tgoop.com/amalajeelatalehu/130
Last Update:
ፍልሰታ ምን ማለት ነው?
ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ለዚህ ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፤ "ፍልሰታ ማለት ፈለሰ /ተሰደደ/ ከሚለው ግስ የወጣ ነው።"
‹ፍልሰት› ማለት ደግሞ የተለያየ ትርጕም ቢሰጠውም ‹ፍልሰታ ለማርያም› ተብሎ ሲገለጽ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ወደ ማያልፈው ዓለም ከመቃብር የወጣችበት (የተነሣችበት) ቀን ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሥጋዊው ዓለም ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተሸጋገረችበት ማለት ነው፡፡››
ቀሲስ ስንታየሁ አባተም በተመሳሳይ መልኩ ስለ ፍልሰታ እንዲህ በማለት ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
‹ፍልሰታ ለማርያም› የሚለው የግእዝ ቃል ሲኾን ‹ፍልሰታ› ማለት ደግሞ ‹ፈለሰ› ከሚል ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ፍልሰት› ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድን (መፍለስን) ያመለክታል፡፡ እመቤታችን ካረፈች በኋላ የሥጋዋን መፍለስ አስመልክቶ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደ ተቀበረ አላወቁም ነበርና እግዚአብሔር የእመቤታችንን ሥጋ እንዲገልጥላቸው የጾሙት ጾም ነው፡፡
ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ ጾመው የእመቤታችንን ሥጋዋን ሰጥቷቸው ትንሣኤዋንና ዕርገቷን በማየት በረከት ያገኙበት ጾም ነው፡፡ ስለኾነም ምእመናን ፍልሰታ ለማርያምን ከልጅ እስከ አዋቂው በጾም በጸሎትና በመቍረብ በጋራ በፍቅር፣ በሰላም ያሳልፉታል፡፡››
ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ እንዳብራሩት ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን እንዲጠብቃት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት ‹‹የእመቤታችን ነገር እንዴት ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ‹‹እመቤታችንማ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ናት›› ብሎ ነገራቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ሐዋርያት እመቤታችን ከመቃብር መነሣቷንና ማረጓን ማየት አለብን፤ እንዴት ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በመንፈሳዊ ቅናት በመነሣሣት ነሐሴ አንድ ቀን በዕለተ ሰኞ ሁለት ሰባት ሱባዔ ያዙ፡፡ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ አንሥቶ ሰጣቸውና በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ እመቤታችን በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋ ነሐሴ ፲፬ ቀን ተቀብራለች፡፡
ይኹንና ሐዋርያት ቢቀብሯትም ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አላዩም ነበር፡፡ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ያየው ሲቀብሯት ያላየው ሐዋርያው ቶማስ ነው፡፡ ቶማስ እንዲያስተምር ሕንድ አገር ዕጣ ደርሶት አስተምሮ በደመና ሲመለስ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችን ስታርግ ሕዋ ላይ ተገናኙ በማለት ሊቀ ማእምራን ደጉ ያስረዳሉ፡፡
እንደ እርሳቸው አገላለጽ ምእመናን ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚዘከርበት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነ ጾም ነው፡፡ በየዓመቱ ሕፃን አዋቂው ሳይቀር የእመቤታችን ፍቅር አድሮባቸው ጾሙን ይጾማሉ፣ ያስቀድሳሉ፤ ይቈርባሉ፡፡
የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሊቀ ማእምራን ደጉ ምላሽ ሲሰጡም "ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዐስራት ሀገር በመሆኗ እና ሕዝበ ክርስትያኑ ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ስላላቸው መሬት ላይ እየተኙ፣ ጥሬ እየበሉ በሰላም በፍቅር ይጾሙታል፡፡
ምእመናን ፍልሰታን ከሌሎች አጽዋማት በተለየ መልኩ መሬት ላይ እየተኙ ይጾሙታል፡፡ ይህ ደግሞ የእመቤታችን ፍቅር ስለሳባቸው ነው ፍቅር›› በማለት ያብራራሉ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ!
BY አማላጄ ነሽ እላታለሁ
Share with your friend now:
tgoop.com/amalajeelatalehu/130