tgoop.com/atronss/5400
Last Update:
የአብያተ ክርስቲያናት አርማ
| ጃንደረባው ሚድያ | ኅዳር 2016 ዓ.ም.|
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አርማዋ መስቀል ነው:: "ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሠጠሃቸው" የሚለው ቃልም የሚፈጸመው በዚሁ መንፈሳዊ አርማ ነው:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለአስተዳደር እንዲመች ደግሞ በአህጉረ ስብከት ተከፍላ እንደምታገለግል ይታወቃል:: ለዚህ መንፈሳዊ አስተዳደርዋ ደግሞ ለእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን የራሱ መታወቂያ የሆነ አርማ (logo) እና ዓላማ (emblem) አለው:: ኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የየራሳቸው አርማ አላቸው:: አርማዎቹም ትርጉም ያላቸውና አብያተ ክርስቲያናቱን የሚገልጹ ናቸው::
የጥቂቶቹን እንመልከት :-
⛪️ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አርማ
በአራቱም በኩል እኩል የሆነ መስቀል ሲሆን እያንዳንዱ ሦስት ቀስት ያለው መሆኑ ቅድስት ሥላሴን ይወክላል:: ሙሉው ሲቆጠር ዐሥራ ሁለት ቀስቶች መሆናቸው ደግሞ ቅዱሳን ሐዋርያት በሰበኩት ወንጌል ላይ ቤተ ክርስቲያን መመሥረትዋን ያስረዳል:: በመስቀሉ ዙሪያ ያለው ቃል ደግሞ በኮፕቲክ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን "ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር" ማለት ነው::
⛪️ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አርማ
ከላይ የሚታየው መስቀልና ከሥሩ ያለው አርዌ ብርት በሞቱና በትንሣኤው ለቤተ ክርስቲያንን ድል ነሺነትን የሠጠ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሲሆን አርዌ ብርቱ ደግሞ በፓትርያርኮች እጅ የሚያዘው "ሙሴ በምድረ በዳ ዕባብን እንደሰቀለ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል" የሚለውን ቃል የሚያስረዳ ያለ በደል ስለ እኛ ተሰቅሎ ያዳነንን ክርስቶስን የሚያሳይ ነው:: ከመስቀሉ ሥር ያለው ብርሃን በመስቀሉ ጨለማን ያራቀ የመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ የማዳኑን ሥራ የሚያስረዳ ነው:: በመካከል ያለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ከሥር ባለው መጽሐፍ ቅዱስ ላይም የተጻፈው "ቃል ሥጋ ሆነ" የሚለውን የተዋሕዶ መሠረት የሆነ ቃል ነው::
በዙሪያ ያለው የስንዴና ወይን ዘለላ ደግሞ ምሥጢረ ቁርባንን የሚያሳይ ነው::
⛪️ የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አርማ
ከላይ የሚታየው የጳጳሳት አስኬማ ከሐዋርያት ጀምሮ በቅብብል የመጣውን የፓትርያርኩንና የሊቃነ ጳጳሳትን ሥልጣነ ክህነት የሚገልጽ ነው::
መስቀሉ በሞቱና በትንሣኤው ለቤተ ክርስቲያንን ድል ነሺነትን የሠጠ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሲሆን አርዌ ብርቱ ደግሞ በፓትርያርኮች እጅ የሚያዘው "ሙሴ በምድረ በዳ ዕባብን እንደሰቀለ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል" የሚለውን ቃል የሚያስረዳ ያለ በደል ስለ እኛ ተሰቅሎ ያዳነንን ክርስቶስን የሚያሳይ ነው:: ከታች ያለው "አምላኬ ጌታዬም" የሚለው የሕንድ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያ የሆነው የቅዱስ ቶማስ ምስክርነት ቃል ነው:: (ዮሐ. 20:28
⛪️ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አርማ
ከላይ የሚታየው የጳጳሳት አስኬማ ከሐዋርያት ጀምሮ በቅብብል የመጣውን የፓትርያርኩንና የሊቃነ ጳጳሳትን ሥልጣነ ክህነት የሚገልጽ ነው::
መስቀሉ በሞቱና በትንሣኤው ለቤተ ክርስቲያንን ድል ነሺነትን የሠጠ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሲሆን አርዌ ብርቱ ደግሞ በፓትርያርኮች እጅ የሚያዘው "ሙሴ በምድረ በዳ ዕባብን እንደሰቀለ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል" የሚለውን ቃል የሚያስረዳ ያለ በደል ስለ እኛ ተሰቅሎ ያዳነንን ክርስቶስን የሚያሳይ ነው::
ቁልፉ የአንጾኪያው የመጀመሪያ ፓትርያርክ ለሆነው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሠጠውን ሥልጣነ ክህነት የሚያሳይ ሲሆን ቁልፎቹ ሁለት መሆናቸው በጴጥሮስ ብቻ ያልተወሰነ መሆኑን ያስረዳል:: ሚዛኑ ፓትርያርኩ በፍትሕ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያስተዳድሩ የተሾሙ እንደሆኑ የሚያሳይ ሲሆን ከሥር በዓረቢኛ የተጻፈው ደግሞ "የአንጾኪያና የመላው ምሥራቅ ፓትርያርክ" የሚል ነው::
⛪️ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አርማ እና ትርጉም
፩ የአርማ ቅርፅ እና ይዘት
፩ . መደቡ ነጭ
፪ . ዙሪያው የስንዴ ዛላ እና የወይን ዘለላ
፫ . ከላይ ከአናቱ ከአክሊሉ ፣ ከታች ከግርጌው መሃል ለመሃል ወጥቶ አናቱ ከአክሊሉ ስር የደረሰና መስቀል ያለበት አርዌ ብርት
፬ . በግራ ሆኖ በቀኝ እጁ አርዌ ብረት በግራ እጁ ዘንባባ የያዘ መልዐክ ፣ በቀኝ ሆኖ በግራ እጁ አርዌ ብረት በቀኝ እጁ ዘንባባ የያዘ መልአክ
፭ ከአርዌ ብርት ሥር "ነዋ ወንጌለ መንግሥት " ተብሎ የተጻፈበት መጽሐፍ ቅዱስ
፮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥር የ "ጸ" ፊደል ቅርጽ የሚመስል ሁለት ጫፎች ከመደቡ ወደ ውጭ የወጣ ሰበን
፯ የስንዴ ዘለላ እና የወይን ዘለላ በሚገናኙበት የዓለም ምስል ያለበት ይሆናል
፪ የአርማው ትርጉም
☞☞☞☞☞☞☞
ሀ / መደቡ ነጭ መሆኑ
ዘመነ ስጋዌ የምሕረት የደስታ የነፃነት ዘመን መሆኑን ያመላክታል
ለ / የአርማው ዙሪያ በስንዴ ዘለላ እና የወይን ዘለላ መሆኑ ምእመናን በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት ፣ ስርየተ ኃጢአት የዘላለም ሕይወት የሚያገኙ መሆኑን
(ዮሐ ፮ ፥፶፫-፶፰ ማቴ ፳፮፥፳፮- ፳፱ መዝ ፬፥፯)
ሐ / በአርማው መሃል ቀጥ ብሎ የቆመ የአርዌ ብርት ምስል ከበላዩ ላይ መስቀል ከዚያም ከፍ ብሎ አክሊለ ክህነት መኖሩ ሕዝበ እስራኤል አርዌ ብርቱን ባዩ ጊዜ ከእባብ መርዝ እንደዳኑ ሁሉ መስቀል ላይ በተሰቀለው ጌታችን በአምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ከዲያቢሎስ ምክንያት የመጣባቸው ፍዳ ኃጢአት የሚድኑ መሆናቸውን መስቀሉም የቤተ ክርስቲያን የድኅነት አርማ መሆኑን ያሳያል
( ዘኁ ፳፮፥፰ ዮሐ ፫ ፥፲፬ )
መ / አክሊሉ
ቅዱሳን በሰማያዊ መንግስት የሚቀዳጁት አክሊል ክብር እና ማኅተመ ጽድቅን ያመላክታል
(ዘፀ ፴፱፥፱ ፩ተሰ ፪ ፥፲፱ ፪ጢሞ ፬ ፥፲ ፩ ጴጥ ፭፥ ፲፬ ራዕይ ፪፥፲ : ፲፥፲፬ )
ሠ / ሁለት መላዕክት የአርዌ ብረት እና የዘንባባ ዝንጣፊ መያዛቸው
ዘንባባ በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ደስታ ድኅነተ ነፍስን ያመላክታል:: ቅዱሳን መላዕክት የቤተ ክርስቲያን ጠባቂዎች እና የመልካም ዜና አብሣሪዎች መሆናቸውን ያሳያል የአርዌ ብርቱን ይዘው መቆማቸው ነገረ መስቀሉን አምኖና እምነቱን አጽንቶ ይዞ የሚኖር የዘላለም ድኅነት የሚያገኝ መሆኑን ያሳያል:: (መዝ ፺፥ ፲፩ ሉቃ ፲፫፥ ፮-፱ ዕብ ፩፥፲፬ )
ረ / በአርማ መሃል መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ በላዩ ላይ "ነዋ ወንጌለ መንግሥት" የሚል ጽሑፍ መኖሩ
የቤተ ክርስቲያን ሀይማኖት ቅኖና እና ትውፊት በመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያመላክታል ( ማቴ ፳፬ ፥ ፲፬ )
ሰ / የስንዴ ዛላና ዘለላ በተገናኙበት ቦታ የሚታይ ክብ ነገር ዓለምን የሚወክል ሲሆን ዓለም በክርስቶስ መዳኑን ያሳያል:: ( ዮሐ ፫፥ ፲፯ )
ማስታወሻ :- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አርማ ጃንደረባው ሚድያ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ሠርቶታል:: ዛሬ ምሽት ከሰርክ ጸሎት በኋላ ይፋ ይሆናል::
#ወደዚህ_ሠረገላ_ቅረብ
#የሚከለክለኝ_ምንድን_ነው
BY አትሮንስ ዘተዋህዶ-atronss zethewahdo
Share with your friend now:
tgoop.com/atronss/5400