tgoop.com/bahreTibebat/854
Last Update:
እንደተሰቀለ ሆኖ ይገለጥላቸው ነበር፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ለአቡነ መባዓ ጽዮን በመሠዊያው ላይ በነጭ በግ አምሳል ይገለጥላቸው ነበር፡፡ መከራ ሞቱን እያስታወሱ ሰውነታቸውን ይጎዱ እንደነበር በቅዱስ ገድላቸው ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡-
‹‹በተቀደሰች በዓርባ ጾምም የመድኃኔዓለምን ግርፋት እያሰበ ሰውነቱን በእጅጉ ገረፈ፡፡ ደሙ ከመሬት እስኪወርድ ድረስ ልቡንም አጥቶ ከምድር ላይ ወደቀ፡፡ የመድኃኔዓለምን መከራውን አስቦ እንደሞተም ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም ወደ እርሱ መጣና ‹ተነሥ እኔ ቁስልህን እፈውስሃለሁ› ብሎ የጀርባውን ቁስል ዳሰሰው፡፡ ምንም ሕማም እንዳላገኘውም ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችንን ‹በአንተው እጅ ትገደልን? እኔ እንኳ የተገደልኩት በአመፀኞች በአይሁድ እጅ ነው› አለው፡፡ በዚያችም ሰዓት ጌታ የመባዓ ጽዮንን ከንፈሮቹን ይዞ ሦስት ጊዜ እፍ አለበትና ‹የከበረ ትንፋሼም ከትንፋስህ ጋራ ይጨመር፣ ሥጋህም ከነፍስህ ጋራ የከበረ ይሁን› አለው፡፡ ‹አንተ በላዩ እፍ ያልህበትም የተቀደሰና የከበረ ይሁን› አለው፡፡››
ጌታችን ለአቡነ መብዓ ጽዮን የወርቅ በትር ሰጥቷቸው በእርሷ ነፍሳትን ከሲኦል ያወጡባት ነበር፡፡ መቋሚያዋም እሳቸው ካረፉ በኋላ የሚሞተውን ሰው እየለየች ትናገር ነበር፡፡ አባታችን እንደ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በመልአክ ተጥቀው ተወስደው የሥላሴን መንበር ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር አጥነዋል፡፡ ጌታችን ከተረገመችና ከተወገዘች ዕፅ ጋር በተገናኘ ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክና ለአቡነ መብዓ ጽዮን ልዩ ምሥጢር እንደነገራቸው በሁለቱም ቅዱሳን ገድላት ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡
አቡነ መብዓ ጽዮን በይበልጥ የሚታወቁት ሁልጊዜ ወር በገባ በሃያ ሰባት መድኃኔዓለምን አብልጠው በመዘከራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹እንደ አንተም በየወሩ በሃያ ሰባት የሞቴን መታሰቢያ ለሚያደርግ ነፍሳትን ከሲኦል አወጣለታለሁ›› የሚል ድንቅ ቃልኪዳን ከጌታችን ተቀብለውበታል፡፡ ይኸውም የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ የሚያድርግ ቢኖር ነፍሳትን ከሲኦል እንደሚያወጣ ሲነግራቸው ነው፡፡ ቅዱስ አባታችን ‹‹ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ! በዓልህን አደርግ ዘንድ አንተ የምትወደውን ግለጥልኝ›› ብለው ጌታችንን ሲጠይቁት እርሱም ‹‹የሞቴን መታሰቢያ ያደረገ እንደ እኔ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ ‹በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ይሠራል፣ ከዚያም የበለጠ ይሠራል› ብዬ በወንጌሌ እንደተናገርሁ› አላቸው፡፡›› ከዚህም በኋላ አባታችን ለልጆቻቸው እንዲህ ብለው መከሯቸው፡- ‹‹ክርስቲያኖች ሁሉ የፈጣሪያችንን የመድኃኔዓለም ክርስቶስን የመታሰቢያ በዓሉን እናድርግ፡፡ የአባቶቻችን የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት መታሰቢያቸው ባረፉበት በተሾሙበት ቀን ይከበራል፡፡ እነርሱን የፈጠራቸው እርሱ መድኃኔዓለም ነው፣ ያከበራቸው፣ ከፍ ከፍ ያደረጋቸው፣ ስማቸውን ለጠራ መታሰቢያቸውን ያደረገ እንደሚድን ቃልኪዳን የሰጣቸው እርሱ ነው፡፡ የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ ያደረገ ግን የተኮነኑ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ በሞቱም ጊዜ ሥቃይን አያያትም፡፡››
የአቡነ መብዓ ጽዮን በዓለ ዕረፍታቸውም እጅግ አብዝተው በሚዘክሩበትና ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ታስቦ በሚውለው በመድኃኔዓለም ቀን ጥቅምት ሃያ ሰባት ነው፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
አቡነ ጽጌ ድንግል፡- ደራሲና ማኅሌታዊ ሲሆኑ የላመ የጣፈጠ ከመብላት ተቆጥበው ጥሬ ቆርጥመው 9 ዓመት ከቆዩ በኋላ የእመቤታችንን ስደት በጣም በጥልቀት የሚተርከውን ‹‹ማኅሌተ ጽጌን›› የደረሱ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ውኃም በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር የሚጠጡት፡፡
አቡነ ጽጌ ድንግል ከደብረ ሐንታው ከአቡነ ገብረ ማርያም ጋር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ድርሰቱን በመዝሙረ ዳዊት መጠን 150 አድገው ደርሰዋል፡፡ አቡነ ገብረ ማርያምና አቡነ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌን በጥምረት ሊደርሱት የቻሉት አቡነ ገብረ ማርያም በወሎ ክፍለ ሀገር በወረኢሉ አውራጃ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ በሚባለው ገዳም የሕግ መምሕር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር በአንድነት አግልግለዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡-
አንድ ዓመት አቡነ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም 25 ቀን ከደብረ ሐንታ መጥተው ደብረ ብሥራት አቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ገብተው ከመስከረም 25 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ40 ቀን አገልግሎት ከአቡነ ጽጌ ድንግል ጋር ፈጽመው ኅዳር 8 ቀን ወደ ደብራቸው ደብረ ሐንታ ይመለሳሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አቡነ ጽጌ ድንግል ከገዳማቸው ከደብረ ብሥራት ተነሥተው ወደ ደብረ ሐንታ ሄደው እንዲሁ እንደ አቡነ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አግልግለው ይመለሳሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን እንደዚህ እያደረጉ በየተራ አንደኛው ወደ ሌላኛው ገዳም እየሄዱ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በፍጹም ፍቅርና በትሕትና አብረው እመቤታችንን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ ይኸውም በራሳቸው በአቡነ ገብረ ማርያም ገድል ላይ እና በአቡነ ዜና ማርቆስ ገድል ገጽ 72-73 ላይ በሰፊው ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ የሁለቱ ድርሰታቸው የሆነው ‹‹ማኅሌተ ጽጌ›› ድርሰት የእመቤታችንንና የልጇን የጌታችንን ሥጋዊ ስደት የሚገልጽ ሲሆን በጨማሪም ስደት የማይገባው አምላካችን ወደ አህጉራችን አፍሪካ ተሰዶ የሠራቸውን ድንቅ ድንቅ ተአምራትና የእመቤታችንን ንጽሕናዋን ቅድስናዋን አማላጅነቷን የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡
አባ ጽጌ ድንግል ከማኅሌተ ጽጌ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አስደናቂ ድርሰቶችን ደርሰዋል፡፡ የጻድቁ ቅዱስ ዐፅማቸው፣ ታቦታቸውና የደረሷቸው በርካታ ድርሰቶች በገዳማቸው ደብረ ጽጌ ውስጥ በክብር ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ አምሃራ ሳይንት ቦረና ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም የ5 ሰዓት የእግር መንገድ ከተሄደ በኋላ የሚገኘው ገዳማቸው ‹‹ደብረ ጽጌ›› ከአንድ ወጥ ዓለት ተፈልፍሎ የተሠራው ሲሆን አሠራሩም እጅግ ድንቅ ነው፡፡
የአቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ከአቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ጋር የሚያገናኘው ‹‹የእግዜር ድልድይ›› የተባለ አስገራሚ ታሪክ ያለው ድልድይ አለው፡፡ ሁለቱ ቅዱሳን በመንፈስ ተጠራርተው ለመገናኘት ቢያስቡም የወለቃ ወንዝ ሞልቶ በአካል ሳይገናኙ ቀሩ፡፡ በዚህም በጣም አዝነው ከወንዙ ወዲያና ወዲህ ሆነው ተላቅሰው አፈር ተራጭተው ወደየገዳማቸው ቢመለሱም ያ ተላቅሰው የተራጩት አፈር በተአምር ትልቅ ድልድይ ሆነ፡፡ ድልድዩን ሁለቱም በበዓታቸው ሆነው በመንፈስ አዩት፡፡ የበጎ ነገር ጠላት ሰይጣንም ይህንን ሲመለከት ድልድዩን በትልቅ ሹል ድንጋይ በስቶ ሊያፈርሰው ሲል አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመንፈስ አዩትና ከጋስጫ ተነሥተው በደመና ተጭነው በመሄድ ሰይጣኑን በግዘፈ ሥጋ ገዝተው ያንን ድልድዩን አፈርስበታለሁ ያለውን ትልቅ ሹል ድንጋይ አሸክመውት በዓታቸው ጋስጫ ድረስ ወስደውታል፡፡ ያ ድንጋይ ዛሬ በጋስጫ አቡነ ጊዮርጊስ ገዳም ለመነኮሳቱ ደወል ሆኖ እያገለገለ ይኛል፡፡ ድልድዩም እስከ አሁን ድረስ ለአካባቢው ኢስላም ማኅበረሰብ ብቸኛው የወለቃ ወንዝ መሻገሪያቸው ሆኖ እያገለገላቸው ነው፡፡
BY ባህረ ጥበባት
Share with your friend now:
tgoop.com/bahreTibebat/854