ተሒያህ
በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
2፥34 ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡ وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ
"ተሒያህ" تَحِيَّة የሚለው ቃል "ሐያ" حَيَّا ማለትም "አከበረ" "ሰላም ሰጠ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "አክብሮት" "ክብር" "መከባበር" ማለት ነው፦
25፥75 እነዚያ በመታገሳቸው የገነትን ሰገነቶች ይመነዳሉ፥ በእርሷም ውስጥ "አክብሮት" እና ሰላምታን ይስሰጣሉ፡፡ أُولَـٰئِكَ يُجْزَوْنَ الْغُرْفَةَ بِمَا صَبَرُوا وَيُلَقَّوْنَ فِيهَا تَحِيَّةً وَسَلَامًا
33፥44 በሚገናኙት ቀን "መከባበሪያቸው" ሰላም መባባል ነው፥ ለእነርሱም የከበረን ምንዳ አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ تَحِيَّتُهُمْ يَوْمَ يَلْقَوْنَهُ سَلَامٌ ۚ وَأَعَدَّ لَهُمْ أَجْرًا كَرِيمًا
እነዚህ አናቅጽ ላይ "አክብሮት" "መከባበር" ለሚለው የገባው ቃል "ተሒያህ" تَحِيَّة ነው፥ በጥቅሉ "ሡጁዱ አት ተሒያህ" سُجُود الْتَحِيَّة ማለት "የአክብሮት ስግደት" ማለት ነው። ይህንን ከተረዳን ዘንዳ አምላካችን አሏህ ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ያለው ስግደት የአክብሮት ስግደት ነው፦
2፥34 ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡ وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ
ቁርኣን ከመውረዱ በፊት የአክብሮት ስግደት በሩቅ ሳይሆን በአካል የአክብሮት ስላምታ መስገድ ሐላል ነበረ፥ የዩሡፍ እናት እና አባት እንዲሁ ወንድሞቹ የአክብሮት ስግደት ለዩሡፍ ሰግደዋል፦
12፥4 ዩሡፍ ለአባቱ፡- «አባቴ ሆይ! እኔ አሥራ አንድ ከዋክብትን፣ ፀሐይን እና ጨረቃን በሕልሜ አየሁ፥ ለእኔ ሰጋጆች ሆነው አየኋቸው» ባለ ጊዜ አስታውስ፡፡ إِذْ قَالَ يُوسُفُ لِأَبِيهِ يَا أَبَتِ إِنِّي رَأَيْتُ أَحَدَ عَشَرَ كَوْكَبًا وَالشَّمْسَ وَالْقَمَرَ رَأَيْتُهُمْ لِي سَاجِدِينَ
12፥100 ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፡፡ አለም፦ ለእርሱም ሰጋጆች ኾነው ወረዱለት፡፡ «አባቴም ሆይ! ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፡፡ ጌታ በእርግጥ እውነት አደረጋት፡፡ وَرَفَعَ أَبَوَيْهِ عَلَى الْعَرْشِ وَخَرُّوا لَهُ سُجَّدًا ۖ وَقَالَ يَا أَبَتِ هَـٰذَا تَأْوِيلُ رُؤْيَايَ مِن قَبْلُ قَدْ جَعَلَهَا رَبِّي حَقًّا
የጸጋ ስግደት"Graceful Prostration" ከአሏህ በስጦታ የተቸረ የአክብሮት ስግደት ሲሆን ነገር ግን ይህ የአክብሮት ስግደት ሲለጠጥ ለመላእክት፣ ለነቢያት፣ ለጻድቃን እና ለሰማዕታት መለኮት ባልሆኑበት ሁኔታ ሰዎች እየተለማመኑ ሲሰግዱ ወደ የአምልኮ ስግደት እየተቀየረ ሲመጣ ቁርኣን ሲወርድ ተከለከለ፥ አሏህም "እርሱን ብቻ የምታመልኩ እንደ ኾናችሁ ለሌላ አትስገዱ" ብሎናል፦
41፥37 ሌሊት እና ቀን ፀሐይ እና ጨረቃ ከምልክቶቹ ናቸው፥ ለፀሐይ እና ለጨረቃ አትስገዱ! ለእዚያም ለፈጠራቸው ለአሏህ ስገዱ፡፡ እርሱን ብቻ የምታመልኩ እንደ ኾናችሁ ለሌላ አትስገዱ፡፡ وَمِنْ آيَاتِهِ اللَّيْلُ وَالنَّهَارُ وَالشَّمْسُ وَالْقَمَرُ ۚ لَا تَسْجُدُوا لِلشَّمْسِ وَلَا لِلْقَمَرِ وَاسْجُدُوا لِلَّهِ الَّذِي خَلَقَهُنَّ إِن كُنتُمْ إِيَّاهُ تَعْبُدُونَ
ተወዳጁ ነቢያችንም"ﷺ" በሐዲስ ላይ የአክብሮት ስግደትን ከልክለዋል፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 9, ሐዲስ 1926:
ዐብደላህ ኢብኑ አቢ ዐውፋ እንደተረከው፦ ”ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል ከሻም ምድር በተመለሰ ጊዜ ለነቢዩ”ﷺ” ሰገደ፥ እሳቸውም፦ “ሙዓዝ ሆይ! ይህ ምንድነው? አሉት። እርሱም፦ “ሻም ምድር ሄጄ ነበር፥ ለኤጲስ ቆጶሳቶቻቸው እና ለጳጳሳቶቻቸው ሲሰግዱ ተመለከትኩ። ይህንን ለእርሶ በራሴ ልሠራው ተመኘሁ” አለ። የአሏህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ “ይህንን በፍጹም እንዳትሠሩ!”። عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ أَبِي أَوْفَى، قَالَ لَمَّا قَدِمَ مُعَاذٌ مِنَ الشَّامِ سَجَدَ لِلنَّبِيِّ ـ صلى الله عليه وسلم ـ قَالَ ” مَا هَذَا يَا مُعَاذُ ” . قَالَ أَتَيْتُ الشَّامَ فَوَافَقْتُهُمْ يَسْجُدُونَ لأَسَاقِفَتِهِمْ وَبَطَارِقَتِهِمْ فَوَدِدْتُ فِي نَفْسِي أَنْ نَفْعَلَ ذَلِكَ بِكَ . فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ ” فَلاَ تَفْعَلُوا
BY ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics"
Share with your friend now:
tgoop.com/Wahidcom/3950