tgoop.com/amalajeelatalehu/153
Last Update:
"ሥጋ በዝሙት እንደሚረክስ ኹሉ፥ ነፍስም በሰይጣናዊ አሳቦች፣ በእኩይ ሃይማኖትና በእኩይ ግብር ትረክሳለች፡፡ አንድ ሰው "በሥጋ ድንግል ነኝ" ቢል፥ ነገር ግን በወንድሙ የሚቀና ከኾነ እርሱ ድንግል አይደለም፡፡ ከቅናት ጋር ሩካቤ ስለ ፈጸመ ድንግልናውን አጥቷል፡፡ ውዳሴ ከንቱን የሚወድድም እርሱ ድንግል አይደለም፡፡ የቅናት ስሜት ክብረ ድንግልናውን አሳጥቶታል፡፡ ስሜት ወደ ውሳጤው ዘልቆ ገብቶ የነፍሱን ድንግልና አፍርሶበታልና። ወንድሙን የሚጠላም እርሱ ድንግል ከመኾን በላይ ነፍሰ ገዳይ ነው። በአጠቃላይ እያንዳንዱ ሰው በተገዛለት ክፉ ስሜት ድንግልናውን ያጣል። ስለዚሁ ምክንያትም ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህን ኹሉ መቀላቀሎችን አራቀ የነፍሳችን ጸር የኾኑ ማናቸውንም አሳቦች ወደን ፈቅደን ባለመቀበል ደናግል እንድንኾን አዘዘን።
እንግዲህ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ልንናገረው የሚገባን ምንድን ነው? የእግዚአብሔርን ምሕረት ልንቀበል የምንችለው እንዴት ነው? ልንድን የምንችለውስ እንዴት ነው? ጸሎትንና የጸሎት ፍሬዎች የኾኑትን እነርሱም ትሕትናንና የውሃትን ዘወትር ለራሳችን እንያዝ ብዬ እነግራችኋለሁ። እርሱ “ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ" ብሎአልና (ማቴ.11፥29)። ክቡር ዳዊትም፦- “የተሰበረን መንፈስ ለእግዚአብሔር ሠዋ፤ የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” ብሎአል (መዝ.50፥17)። እግዚአብሔር ከተሰበረ፣ ትሑት ከኾነና ከሚያመስግን ልብ በላይ አጥብቆ የሚወድደው የለምና።
ስለዚህ ወንድሜ! አንተም ያላሰብከውና የሚያናውጽ መከራ ቢገጥምህ መጠጊያ ይኾኑህ ዘንድ ሰዎችን እንዳትመለከት፤ ዘላቂና ቋሚ ያይደለ እርዳታን እንዳትፈልግ ተጠንቀቅ። ይልቅ ኹሉንም ናቃቸው፤ በአሳብህም መድኃኒተ ነፍሳት ወደ ኾነው ወደ እግዚአብሔር ተፋጠን። ልባችንን መጠገን (መፈወስ) የሚቻለው ልባችንን ብቻውን የሠራ (የፈጠረ) እና ግብራችንን ኹሉ የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነውና (መዝ.32፥15)። ወደ ሕሊናችን ጓዳ መግባት፣ አሳባችንን መመርመር ልባችንንም ማጽናናት ሥልጣን (ኃይል) ያለው አርሱ ብቻ ነውና። እርሱ ልባችንን ካላጽናና ሰዎች ኹሉ የሚያደርጉልን ነገር ትርፍና ረብ የለሽ ነውና። እግዚአብሔር ሲያጽናናንና ሲያረጋጋን ግን እንደ ገና ሰዎች ቍጥር በሌለው መከራ ቢያውኩንም በፍጹም እኛን መጉዳት አይቻላቸውም፤ እርሱ ልባችንን ጽኑዕ ሲያደርግ ማንም እኛን ለማነዋወጽ ኃይል የለውምና።"
(ንስሓ እና ምጽዋት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው ገጽ 73-74 ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው)
ለሌሎች ያካፍሉ!
BY አማላጄ ነሽ እላታለሁ
Share with your friend now:
tgoop.com/amalajeelatalehu/153